Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌዴራላዊ ስርዓቱ እንዲጎለብት ከዜጎች ምን ይጠበቃል?

0 245

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፌዴራላዊ ስርዓቱ እንዲጎለብት ከዜጎች ምን ይጠበቃል?

                                                   ታዬ ከበደ

የአፈና አገዛዝ፣ የግፍ ቀንበር ተጭኖት የኋላቀርነትና የበታችነት ተምሳሌት ተደርጎ ይታይ የነበረው የብሔር ብሔረሰቦቿ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ የህዝቦቿ መኩሪያና መከበሪያ፣ የሀገራችን መድመቂያ ጌጥና የመልካም ገጽታዋ መገለጫ ወደ መሆን ተሸጋግሯል፤ ባለፉት 26 ዓመታት፡፡

የተለያየ እምነትና የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመግባባትና በመረዳዳት መንፈስ አብሮ በመኖር በዓለም የሚታወቁበት የመቻቻል ባህልም ከመቼውም በላቀ ሁኔታ በመዳበር ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ታሪካዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ የጋራ እሴቶቻችን ለሀገራችን ተጨማሪ ክብርና ሞገስ ከማላበስ አልፎ ለፈጣን ልማት ስራዎቻችን የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ወደሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል፡፡

ይህን ዕድል በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ችለዋል፡፡ መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም እየሰመረ ነው፡፡ “የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንደሚባለው ይህ የዕድገት ጉዞ ገና በለጋ ዕድሜው ብቻ የበርካታ አፍሪካዊ ወንድሞቻችንን ቀልብ ከመሳብ አልፎ፤ በአርአያነት እየተጠቀሰና በሞዴልነትም እየተወሰደ ነው፡፡

ርግጥ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን አርአያና መኩሪያ የሆነው የሀገራችን ህዝቦች የሚከተሉት ዕድገት ብቻ አይደለም፡፡ ለዕድገቱ ያበቃን የምንከተለውና በህገ መንግስቱ አማካኝነት እውን የሆነው ፌዴራላዊ ስርዓታችንም የህዝቦች መፈቃቀድና በጋራ የመኖር መቻቻል አኳያ ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ ይህ አብነታዊ የፖለቲካ ስርዓት በርካታ ቁጥር፣ ባህልና ቋንቋ ብሎም ትውፊቶች ያላቸው ህዝቦች እንደምን ተከባብረውና ተፈቃቅረው መኖር እንደሚችሉ ማሳያ ሆኗል።

ለነገሩ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ረጅሙንና አስቸጋሪውን የትግል ምዕራፍ በድል አድራጊነት በቋጩ ማግስት በጋራ ተወያይተውና አምነው ያፀደቁት ህገ – መንግስት የዘመናት ጥያቄዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ የመለሰ ከመሆኑም ባሻገር፤ በቀጣይ ለሚያካሄዷቸው የጋራ አጀንዳዎች ዘላቂነትና ውጤታማነት ዋስትና የሰጠ ነው፡፡

በሀገራችን እውን የሆነው ፌዴራላዊ የመንግስት ስርዓት አወቃቀር ለሀገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ የዚህ አዲስ ስርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው፡፡ የተገነባው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ ከብረት የጠነከረ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን አስገኝቷል

በዚህም ሳቢያ የሀገራችን ህዝቦች ህገ- መንግስቱን ይጠብቁታል፤ ይንከባከቡታልም፡፡ ምክንያቱም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከህገ – መንግስቱ ጋር በብዙ መልኩ የጠበቀ ቁርኝት አላቸው፡፡ እዚህ ላይ ሶስት ትስስሮችን ማንሳት እችላለሁ፡፡ የመጀመሪያው የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህገ- መንግስቱ ባለቤቶች መሆናቸው ነው፡፡ ህዝቡ ህገ- መንግስቱን ያቋቋመ፣ የመንግስትን አወቃቀርም የነደፈ ነው። ይህም በህገ- መንግስቱ ላይ በግልፅ ሰፍሯል፡፡

ሁለተኛው ትስስር የሀገራችን ህዝቦች ህገ -መንግስቱንና ህገ- መንግስታዊ ሥርዓቱ ከማንኛውም የወስጥም ይሁን የውጭ ፀረ ሰላም ሃይሎች በጽናት አንዲጠበቅላቸው የመሻታቸው ጉዳይ ነው፡፡ በመሰረቱ ህገ- መንግስቱም ይሁን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆኑ፤ ስርዓቱን ከማንኛውም አደጋ የመጠበቁ ኃላፊነትም የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነው፡፡ ታዲያ ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ማንኛውም ዜጋ በተናጠልም ይሁን በተደራጀ መልኩ ህገ -መንግስቱንና የሥርዓቱን ደህንነት መጠበቅ የዕለት ተዕለት ስራውና አደጋ ሊያንዣብብ ከቻለም ግንባር ቀደም ተሰላፊ የመሆን ኃላፊነት አለበት፡፡ ምክንያቱም በህገ- መንግስቱ ዕውን ያደረገው ስርዓት የራሱ ስለሆነ ነው፡፡

በሦስተኛነትም በትስስርነት የሚነሳው ጉዳይ ህዝቡ የህገ- መንግስቱ ባለቤትና ጠባቂ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚም የመሆኑ ዕውነታ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደሞከርኩት የኢፌዴሪ ህገ- መንግስት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዘመናት ጥያቄን የመለሰ እንዲሁም ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ዋስትና የሰጠ ነው፡፡

ህገ – መንግስቱ ጸድቆ በስራ ላይ ከዋለ ጀምሮ ሀገራችንና ህዝቦቿ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች እጅግ ውጤታማ ተግባራት አከናውነዋል፡፡ እነዚህን ውጤቶች አቅቦ ከመጓዝና ለአዳዲስ ድሎች ከመብቃት አኳያም፤ በአሁኑ ወቅት መንግስትና መላው ህዝብ በላቀ ቁርጠኝነት እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁኔታም የሀገራችን የድህነትና ኋላቀርነት ገፅታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲለወጥ እያደረገ ነው፤ ሂደቱም እጅግ በተጋጋለ ሁኔታ እንዲቀጥል ፈር እያስያዘ ነው፡፡

ሀገራችን በሁሉም የልማት ዘርፎች የምታስመዘግባቸው የዕድገት መገለጫዎች ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የህዝባችን ተጠቃሚነት ደግሞ የሀገራችንን ዕድገት የሚያፋጥን መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል— የኢፌዴሪ ህገ- መንግስት የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለፈውን መጥፎ ታሪክ የሻረ ከመሆኑም በላይ፤ መጻዒ ዕድላቸውን ብሩህ ያደረገ ነው የሚባለው፡፡

ህገ- መንግስቱ በሀገራችን ታሪክ በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ እንዲፈጠርም ያደረገ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ከደርግ ውድቀት ማግስት በኋላ የተረጋጋችና ህዝቦቿም አንድ የጋራ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ስርዓት መስርተው እርስ በርሳቸው እየተከባበሩ በፈጠሩት ፈጣን ልማት ተቋዳሽ የሚሆኑበትን ሀገር ለመገንባት ከባድ ትግልን ጠይቋል፡፡ ታዲያ ይህን ሃቅ የማይቀበሉ ፅንፈኞች ትናንትም ነበሩ፣ ዛሬም አሉ። ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ መኖራቸውም አይቀርም፡፡

እናም ይህን በህዝቦች መስዕዋትነት የተገኘን ፌዴራላዊ ስርዓት ለመንጠቅ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ዜጎች ማጋለጥና እኩይ ዓላማቸውንም እንዳያስፈፅሙ በንቃት መከታተል አለባቸው፡፡ እነዚህ ሃይሎች የሚፈልጉት ህዝቡ በመስዕዋትነቱ ያገኘውን ድል መንጠቅ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ፍላጎታቸው እንዳይሳካ ዜጎች የስርዓቱን ጠቀሜታዎች በማስረዳት አሊያም ተጠቃሚነታቸውን በመግለፅ ተግባራቸውን ሊኮንኑት ይገባል፡፡ ይህን ሲያደርጉም ፌዴራላዊ ስርዓቱ እንዲጎለብት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy