Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህዝባዊው ፕሮጀክት

0 230

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህዝባዊው ፕሮጀክት

ዳዊት ምትኩ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚገነቡት ህዝባዊ ፕሮጀክት ነው። የሀገራችን ህዝቦች የግድቡ ግንባታ እውን ከሆነበት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የህዝቡ ጥረት ዛሬም ድረስ አልተቋረጠም። በአሁኑ ወቅትም የህዝቡ ተሳትፎ አላቋረጠም። የግድቡ ግንባታ የነገ ታላቅ ሰው መሆኑን የሚያልመው የኢትዮጵያ ህዝብ እየተረባረበ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ካለፉት 26 ዓመታት ወዲህ ነባሩ የሽንፈትና የድህነት ካባ ቀስ በቀስ እየተቀየረ በመምጣት ላይ መሆኑ ከማንም በላይ ምስክር የሚሆነው የችግሩ ተቋዳሽ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡

በተለይም መንግስት ውጤታማ የሆኑ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀይሶ ምልዕዓተ ህዝቡን ባሳተፈ አኳኋን የጀመረው ያልተቋረጠው ርብርብ ባለፈው አስር ዓመት ውጤታማ ፍሬ ማፍራት ታሪካችንን በአዲስ መልክ ቀይሮታል። ባለ ሁለት አሃዝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ በአዲስ የዕድገት መዝገበ ቃላት ላይ መመዝገብ ችለናል—ከሰሃራ በታች ነዳጅ ከሌላቸው ሀገሮች ቀዳሚ የዕድገት ተምሳሌት በመባል።

ከዘመናት በፊት ያለፈው ትውልድ ለእኛ አወርሶን የሄዱው የአክሱምና የላሊበላ ስልጣኔ- ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ጥበብ በመሆኑ በኩራት ለቱሪስት መስህብነት እየተጠቀምንበት ያን ትውልድ እያስታወስነው ነው፡፡ የእኛው ትውልድም ይህን ታላቅ የልማት ፕሮጀክት ዕውን አድርጎ ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ በአዲስ ምዕራፍ ደማቅ የዕድገት ታሪክ ለመፃፍ ሌት ተቀን እየሰራ ነው። ይህም ለመጪው ትውልድ ልማትንና ብልፅግናን እንጂ ልመናን ያለማውረስ ራዕይን የሰነቀ ነው፡፡ የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ጀምሮ መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት በመነሳሳት ለግንባታው አጋርነታቸውን መግለፃቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ይህን ለማደግ ያላቸውን ፍላጎትንና መልካም ተግባራቸውን አሁንም በልበ ሙሉ አጠናክረው እየቀጠሉ ናቸው፡፡ በእስካሁኑ የግድቡ ግንባታ ከ58 በመቶ በላይ እስኪደርስ ድረስ በአራቱ ማዕዘናት የሚገኙት መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ርብርብ ከማድረግ አለተቆጠቡም፡፡

በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ በተለያዘለት የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ እንዲችልም ህዝቡ ባለው አቅም በሙሉ ፍቃደኝነትና ቁርጠኝነት ዕገዛ ሲያደርግ በዚህ ታሪካዊ ግድብ ላይ አሻራውን ማስቀመጡ ዕደለኛ መሆኑን ደጋግሞ እየገለፀ ነው። በተለያዩ ጊዜያት ሰልፍ በመውጣት እንዲሁም ልዮ ልዮ መድረኮችን በማዘጋጀት በየመንደሩና በየቤቱ ሁሉም የጋራ አጀንዳ አድርጎታል፡፡

ለዘመናት በማንም ሳይደፈር የቆየውን የዓባይ ወንዝን በመድፈር ለሀገር ልማት እንዲውል መደረጉ ሁሉንም ዜጋ በአንድ ልቦና ያስተሳሰረ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በዕውቀቱ ለመደገፍ የገባውን ቃል አሁንም ቀጥሏል፡፡ በዚህም ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ የተለያዩ ሃይሎች የፈለጉትንና ያሻቸውን ቢያወሩም ዛሬም ድረስ ለአንድ ሰከንድ እንኳን አልተቋረጠም፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ለግንባታው ማስፈፀሚያ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚል መንግስት ያዘጋጀውን ቦንድ በመግዛት የበኩሉን ተወጥቷል፤ እየተወጣም ነው፡፡ የቦንድ ግዥውን እያከናወኑ ያሉት የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ናቸው—ከህፃን እስከ አዋቂ ድረስ። ለዚህም ነው ‘የህዳሴው ግድብ ግንባታ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለ ፕሮጀክት ነው’ እየተባለ የሚነገረው፡፡

በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዚሁ ግድብ ግንባታ እየፈጸሙት ካለው ቀላል የማይባል የቦንድ ግዥን ጨምሮ ካሉበት ቦታ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት የግድቡን ግንባታ በመጎብኘትና ሌሎች ኢትዮጵያዊንም አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በማነሳሳት ረገድ በቀላሉ የማይገመት ሚና ተጫውተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሀገራችን ህዝቦች በተጨማሪ እንደ ሱዳን ያሉ የጎረቤት ሀገራት ዜጎች ለግድቡ ግንባታ ቦንድ እስከመግዛት መድረሳቸው ግድቡ ምን ያህል ቀጣናዊ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው።

እርግጥ ማናችንም እንደምናስታውሰው የኢትዮጵያውያን የትላንት ታሪክ ሀገር በወራሪዎች ስትደፈር በአንድ ላይ በመዝመት ጠላት ላይ ድል መንሳት ነበር፡፡ ይሁንና ከዚህ ሀገርን ከጠላት መከላከል ተግባር በዘለለ ህዝቡ ለልማት የተባበረ ክንድ እንዳይኖረው ያለፉት መንግስታት ቁርጠኝነት እንዳልነበራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ዳሩ ግን የኢፌዴሪ መንግስትና ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የትኛውም የሀገራችን ቀደምት መንግስታት ደፍረው የማያውቁትን በአባይ ወንዝን የመጠቀም መብታችንን ካወጀ ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ህዝብ እጅና ጓንት ሆኖ በተገኘው የልማት አጋጣሚ ያለ ዕረፍት እየሰራ ነው። ወትሮም ቢሆን ይህ ድህነት ያንገሸገሸው ህዝብ ‘እንስራና ሀገራችንን በጋራ እንገንባ’ የሚል መንግስት አጥቶ እንጂ፤ በተፈጥሮው ስንፍና ኖሮበት አይደለም፡፡ ስለሆነም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በውጭ ሀገር ያሉት ወገኖቻችን ጭምር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረጉት ያለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና ሊቸረው የሚገባ ይመስለኛል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከምንም በላይ ህዝቦች በተፈጥሮ ሃብታቸው ማልማት እንዲችሉና ድህነትን ታሪክ በማድረግ ዘመቻ ላይ በጋራ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያነሳሳ ነው፡፡ በእኔ እምነት ይህ ታላቅ ፕሮጀክት የሰንደቅ ዓላማችን ፕሮጀክት ሆኗል። ለዚህም አንድም ግድቡ ሲጠናቀቅ ሊሰጠው የሚችለው ጠቀሜታ እኛን ብቻ ሳይሆን ከዓባይ ጋር የተቆራኙ ሃገሮችን የሚጠቅም መሆኑ፣ ሁለትም ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶቻችን አቅማቸውን በመገንባት እንደገና ለተጨማሪ ታሪክ እንድንዘጋጅ አዲስ ምዕራፍ ሊከፍት የሚችል ማሳያ መሆኑ በምክንያትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ይመስለኛል፡፡

የግድቡ ግንባታ ይፋ ከሆነ ጀምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አስተሳሰብ ለውጧል፡፡ ዜጎች ዛሬ ላይ ሆነው የዚህን ታሪካዊ ግድብ የቦንድ ግዥ መፈጸማቸው ግድቡ አልቆ ነገ ለሚወልዷቸው ልጆች ክስተቱን በታሪክነት የመናገር ጉጉታቸውን ጫፍ ላይ ያደረሰ ግድብ ሆኗል ማለት ይቻላል።

እዚህ ላይ በግድቡ ዙሪያ ከተሰጡት አስተያየቶች ውስጥ አንድ የሃይማኖት አባት በአንድ ወቅት የተናገሩትን ማንሳት አስፈላጊ ይመስለኛል። ይኸውም የሃይማኖት አባቱ “ዛሬ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የድጋፍ ማሰባሰቢያ በማህጸን ላይ ካሉት ህጻናትና በመቃብር ካሉት ሙታኖች በስተቀር፣ የበኩሉን አስተዋጽኦ የማያደርግ ኢትዮጵያዊነቱን መጠራጠር ይገባል” ያሉት ነው። ይህ አባባል በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የማደግ ቁጭት የሚያሳይ ይመስለኛል። የትናንት የተዛነፈ ማንነትን በአዲስ ማንነት የመቀየር ፅኑ ፍላጎትም ጭምርም ነው። ይህ ግድቡን ዕውን የማድረግ ህዝባዊ ስሜት ዛሬ ላይ ባለበት የግለት መንፈስ ውስጥ ይገኛል። በመሆኑም በእኔ እምነት ህዝቡ ዛሬም ተግባሩን በብቃት እንዲወጣ ቀስቃሽ የሚያስፈልገው አይመስለኝም—ስለ ግድቡ ያለውን ዕውነታ በሚገባ ይገነዘባልና። ስለሆነም የህዳሴው ግድብ የሚገነባው በህዝቦች ተሳትፎ እንደ መሆኑ መጠን የሚያወዛግቡ ጉዳዩችን ወደ ጎን በማለት ለግድቡ ዕውን መሆን አሁን ካለው በበለጠ ሁኔታ መረባረብ ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy