Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፈተና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ዕውቀት መለኪያ ነው!

0 483

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፈተና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ዕውቀት መለኪያ ነው!

ዮናስ

በመላ አገራችን  የ2009 ዓ.ም. አገር አቀፍ ፈተናዎች ተጀምሯል።የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተጠናቆ የመሰናዶ ተማሪዎች የማጠቃለያ ፈተና እየተሰጠ ነው። ከሞላ ጎደል የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በስኬት የተጠናቀቀ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ገጥመዋል የተባሉት ችግሮች ግን አሳሳቢ እና የዚህ ጽሁፍ መነሻ ምክንያት ሆነዋል ።

በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች  647 የፈተና ጣቢያዎች 311ሺህ ተማሪዎች  ለ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ለፈተና ተቀምጠዋል፡፡በፈተናው ሂደት በሀዋሳ ፣ በወላይታ ሶዶና በአርባምንጭ ከተሞች የፈተና መልስ ይዘናል በሚል ተፈታኞችን አጨብርብረዋል ተብለው የተጠረጠሩ የኮሌጅ ተማሪዎች በህብረተሰቡና በፖሊስ ትብብር መያዛቸውን የተመለከተው የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ የመጀመሪያው መነሻ ነው፡፡በተመሳሳይ በሃዋሳ፣ ዲላ፣ አርባምንጭ፣ ሆሳዕና እና ጂንካ ከተሞች ሀሰተኛ መልስ ሲሸጡ የነበሩ ግለሰቦች በህብረተሰቡ ጥቆማ ተይዘው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑም ተጨማሪው መነሻ ነው።

በጋምቤላ ክልል በተሰጠው የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለሌሎች ተማሪዎች ለመፈተን የሞከሩ 56 ግለሰቦች መያዛቸውን የተመለከተው ዜናም ሌላኛው እና ከፈተና ዓላማና ግብ ጋር የተጣረሰው መነሻ ነው። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይልቃል ከፍአለን ዋቢ ያደረጉ መረጃዎች እንዳመለከቱት ደግሞ ተፈታኞችን በማደናገር የውሸት መልስ በሞባይል መልእክት በመላክ ለማሳሳት የተሞከረ ቢሆንም ድርጊቱ ለማዘናጋትና ለማደናገር ሆን ተብሎ የተፈፀመ መሆኑን በማስረዳት ተማሪዎች ተረጋግተው እንዲፈተኑ ተደርጓል።

ባለፈው ዓመት ፈተና ስለመሰረቁና ተፈታኞች ጋር ስለመድረሱ በመወራቱ ተማሪዎች ላይ ደርሶ የነበረውን ከፍተኛ ጫና ምክንያት በማድረግ መንግስት የወሰደው ጥንቃቄ እነዚህን ሃይሎች በቁጥጥር ስር ለማዋል ቢያስችልም አስተሳሰቡ ግን አሁንም ያሳስባል።

ፈተናው በሶስት ሺህ 500 ጣቢያዎችና 72 ሺህ የትምህርት ባለሙያዎች፣ የፖሊስ አባላትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተጠናቀቀ ሲሆን ፤በውጭ አገራትም በሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሪያድና ጂዳ እንዲሁም በሱዳን በሚገኙ የኮሚኒቲ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች በተመሳሳይ ፈተናውን ወስደዋል። ከግንቦት 23 እስከ 25 ቀን 2009 ዓ.ም በተካሄደው የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አንድ ሚሊዮን 206 ሺህ 869 ተማሪዎች የተቀመጡ ሲሆን 46 ነጥብ 74 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው።

ከላይ የተመለከቱት መነሻዎች የሚያረጋግጡት ነገር አንዳንድ ወጣቶች በተዘጋጁበት ልክ ውጤትን ከማግኘት ይልቅ በአቋራጭ ፈተና ኮርጀው ከክፍል ወደክፍል እንሸጋገራለን የሚል የተዛባ አመለካከት የሚያራምዱ መሆናቸው አሁንም ያልተጠናቀቀ ሃገራዊ ጉዳይ መሆኑን ነው።

በሃሰት የተሰረቀ ፈተና እንዳላቸው በመግለጽ ርካሽ ጥቅም ለማጋበስ እና የተማሪዎችን ስነ-ልቡና ለመስረቅ የሚራወጡ ህገ ወጦች መኖራቸውን የሚያጠይቁ መነሻዎች ሲሆኑ  እነዚህን መሰል ወንጀለኞችም በተመሳሳይ እየተሰጠ በሚገኘው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ላይ የሚያጋጥሙ መሆናቸውንም የሚያመላክትና እነዚህን ተማሪዎችና ህብረተሰቡ ማጋለጥ እንደሚገባቸው የሚያስገነዝብ ነው።

የፈተና ስርቆት እና ኩረጃ ተግባር በትምህርት ጥራት ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ባሻገር የነገ አገር ተረካቢው ትውልድ ከእውቀት ፍለጋ ይልቅ ስርቆትን ባህሉ ያደረገ እንዲሆን በማድረግ የአገራችንን እድገት ወደኋላ የሚመልስ ጸረ ልማት ወንጀል ነው።በየደረጃው የሚሰጡ ፈተናዎች ከካሪኩለሙ ጋር አያይዞ በቀጣይ ወደ ትምህርትና ሥልጠና የሚሄዱ ተማሪዎች እነማን እንደሆኑ ለመለየት የሚያስችል ወይም የመለየት ሥራ ነው፡፡ ኩረጃ የዝግጅት ማነስ፤ ወይም ፍርኃት ነው ሲሉ የሚከራከሩ ቢኖሩም ከላይ የተመለከቱት መነሻዎች ከነዚህም ባሻገር ኪራይ ሰብሳቢነትና በአቋራጭ የመበልጸግ ፍላጎት ጭምርም መሆኑን የሚያጠይቁ ናቸው፡፡ በኩረጃ የተገኘ ውጤት የትም የማያደርስ ከመሆኑ እውነታ ስንነሳ ደግሞ ፍርሃትና የዝግጅት ማነስ የሚሉት ምክንያቶች ውሃ አያነሱም፡፡  

ከላይ በተመለከቱት መነሻዎች አግባብ ኩረጃን ማስቀረት የሚችለው አንደኛ ተማሪው፣ ሁለተኛ መምህሩ (ፈታኙ) እና ሱፐርቫይዘሩ ናቸው፡፡ ከዚህ የበለጠ ደግሞ የአካባቢው ማኅበረሰብና ወላጆች ናቸው፡፡ ዋነኛ ሊሆን የሚገባው የወላጆች ስራ ግን ከሆነ በኋላ ማጋለጡ ሳይሆን ወላጆች ልጆቻቸው በርትተው እንዲያጠኑ መደገፍ እና ሰርቀው የሚያመጡትን ውጤት ማውገዝ ነው፡፡ከላይ የተመለከቱት መነሻዎችና ሰሞንኛ መሸኛዎች የሚያጠይቁት ሌላ ነገር ተደራጅተው ገንዘብ በማዋጣት ፈታኞችን አግባብተውና ጉቦ ሰጥተው ውጤት ለማስቀየር የሚተጉ ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች በየአካባቢው መፍላታቸውን ነው።  

ይህንን ለመከላከል የሚያስችል ሌላ ስርአት መዘርጋቱ በእርግጥ ሙከራዎቹን ለማክሸፍ ቢያስችልም ከፈተና አላማና ግብ አኳያ ግን አስተሳሰቡን መፋለም ያስፈልጋል። አዲሱ የአሰራር ስርአት እስካለፈው ዓመት ድረስ የፈተና ጥያቄዎች፣ የመልስ መስጫ ወረቀቶችና ሌሎች ሎጂስቲኮችን በፈተና ጣቢያዎች የሚያሠራጩት የኤጀንሲው ሠራተኞች የነበሩበትን አሰራር የሚቀይር ነው፡፡ይኸውም በፈተና አሰጣጥ ላይ የሚሳተፉ የትምህርት ባለሙያዎች ኤጀንሲው ድረስ እየመጡ እንዲረከቡና እንዲወስዱ የሚያደርግ አሰራር ሲሆን፤ ከዚያም የፈተናው ጥያቄና የመልስ መስጫው ወረቀት በፖሊስ አካባቢ በጥበቃ ሥር እንዲቆይ የሚያደርግ መሆኑም ከላይ የተመለከቱት ሙከራዎች እንዲከሽፉ አስችሏል፡፡ ይህ አሰራር ጥንቃቄን እንጂ ዘላቂ ከሆነው በእውቀት የታነጸ ትውልድ ከመቅረፅ አኳያ ፋይዳ የሌለው በመሆኑ ትግሉ አሁንም አስተሳሰብና አመለካከት ላይ ሊሆን ይገባዋል።

የትኛውም ተማሪ በአንደኛው ፈተና ባይሆንለት ተጨማሪ የመማሪያ ጊዜ የሚሰጠው ስለመሆኑና በዚህ ሂደት  ውጤት ይዘው የወጡ በርካታ ተማሪዎች ስለመኖራቸው ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ አንድ የፈተና ውጤት ተፈታኙ አሁን ያለበትን ደረጃ የሚገልጽ እንጂ፣ የበለጠ ይሠራል ወይም አይሠራም የሚል የመጨረሻ መገለጫ አይደለም፡፡ ወይም ተማሪውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወስን አይደለም፡፡ትግሉም  ሰዎች ራሳቸውን ቶሎ ቀይረው የሚያጠኑና የሚማሩ ከሆነ ምንም ነገር መያዝ የማያቅታቸው መሆኑን ያገናዘበ ሊሆን ይገባዋል። ትግሉ የፈተና ኩረጃ ትውልድ ገዳይ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባዋል። ትግሉ  እውቀትን እንጂ ፈተናን የማይኮርጅ ትውልድ መገንባት ነው።በፈተና ስርቆት የሚመጣ ነገር ቢኖር ውድቀታችንን ማፋጠን ብቻ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy