Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍልን የሚያረጋግጥ በጀት

0 306

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍልን የሚያረጋግጥ በጀት

                                                  ቶሎሳ ኡርጌሳ

የኢፌዴሪ መንግስት ሰሞኑን ለ2010 የበጀት ዓመት ከ320 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አፅድቋል። በጀቱ ከ2009 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር የ46 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወይም የ16 ነጥብ 9 በመቶ ብልጫ አለው። ከበጀቱ አጠቃላይ የመደበኛና ካፒታል የመንግስት ወጪ በጀት ውስጥ 61 ነጥብ 8 በመቶ ያህሉ ቅድሚያ ትኩረት ለተሰጣቸው ዘርፎች የሚውል ነው። እነዚህ ዘርፎች ትምህርት፣ መንገድ፣ ግብርና፣ ውሃና የተፈጥሮ ሃብት እንዲሁም የጤና እና የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራሞች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ለወጣቶች የተዘዋዋዋሪ ፈንድ፣ ለከተማ ልማትና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ከፍ ያለ በጀት ተይዟል።

ከበጀቱ ውስጥ 114 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለካፒታል፣ 81 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 7 ቢሊየን ብር ለዘላቂ ልማት እና 117 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለክልሎች ድጋፍ የተመደበ ነው። ለክልሎች የተበጀተው ድጋፍ የ36 ነጥብ 6 በመቶ ድርሻ አለው። ይህ የሆነውም በክልሎች ውስጥ በርካታ ስራዎች ስለሚከናወኑ በጀቱ ከፍ ሊል ችሏል። በተለይ ዘላቂ የልማት ግቦችን የሚያጠናክር 7 ቢሊዩን ብር እንዲካተት ተደርጓል። የአግሮና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት እንዲሁም ስራ ፈጠራ ዕድል በቂ ትኩረት የተሰጠው ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የካፒታል በጀት ከአጠቃላይ በጀቱ የ35 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ ያለው ነው። መደበኛ በጀቱ ግን ካለፈው የበጀት ዓመቱ ጋር ሲነፃፀር የአንድ ነጥብ አራት በመቶ ብልጫ ያለው ነው። ይህ ሁኔታም መንግስት ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ በጀት ትኩረት እንደሰጠ የሚያሳይ ነው። መንግስት የመደበኛ በጀቱን ይህ ነው በማይባል ደረጃ ከፍ ሳያደርግ አብዛኛውን የጭማሪ ወጪውን የሀገሪቱንና የህዝቡን የአኗኗር ዘይቤ መለወጥ በሚያስችሉ ልማታዊ ጉዳዩች ላይ ማድረጉ ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍልን ይበልጥ እውን ለማድረግ ማለሙን የሚያሳይ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት እንደ መንግስት ሀገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጀቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። ይህም በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ባለሁለት አሃዝ ዕድገት ውጤት ነው። ዕድገት እየጨመረ በሄደ ቁጥር የህዝቡ የኑሮ ደረጃ መለወጡ አይቀርም። የኑሮ ደረጃውን ለማሟላት ደግሞ መንግስት በቂ በጀት መመደብ ይኖርበታል። ለውጥ እስካለ ድረስ ያንን ለውጥ ማስፈፀም የሚችል የበጀት አቅም መኖር እጅግ አስፈላጊ ነው።

በርግጥ በሀገራችን እየተመዘገበ ለሚገኘው ለውጥ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው ጉዳይ የጠራ መስመር የያዘ፣ ሀገራዊውን ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ በተግባር ላይ የሚያውል አመራርና በህዝባዊ ተሳትፎ የተደገፈ አቅጣጫን የሚከተል የልማታዊ መንግስት አካሄድ መሆኑን ማንም የሚስተው ሃቅ አይደለም።  

መንግስት ሀገሪቱንና ህዝቦቿን ከድህነት ኋላቀርነት ለማላቀቅ የነደፈው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተግባራዊ በማድረግ ተስፋ ሰጪ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ያለና የውጭው ዓለም የመሰከረለት መሆኑን በጀቱ የሚገልፅ ይመስለኛል። ርግጥም የኢትዮጵያ መንግስት ሀገሪቱ ከገባችበት የድህነትና ኋላቀርነት ማጥ ለማውጣት የሚያስችል ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ነድፎ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ እስካሁን ድረስ እየፈፀማቸው ያሉት ልማታዊ ተግባራት ውጤትአምጥተዋል። የውጤቶቹ መገለጫም የቀጣዩ በጀት ዓመት በጀት ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ልማታዊ የኢኮኖሚ አውታሩ ፈጣን ልማትን የማረጋገጥና ህዝብን በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እያደረገ ነው። በዚህም ባለፉት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ በአነስተኛና ጥቃቅን የተሰማሩ ወደ በሚሊዩን የሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል ማግኘት ችለዋል። በሀገሪቱ ገጠራማ ክፍልም አርሶ አደሩ እያካሄደ ያለውን ምርትና ምርታማነት የማሳደግ እንቅስቃሴ በእጅጉ ውጤታማ በመሆኑ፤ ሞዴል ሚሊዮነር አርሶ አደሮች እንዲፈጠሩ ያደረገ ነው። ይህ ደግሞ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እየተደረገ ያለውን ሽግግር የሚያፋጥን መሆኑ አይቀሬ ነው። ለ2010 ዓ.ም የተያዘው በጀት ይህን ዕውነታ ካማሳካት አኳያ የራሱ ሚና ይኖረዋል።

ሀገራችን በአሁኑ ወቅት መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ በገጠርም ሆነ በከተማ የምታከናውነው የልማት ርብርብ የህብረተሰቡ የኑሮ ደረጃ እንዲቀየር ማድረጉ የማይካድ ሃቅ ነው። እናም አብዛኛዎቹ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገቱ በዚሁ ከቀጠለ በቀሚቀጥሉት ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱ ባስቀመጠችው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ጎራ ለመሰለፍ ያስችላታል። መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርም እውን የማይሆንበት ምክንያት የለም። የቀጣዩ ዓመት በጀት ይህን ሚና በመጫወት ረገድ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በጀቱ የዜጎችን የትምህርት፣ የጤናና የንፁህ መጠጥ ውኃ …ወዘተ ተጠቃሚነት የመሳሰሉት መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚያስችሉ የማህበራዊ አገልግሎት እንዲዳረሱ በማድረጉ በኩል አስተዋፅኦ አለው። ይሀም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ታዳጊ ሀገራት እንዲያሳኩት ያስቀመጠውን ቀጣይነት ያላቸውን የልማት ግቦች ለማሳካት ያስችላል።

የአዲሱ ዓመት በጀት መንግስት የካፒታል ወጪዎችን ለመሸፈን ብድርና እርዳታ እንዲቀነስ ማድረግ ችሏል። በዚህም ከግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ 80 ነጥብ ሶስት ቢሊዩን ብር ከእርዳታ 10 ነጥብ ሶስትና ከብድር ደግሞ 20 ነጥብ ሶስት ቢሊዩን ብር ለማግኘት ታቅዷል። ይህም አብዛኛው የሀገሪቱ በጀት የሚገኘው ከሀገር ውስጥ ከሚሰበሰብ በጀት ሆኗል። ይህም መንግስት በጀቱን በአብዛኛው በሀገር ውስጥ ከሚገኝ ሃብት ለማግኘት ያሰበና የሀገሪቱም በጀት በሂደት ራሱን እንደሚችል አመላካች ነው።

በጀቱ ዘላቂ ልማትን በማምጣት ድህነትን ለማስወገድ ቁልፍ ሚና ባለቸው ክፍላተ- ኢኮኖሚዎች የመሰረተ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት የምጣኔ ሃብት ትራንስፎርሜሽንን በማረጋጋጥ ላይ ያመዘነ ነው። መንግስት ከሀገሪቱ በጀት ከፍተኛ ድረሻውን የሚመደበው ለመሰረተ ልማት ማስፋፊያ እንዲሁም ለትምህርትና ለጤናው ዘርፍ ነው። ይህ የሚያመላክተው መንግስት በዜጎች መካከል ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ያለውን ፍላጎት ነው።

የኢፌደሪ መንግስት በባህሪው ህዝባዊ ነው። ይህ ህዝባዊ መንግስት የሚያከናውኗቸው ማናቸውም ጉዳዩች የሚያከናውነው ህዝብን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ነው። መንግስት የትኛውንም ተግባር የሚያከናውነው ህዝቡን ማዕከል አድርጎ በመሆኑ በጀቱም ህዝቡ ከተገኘው ልማት በፍትሐዊነት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የሚያረጋግጥ ነው። በአጠቃላይ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ልማት ሽግግር እንዲመጣ መንግስት የበጀተው በጀት፤ በተለይም በክልሎች ውስጥ ስራ ፈጠራን እውን በማድረግ፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን በመታገልና ህይወትን በመለጠጥ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፤ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትንም ያረጋግጣል። ይህ በጀት በአግባቡ በታሰበው የልማት ትልም ላይ እንዲውል በአፈፃፀሙ ላይ ሀዝቡ የበኩሉን ሚና መጫወት ይኖርበታል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy