ፕሮጀክቱ የሁላችንንም ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል!
ደስታ ኃይሉ
የኢፌዴሪ መንግስት የህዳሴውን ግድብ ፕሮጀክት ሲያቅድ ጀምሮ ያራምደው የነበረው “በተፋሰሱ አገራት መካከል ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል’’ የሚለው መርህ አሁንም የተጠበቀ ነው። ኢትዮጵያ ከጋራ ተጠቃሚነት ውጭ የትኛውንም ሀገር የመጉዳት ፍላጎት የላትም። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ከሁሉም ሀገራት ጋር በጋራ ማደግን በመርህነት የያዙ ናቸው። አንዲ ሲያድግ ሌላውም እንደሚያድግ ይገነዘባሉ። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚያራምዱት አቋምም ይህንኑ ነው።
የሀገራችን መንግስትም ሆነ የግድቡ ባለቤት የሆኑት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓባይ ጉዳይ ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ አቋማቸው ፅኑ ነው። የግድቡ ግንባታ ለአንድ ደቂቃም ቢሆን አይቋረጥም። ዓላማቸው ድህነትን ማቸነፍ ብቻ ስለሆነም ግንባታው ለአፍታም ቢሆን እንዲስተጓጎል አይፈቅዱም። ይህ ፅኑ አቋማቸው መቼም ቢሆን ሊለወጥ አይችልም—ድህነትን መቅረፍ ብሎም ማስወገድ የሞትና ሽረት ጉዳያቸው ነውና።
ሀገራችን ለመስኖና ለኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫነት ያሚያገለግሉ በርካታ ወንዞች ያላት በመሆኗ ሳቢያ የምስራቅ አፍሪካ “የውሃ ማማ” በሚል ስያሜ ብትታወቅም በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ የመጠቀም መብቷ ተገድቦ መቆየቱ ከማናችንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የሚጠቀሱት ሀገሪቱን ጨምድዶ ይዞ የነበረው የከፋ ድህነት እንዲሁም ያለፉት መንግስታት የአስተሳሰብ ውስንነት መሆናቸው እሙን ነው፡፡
ታዲያ በህዝብ ተሳትፎና በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ራዕይን የሰነቀው የኢፌዴሪ መንግስት፤ የህዝቡን ልማታዊ ተጠቃሚነትን በየደረጃው የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ለውጤት በመብቃቱ ከላይ የተጠቀሱን ሁለት ተግዳሮቶች በአስተማማኝ ሁኔታ መፍታት ችሏል። በዚህም የዘመናት ቁጭታችን የሆነውን በተፈጥራዊው የውኃ ሀብታችን የመጠቀም መብታችንን በበቂ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ታጅቦ በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡
በእርግጥ የግብጽ መንግስታት በናይል ውኃ የብቻ ተጠቃሚነትን እንደ ታሪካዊ መብት ባለቤትነት ሲያጣቅሱ መደመጣቸው የሚገርም ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት መብትን በተለያዩ ዘዴዎች እያደናቅፉ ዘመናትን ሲቆጥሩ የኖሩ በመሆናቸው ነው፡፡ ለማንኛውም ትናንት ዛሬ አይደለምና ሀገራችን ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት እያስመዘገበች በመሆኑ፤ በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ በመጠቀም መብቷ በማትደራደርበት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በአሁኑ ወቅት እየተጠናከረ የመጣው የህዝቧ የልማት ቁርጠኝነት እንዲሁም መንግስት የሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ዘላቂና ከባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆን ችለዋል፡፡ ይህ ተግባሯም ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ ውጭ አሮጌና ዘመን ያለፈባቸው አስተሳሰቦች ዋጋ ቢስ መሆናቸውን ያረጋገጠ ነው፡፡
ለዚህም ነው ኢትዮጵያ አሮጌው የቅኝ ገዥዎች ስምምነት የተፋሰሱ ሀገራትን በውሃው እኩል ተጠቃሚነት እንዲሆኑ በሚያደርገው የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ መተካት ለአማራጭና ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በየጊዜው በመግለፅ ላይ የምትገኘው፡፡
ታዲያ ሀገራችን ስምምነቱን ስትቀበል በምክንያታዊነት ላይ ተመስርታ መሆኑን ልብ ማለት ያሻል፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ደረጃ የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት የሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት መብት የሚያስጠበቅና እኩል ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ እንጂ ልክ እንደ ቅኝ ገዥዎቹ ስምምነት በጣት ለሚቆጠሩ ሀገሮች መብት የቆመ አለመሆኑን ስለምትገነዘብ ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ስምምነቱ በዓለም አቀፉ የውሃ አጠቃቀም መሰረታዊ መርሆዎች ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀና ህጋዊ መሰረት ያለውና ህገ ወጥ ስምምነቶችን በተለይም የቅኝ ግዛት ውሎችን በጽኑ የምትቃወም ሀገር ስለሆነች ነው።
እናም አሮጌው ስምምነት በአዲሱ የመተካቱ አስፈላጊነት ከፍተኛ እንደሆነ ታምናለች፡፡ በመሆኑም ዕውቅና የምትሰጠው አብዛኛው የተፋሰሱ ሀገራት ለተስማሙበት የኢንቴቤው ስምምነትን እንጂ እንደ መከራከሪያ ነጥብ ለሚጠቀሰው የቅኝ ገዥዎች ሰነድ አይደለም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን የትኛውም ወገን ያሻውን ቢልም፤ ሀገራችን እንደ ማንኛውም ሀገር በውሃ ሃብቷ በመጠቀም ህዝቦቿን ከድህነት የማላቀቅ መብት እንዳላት ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ሀገራቱ በውሃ ሀብታቸውን ተጠቅመው የምግብ ዋስትናቸውን እንዲሁም የሃይል አቅርቦትን በማሳደግ ለኢንዱስትሪው ኢኮኖሚ ምቹ ሁኔታ መፍጠርን ዋነኛውና ወሳኙ አማራጭ አድርገል፡፡ በዚህም የዘመናት በደላቸውን ወደ ጎን በመተው በሆደ ሰፊነት በውሃው እኩል ተጠቃሚነት ላይ ለሁለት አስርት ዓመታት ሲደራደሩ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ታዲያ ይህ ሂደት አንድ ትልቅ ግንዛቤን ያስጨበጠናል፡፡ እርሱም የተፋሰሱ ሀገራት በውሃው የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ብቻ መመስረታቸውን እንዲሁም ይህ ሃሳባቸው ማንንም ለመጉዳት የታሰበ አለመሆኑን ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን ተጎጂ ያደረጉት ሁለቱም የቅኝ ገዥዎች ስምምነቶች ከግብጽና ከሱዳን በስተቀር ሌሎቹን የተፋሰሱ ሀገራት ያገለሉና በሃይል ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን ለድርድር አቅርባ የማታውቅ የጥቁር ህዝቦች መኩሪያ ሀገር ናት። ከባርነት፣ ከጭቆና እና ከቅኝ ተገዢነት ለመላቀቅ ብርቱ ትግል ላደረጉ በርካታ የዓለማችን ህዝቦች አርአያና ምሳሌያቸው እስከ መሆንም ደርሳለች።
ፈለጓን የተከተሉ በርካታ አፍሪካውያንም ባስመዘገቡት ድል ባለውለታነታቸውን በብዙ መንገድ ገልጸውላታል። የሰንደቆቻቸው ቀለማት በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት እንዲደምቅ ማድረጋቸውም አንዱ ማሳያ ነው። መሰል የኩራትና የክብር መገለጫ ያላት ሀገር በሌላ ገጽታዋ ደግሞ በጥቁር ቀለም የተከተበ ታሪክም አላት- ስሟ ከረሃብና ድህነት ጋር ደጋግሞ የሚያስነሳ ጠባሳ። ዛሬ ግን የሀገሪቱ መንግሥትና መላው ህዝብ ይህን ጠባሳና ቁስል በመፋቅ ታሪክ ለመለወጥ በጋራ ተነስተዋል።
ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ረሃብና ጦርነት ሲነሱ የኢትዮጵያን ስም አብሮ መነሳቱ ማብቃት አለበት ብለው ቆርጠዋል። ‘ለዚህ ሁሉ ያደረሰን ዋነኛ ጠላታችን ማነው?’ ብለው ጠይቀው ትክክለኛውን ምላሽም አግኝተዋል። ድህነትንም ዋነኛው ጠላታችን ነው ብለው ደምድመዋል። ጎረቤቶቻቸውን፣ በተለይም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ ለማድረግ በእኩልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ የግንኙነት ፖሊሲን ቀርፀውም እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ‘ድህነትንም እንዴት እናስወግዳለን?’ ብለው መክረው መፍትሔ ካበጁም ቆይተዋል። በሁሉም መስክ ፈጣን ልማትን ሊያመጡላቸው የሚችሉ አቅጣጫዎችን መከተል ብቸኛ አማራጫቸውን ከማውጣትም ባሻገር፤ በትግበራ ሂደቱ ላይ የጋራ መግባባትን እየፈጠሩ ነው። ይህ መግባባታቸውም ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንጂ የትኛውንም ሀገር የመጉዳት ዓላማ የሌለው መሆኑን የትኛውም አካል ሊረዳላቸው ይገባል እላለሁ።