Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ አፍሪካዊ አቋሞች የተሰጠ እውቅና

0 424

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ አፍሪካዊ አቋሞች የተሰጠ እውቅና

                                                        ዘአማን በላይ

የአፍሪካ ህብረት ግማሽ ክፍለ ዘመንን የተሻገረ ተቋም ነው። በዚህ የጎልማሳነት ዘመኑ ከምስረታው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) ከጥንስሱ ጀምሮ አሁን እስከሚገኝበት የህብረትነት ቁመናው ድረስ ኢትዮጵያዊያን ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ ዕውቅና ሰጥቷል። ይህ የህብረቱ እውቅና ሰሞኑን የህብረቱ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ የአህጉሪቱ መሪዎች ባካሄዱት 29ኛ መደበኛ ስብሰባቸው ላይ የተወሰነ ነው። በዚህም ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ለቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉስ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለነበሩት ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ አስረስ የመታሰቢያ ሃውልት በህብረቱ ፅህፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዲቆምላቸው ውሳኔውን አሳልፏል።

ቀዳማዊ ኃይለስላሴ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረትና እንዲጎለብት እንዲሁም በምስረታው መባቻ ላይ የአህጉሪቱ መሪዎች “የሞርኖቪያ” እና “የካዛብላንካ” በሚል በሃሳብ ለሁለት ሲከፋፈሉ የአስታራቂነት ሚና በመጫወታቸው እንዲሁም በወቅቱ ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን ነፃነት ላበረከተችው አስተዋፅኦ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሃውልታቸው እንዲቆም ተወስኗል።

የዓለም ሀገራት “World Class Mind” (የዓለም ምርጥ አዕምሮ ባለቤት) እያሉ የሚጠሯቸውና የአፍሪካዊያን ድምፅ መሆናቸው የሚነገርላቸው እንዲሁም የአፍሪካዊያን የእርስ በርስ መገማገሚያ መድረክን (ኔፓድ) ሃሳቡን በማመንጨትና በመምራት እንዲሁም በቡድን ስምንትና 20 ጉባኤዎች ላይ አፍሪካን በመወከል የአህጉሪቱ ጥቅሞች እንዲከበር ምዕራባዊያንን ሳይቀር የሚያስደምም ሃሳብ በማቅረብ የሚታወቁት ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊም ሃውልታቸው በመታሰቢያነት በህብረቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዲቆም ተወስኗል። ከዚህ በተጨማሪ የህብረቱ 29ኛ የመሪዎች ጉባኤ ለታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ መታሰቢያ እንዲሆን ውሳኔ አሳልፏል። ይህም ኢትዮጵያ ሁሌም በአፍሪካ ጉዳዩች ላይ ላላት ቁርጠኛ አቋም የተሰጠ ምላሽ ነው።  

በእኔ እምነት ይህ የህብረቱ ውሳኔ ለሁለቱ የሀገራችን የቀድሞ መሪዎች ብቻ የተሰጠ ዕውቅና አይደለም። ህብረቱ ከምስረታው ጀምሮ አሁን እስካለበት ቁመናው ድረስ መላው ኢትዮጵያዊያን ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ የተሰጠ እውቅና ጭምርም ነው። ምክንያቱም እውቅናው መላው ኢትዮጵያዊያን ትናንትም ይሁን ዛሬ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻቸው ነፃነትና ሰላም መሆን ላበረከቱት አስተዋፅኦ የተበረከተ ነው። እንዲሁም የመዲናችን ነዋሪዎች ከ50 ዓመታት በላይ የአፍሪካ መሪዎች አዲስ አበባ ሲሰበሰቡ ጉባዔያቸው በሰላም እንዲጠናቀቅ መሪዎቹን በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት ባህሪ መንገድ ላይ ቆመው በአክብሮት ሲቀበሉና ሲሸኑ ኖረዋል። እናም እውቅናው ለሀገሪቱ ዜጎች ሁሉ የተሰጠ ነው ማለት ይቻላል።

አዎ! እውቅናው እንደ ሀገር የሁሉም ዜጋ ነው። ለዚህም ነው—የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የህብረቱን ጉባኤ መጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ “ህብረቱ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከአፍሪካ አንድነት ድርጀት ምስረታ ጀምሮ ለአፍሪካ ህብረት ላበረከተቸው አስተዋፅኦ እውቅና ሰጥቷል” በማለት የተናገሩት።

ታዲያ እዚህ ላይ የአፍሪካን አጀንዳዎች ከመወሰን ባለፈ ማስፈፀምና ለተግባራዊነቱ ይሰራ ዘንድ የቀረበው የሪፎርም ማሻሻያ ተቀባይነት ያገኘበት፣ ለአህጉሪቱ ይበጃሉ በተባሉና ተፈፃሚ በሚሆኑ አጀንዳዎች ላይ ህብረቱ ትኩረቱን እንዲያደርግ የተወሰነበት 29ኛው የአፍሪካ ህብረተ የመሪዎች ጉባኤ ለእርሳቸው መታሰቢያ እንዲሆን ስለተወሰነላቸው አቶ መለስ ዜናዊ ለህብረቱ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በጥቂቱ ማውሳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ተገቢም ነው ብዬ አምናለሁ።

የአቶ መለስ የገዘፈ ስብዕና ሀገራቸው በአስተማማኝ ሰላም፣ በፈጣን ልማትና ስር በሚሰድ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማስፈን ጥረታቸው የሚነሳ ነው። ለጥቆም የምስራቅ አፍሪካን ቀጣና በተለይም የኤርትራ መንግስት ሀገራችንንና ምስራቅ አፍሪካን የጦርነት አውድማ ለማድረግ የቀመረውን የሽብር ስትራቴጂ በቅርበት በመከታተል ብቃትና ብስለት ባለው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ እየተመሩ ሻዕቢያ ለመፍጠር የሞከረውን ቀጣናዊ ቀውስ ለማርገብ በቁርጠኝነት ሲሰሩ የነበሩ የአፍሪካ ልጅ መሆናቸውን ማስታወስ ይቻላል።

ምን ይህ ብቻ። ታላቁ መሪ በወቅቱ በምስራቅ አፍሪካ ሰማይ ላይ አንዣቦ የነበረውን የጦርነት ደመና ብስለት በተሞላው ዘዴ ማስወገድ የቻሉ መሪ ናቸው። በወቅቱ የኢጋድ አባል ሀገራትንና አፍሪካ ህብረትን ከጎናቸው በማሰለፍ የሶማሊያ አክራሪ ፅንፈኞች አከርካሪያቸው እንዲሰበር ማድረግ ችለዋል። በዚህም በአንድ በኩል እንደ መንግስት በአስተማማኝ ዲፕሎማሲ የሚመሩ መሆናቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፤ በሌላ ረገድ ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት መፈፀም የሚችል ቁመና እንዳለው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ አስተማማኝ ወታደራዊ ዲፕሎማሲ የገነቡ ታላቅ መሪ ናቸው።

ታላቁ መሪ በኢጋድና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ ባከናወኑት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ሌሎች ሀገራትም ሰራዊታቸውን ወደ ሶማሊያ እንዲልኩ የማግባባት ተግባራትን ተግባርን መፈፀማቸውንም እናስታውሳለን። ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት ሰብዓዊ ጥፋት ያስከተሉ ጦርነቶች የተካሄዱበትን ይህን ቀጣና ማረጋጋት ቀላል ባይሆንም፤ እርሳቸው ግን ለሰላምና መረጋጋት ጠንቅ የሆኑ አካሄዶችን በሳል በሆነና ብቃት ባለው አካሄድ እየተመሩ ያጋጥሙ የነበሩ ፈተናዎችን በድል መወጣት የቻሉ የአፍሪካ ውድ ልጅ ናቸው።

ከምስራቅ አፍሪካ ባለፈም የመላው አፍሪካ ድምፅ በመሆን ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን ወደ ማግኘትም የተሸጋገሩ መሪ ነበሩ—አቶ መለስ ዜናዊ አስረስ። አፍሪካውያን በመሠረታዊ የጋራ ጥቅም ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም እንዲወስዱ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የአህጉሪቱ ቃል አቀባይ ሆነው ውጤት ማስገኘት የቻሉ የአፍሪካ ተቆርቋሪ ናቸው።

በተለይም በየዓመቱ በአማካይ በሁለት ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይጨምራል ተብሎ በሚጠበቀው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ “አፍሪካ ዋነኛዋ ተጎጂ ናት” በማለት የምዕራቡ ዓለም በኢንዱስትሪ ሳቢያ ለፈጠረው የካርቦን ልቀት ለአህጉሪቱ ካሣ እንዲከፍል በመጠየቅ ከአፍሪካ ህዝቦች ባሻገር ከራሳቸው ካደጉት ሀገራት ጭምር አንቱታን ለማትረፍ የበቁ የአፍሪካ ጥቅም አስከባሪ መሪ ናቸው። ታላቁ መሪ አቶ መለስ በኮፐንሃገን፣ በሜክሲኮ…ወዘተ በተካሄዱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔዎች፤ አፍሪካ በለውጡ ይበልጥ ተጎጂ የሆነችው የአየር ንብረቷ ተጋላጭ፣ ለውጡን ለመቋቋም ያላት ገንዘብና ቴክኖሎጂ ውስን እንዲሁም አህጉሪቱ ዕድገቷን በአዲስ አማራጭ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ለመገንባት ያላት አቅም ከበለጸጉት ሀገሮች በአያሌው ያነሰ መሆኑን በማስረዳት በብርቱው የተከራከሩና አበረታች ውጤት ያመጡ ናቸው። በዚህ ተግባራቸውም የአፍሪካ አለኝታና መከታ መሆናቸውን በአደባባይ አስመስክረዋል።

የዲፕሎማሲ እምቅ አቅማቸውንና ክሂላቸውን የተገነዘበው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፤ በተለይም የበለፀጉት ሀገራት በቡድን ስምንት እና 20 ስብሰባዎች ላይ ከሚገኙት በጣት የሚቆጠሩ የአፍሪካ መሪዎች ውስጥ በቀዳሚነት ያደረጋቸው መሆኑን አንዘነጋም። ዛሬም ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም ሀገራችንንና አህጉሪቱን በመወከል በበለፀጉት ሀገራት ጉባኤዎች ላይ እየተገኙ የአፍሪካን አቋም እያንፀባረቁ ነው።

ይህም ኢትዮጵያ በንጉስ ኃይለስላሴም ይሁን በሀገር ውስጥ ጨፍጫፊ በነበረው መንግስቱ ኃይለማርያም እንዲሁም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊና በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አመራር ወቅት ለአፍሪካዊያን ነፃነትና ጥቅም መጠበቅ ያላቸው አቋም ተመሳሳይ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ኢትዮጵያውያን በማንኛውም ሥርዓትና ጊዜ ለአፍሪካውያን ታማኞችና አጋር መሆናቸውን፣ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ከ850 ሺህ በላይ አፍሪካውያን ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ የምትገኝ  እንዲሁም  ለአፍሪካ ህብረት ውሳኔዎች ሁሌም ተገዥ መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው። ለዚህም ነው— ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤“…ለአፍሪካ አጀንዳዎች ቅድሚያ የምትሰጠውን ኢትዮጵያንና የቀድሞ መሪዎቿ በህብረቱ ለሰሩት ስራና ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከህብረቱ ለተሰጠው እውቅና እና ክብር በኢፌዴሪ መንግስት ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ያሉት።

አዎ! ኢትዮጵያዊያን አፍሪካዊያን ሰላም እንዲጠበቅ በርካታ አስተዋፅኦዎችን አድርጋለች። በንጉስ ኃይለስላሴ ዘመን ወቅት በኮሪያና በኮንጎ ልሳነ ምድሮች ሰራዊቷን በማዝመት፣ በሽግግር መንግስቱ ወቅት በሩዋንዳ እንዲሁም ከኢፌዴሪ መንግስት ምስረታ በኋላ በብሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን በዳርፉርና በአብዬ ግዛት ብሎም በሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይሎችን አሰማርታ መስዋዕትነት በመክፈል አፍሪካዊ ኃላፊነቷን በብቃት የተወጣች ሀገር ናት።

በአሁኑ ወቅትም አፍሪካዊያን በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች በጋራ ትስስር እንዲያድጉ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ትገኛለች። ለምሳሌ ያህልም በመሰረተ ልማት ዘርፍ ረገድ፤ ሁሌም ለሰላምና ለልማት በሩን ክፍት ከማያደርገው ከኤርትራ መንግስት በስተቀር ከሌሎች አጎራባቾቿ ጋር በመንገድ፣ በባቡር መስመር፣ በአውሮፕላን በረራ፣ በታዳሽ ኃይል ኤሌክትሪክ አቅርቦት ለመተሳሰር ጥረት እያደረገች ነው። ይህም ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያንን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር፤ በጋራ ለምቶና ተጠቃሚ ሆኖ እጅ ለእጅ ተያይዞ የማደግ የዕድገት መስመርን እንደምትከተል የሚያሳይ ነው።  

ታዲያ እነዚህ እውነታዎች የአፍሪካዊያን ወሳኝ አጀንዳዎች ውሳኔ የተሰጠባቸው 29ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ እንደ ሀገር እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ለቀዳማዊ ኃይለስላሴና ለታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የመታሰቢያ ሃውልት እንዲቆምላቸው መወሰኑ አግባብነት ያለው መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው።

እናም አፍሪካዊያን ለሀገራችንና ለመላው ዜጎቿ ብሎም ብሎም ለሀገራችን የቀድሞ መሪዎች ዕውቅና መስጠታቸው ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። የኢፌዴሪ መንግስትም እውቅናው እውን እንዲሆን ላደረገው ተከታታይ የዲፕሎማሲ ጥረት እንዲሁ ሊመሰገን ይገባል። እውቅናው የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ላካሄዷቸው የዲፕሎማሲ ስራዎች የተሰጣቸው ምላሽ ነው። የዲፕሎማሲ ድልም ጭምር። ታዲያ በህብረቱ የተሰጠው ይህ እውቅና ሀገራችን ነገም እንደ ትናንቱና ከትናንት በስቲያው የአፍሪካውያን የነፃነት ፈርጥ፣ የሰላማቸው አለኝታ እንዲሁም የዕድገታቸው አነሳሽና ቀያሽ ሞተር ሆና እንድትቀጥል የሚያደርጋት መሆኑን በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy