Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሕገ መንግስት

0 283

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሕገ መንግስት

                                                         ታዬ ከበደ

መንግስት ድህነትንና ኋላቀርነትን በመዋጋት ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆነበትን ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን እውን በማድረግ ላይ ያተኮረ አሰራርን ዘርግቶ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። በሀገራችን ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የተጀመረው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀ ነው።

በህገ መንግሥቱ የተቀመጡ የልማት መብቶችና ዓላማዎችን ለማረጋገጥ የግብርና መር የኢንዲስትሪ ልማት ስትራቴጂ ተቀይሷል፡፡ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብትም የተመሰረተው በግብርና ላይ ነው፡፡ ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ሕዝብ 85 በመቶው የሚኖረውም በገጠር ነው፡፡ የሚተዳደረውም በግብርና ሥራ ነው፡፡ አገሪቱ በብዛት ያላት የጉልበትና የመሬት ሃብት ከግብርናው ዘርፍ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ይህም ሆኖ የግብርናው ዘርፍ ባለፉት ሥርዓቶች እጅግ ትኩረት የተነፈገውና ሲበዘበዝም የኖረ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ህገ መንግሥቱ በሚደነግገው ፍትሀዊና የሕዝብን ጥቅም ማዕከል ባደረገው ልማት መሠረት በመንግሥት ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት የአገሪቱን  በአጠቃላይ በገጠር የሚኖረውን ሕዝብ የሚጠቅም ግብርናና ገጠርን ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ በሥራ ላይ ውሏል፡፡

ስትራቴጂው ፈጣን እድገት ለማረጋገጥ፣ ሕዝቡ ከልማቱ በላቀ ደረጃ እንዲጠቀም  ለማድረግ፣ ኢትዮጵያን ከተመጽዋችነት ለማዳን እና በአገሪቱ የዳበረ የነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል፡፡ በተጨባጭ እየተረጋገጠ ያለውም ይኽው ነው፡፡

በዚህ መሠረት የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓትን በመከተል ግብርና ዋና የኢኮኖሚ እድገት ምንጭ ሆኖ የኢንዱስትሪ ልማቱ እንዲፋጠን ስትራቴጂው ከኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶችና ማህበራዊ አገልግሎቶች ማለትም ትምህርት፣ ጤናና ውኃ እንዲሁም ከከተማ ልማት ጋር ትስስርና ተመጋጋቢነት ባለው አግባባ ተፈፃሚ በመሆን ላይ ነው፡፡

የግብርናው ዘርፍ በግብርና የሚተዳዳረውን ኅብረተሰብ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ያደረገ ነው፡፡ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በሚመራው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከተሳትፎና ከተጠቃሚነት አንፃር መንግሥት በዋነኛነት ለጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቷል፡፡

የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት መስፋፋት የሥራ እድል በመፍጠር የዜጐች ገቢ አቅምና የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ ያስችላል፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለልማታዊ የአገር ውስጥ ባለሀብት መፈጠር መሠረት እንደሚሆኑም ታምኖበታል፡፡ ጎን ለጎንም መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በግሉ ባለሃብትና በመንግስት በማስፋፋት የኢንዱስትሪ፣ የቴክኖሎጂና የሙያ አቅም እንዲዳብር እየተደረገ ይገኛል፡፡  

ይህም አቅጣጫ በህገ መንግሥቱ የተቀመጡ ፍትሃዊነት፣ የህዝብ ተጠቃሚነትና የተሳትፎ ብሎም ነፃ አገራዊ ኢኮኖሚ የመገንባት ድንጋጌዎችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በህገ መንግሥቱ ከሰፈሩ ድንጋጌዎች ጋር የተቆራኙ የማህበራዊ ልማት ስትራቴጂና የመሠረተ ልማት ማስፋፋት ኘሮግራሞች ተነድፈው ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በዚህም በህገ መንግሥቱ የተቀመጡትን የህዝብ ተጠቃሚነትንና አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ዓላማዎችን ያካተተ ነው፡፡

በማህበራዊ ልማት ዘርፍም መንግሥት መሠረታዊ ለውጦችን አድርጓል፡፡ የትምህርት ዘርፉ ሲታይ ባለፉት ሥርዓቶች ሽፋኑ አነስተኛ ሥርጭቱ ደግሞ አድሏዊ ነበር፡፡ መንግሥት በህገ መንግሥቱ የተደነገጉ ሁሉም ዜጐች ትምህርት የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥና ተደራሽነቱም ፍትሃዊ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ አዘጋጅቶ ሥራ ላይ አውሏል፡፡ ውጤትም ተገኝቶበታል፡፡

በኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶች ዘርፍ መንግሥት ትኩረት የሰጠው ለመንገድ፣ ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ለኃይል ማመንጫ፣ ለቴሌኮምና ለባቡር ልማቶች ነው፡፡ መንግሥት እነዚህ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ፍትሃዊነትንና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ እና አገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር ሁኔታ እንዲቀርቡ ለማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

ለዘላቂ እድገትና ልማት እንዲሁም ፍትሀዊ የሕዝብ ተጠቃሚነት የሰው ኃይል ልማት ወሳኝ መሆኑ ይታመንበታል፡፡ ቀደም ሲል የነበረው የትምህርት ሥርዓት ሽፋን አነስተኛ፣ ኢ ፍትሃዊ እና ጥራቱና አግባብነቱ መሠረታዊ ችግር ነበረበት፡፡ አሁን ይህ ሁኔታ ተሻሸሏል። በትምህርት ጥራት ረገድ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ርብርብ እየተደረገ ነው።

በዘርፉ የተከናወኑና የተገኙ መልካም ውጤቶች የዜጐችን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻል፣ ዜጎች በመረጡት ቦታና የሥራ መስክ እንዲሰማሩ ከማድረግ፣ ሁሉም አካባቢዎች እኩል የመልማት እድል እንዲያገኙ ከማስቻልና አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ከመገንበት አንጻር ወሳኝ ድርሻ አላቸው፡፡

እርግጥ ይህ ውጤት የተገኘው መንግሥት ለመንገድ ልማት ኘሮግራሙ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ቅድሚያ ትኩረት እንዲያገኝ በማድረጉ ነው፡፡ ለአገሪቱ ቀጣይ የምጣኔ ሀብት እድገት በወሳኝ መልኩ ከሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች ውስጥ አንዱ ኢነርጂ ነው፡፡

ድህነትን ለመቀነስና ብሎም ዘላቂ ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ርብርብ የኤሌክትሪክ ዘርፍ ለግል ኢንቨስትመንት መስፋፋትና ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ከፍተኛ አስተጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ በመሆኑም እያደገ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍላጎት ለማርካት መንገስት በኤሌክትሪፊኬሽን ዘርፍ ለውጥ አምጥቷል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜኝን ዕቅድ ላይ እስከ 10 ሺህ ሜጋ ዋት ለማመንጨት ታቅዷል።

የመሠረተ ልማት ኘሮግራሞች አንድ የኢኮኖሚና የፖሊቲካ ማኅበረሰብን የመፍጠርና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የማጠናከር ህገ መንግሥታዊ ግብም ለማሳካት የበኩላቸውን ድርሻ ተጫውተዋል፡፡ ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ግንኙነትንም አጠናክረዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ አሁንም በዘርፉ መሠረታዊ ችግሮች ይታያሉ፡፡

የመሠረተ ልማት ኘሮግራሞቹ ከፍተኛ ፋይናንስንና የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ መሆናቸው፣ የመሠረተ ልማት ኘሮጀክቶችን የማስፈፀም አቅም ውስንና በውጭ አማካሪዎችና ኮንትራክተሮች ላይ የተንጠለጠለና የተለያዩ ማነቆዎች የሚያጋጥሙ መሆኑ ብሎም ያሉት የመሠረተ ልማት ተቋሞች ዘመናዊ መሠረተ ልማትና አገልግሎት የማስተዳደደር ብቃት ማነስ ቁልፍ ችግሮች ሆነው ወጥተዋል፡፡

በእነዚህ መሠረታዊ ችግሮች ሣቢያም አሁንም የመሠረተ ልማት ሽፋንና ጥራት ጉድለት በሰፊው ይታያል፡፡ ስለሆነም በቀጣይ እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች በተሰጠው አቅጣጫ መነሻ በመፍታት የተጀመረው የመሠረተ ልማት እመርታ ዳር እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡ ህገ መንግሥታዊውን ሥርዓት ተከትሎ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በተመለከተ ትልቅ እርምጃ ወደፊት ተራምዳለች፡፡ እርምጃዎቹ ሕገ መንግስቱ ያስገኛቸው ናቸው፡፡ ይህም ሕገ መንግስቱ ባለፉት ዓመታት የህዝቦችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ መሆኑን ያመላክታል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy