Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መልካም አስተዳደር የህዝቡንም ብርቱ ጥረት ይጠይቃል!

0 289

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መልካም አስተዳደር የህዝቡንም ብርቱ ጥረት ይጠይቃል!

                                  ዳዊት ምትኩ

በያዝነው ዓመት የጥልቅ ተሃድሶ ተካሂዷል። በዚህ የጥልቅ ተሃድሶም ከመልካም አስተዳደር አኳያ በተጨባጭ አበረታች ውጤት ተገኝተዋል። ይህ ውጤት የተገኘው በሁሉም ክልሎች ውስጥ የሚገኘው ህዝብ የጥልቅ ተሃድሶው አካል በመሆን በሂደቱ ስለተሳተፈ ነው። ውጤቱ ጠንክሮ መሰራት ከተቻለ በሚቀጥለው የበጀት ዓመትም ተደማሪ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ህዝቡ ወሳኝ ሚናውን መጫወት ይኖርበታል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ይህን የህዝብ ወሳኝ ሚና ለማጎልበት ዕቅድ መያዙ ይታወቃል። እንደሚታወቀው ሁሉ ልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ለመገንባትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማዳከም የዛሬ 15 ዓመት ገደማ በተካሄደው የመጀመሪያ ተሃድሶ ተግባራዊ መሆን ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መልካም ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ታዲያ አሁንም በገጠር ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት ያለው እንዲሆንና የግብርናና የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት የበለጠ መትጋት ያስፈልጋል።

በአንፃሩም በከተሞች የበላይነት ያለው የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቡ ዛሬም ስር የሰደደ መሆኑን ነው። እናም ልማታዊነትን ይበልጥ በማጐልበትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ከምንጩ በማድረቅ ፖለቲካ ኢኮኖሚው ልማታዊ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡

ይህን የዕቅዱን ትልም ዕውን ለማድረግ የፖለቲካ አመራሩና የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛው ከህዝቡ ጋር በተደራጀ መንገድ በመቀናጀት መስራት ይገባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ‘ይህ ስራ የእገሌ ነው’ ሳይባል ሁሉም የበኩሉን ገንቢ ሚና ሊጫወት ይገባል።

እርግጥ ሀገራችን አረጋግጠዋለሁ ብላ ለተነሳችው የህዳሴ ጉዞ ትልልቆቹ አደጋዎች ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። እናም አደጋዎቹን ለመዋጋትና ትግሉን በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ  እሳቤ የበላይነት ለመደምደም በርካታ ስራዎችን ማከናወን የግድ በመሆኑ በዕቅዱ ተይዟል።

በተለይም የመንግሥትን ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ይበልጥ የማስፈፀምና አገልግሎቶችን ለዜጐች በብቃት የማድረስ ዋና ተልዕኮ የተሸከሙት ልማታዊ የፖለቲካ አመራሩና የሲቪል ሰርቪስ የመፍጠር እንዲሁም በሁሉም የአስተዳዳር እርከኖች በየደረጃው የሚገኘውን የሰው ኃይል በተከታታይ አጠናከሮ ማብቃት በቁልፍነት የሚከናወን ተግባር እንዲሆን ታቅዶ ስራው ከተጀመረ ሁለት ዓመት ሞልቶታል።

ለመልካም አስተዳደር መስፈን ዋና መሳሪያ የሆነውን የግልፅነትና ተጠያቂነት ሥርዓት በሁሉም መንግስት ተቋማት ለመዘርጋት በሚቀጥለው የዕቅድ ዘመን በፌዴራልና በክልል የመንግስት ተቋማት የዜጎች ቻርተርን በተሟላ ሁኔታ በመተግበር በተቋማት የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራር የበለጠ እንዲጎለብት የሚያስችሉ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡  

በሁለተኛው የልማት ዕቅድ በትግበራ ላይ ያሉት ሁሉም የሪፎርም ፕሮግራሞች በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበሩና ለውጡ ስር እንዲሰድና ተቋማዊ ባህል እንዲሆን ብርቱ ጥረት ይደረጋል፡፡

በመሆኑም በቀዳሚው ዕቅድ ወቅት ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን ከምንጩ ለማድረቅ ይቻል ዘንድ፤ በመሬትና በታክስ አስተዳዳር፣ በመንግሥት ፋይናንስና ግዥ አስተዳደር እንዲሁም በንግድ ውድድር ሥርዓት ላይ የተጀመሩት የሪፎርም ሥራዎች የበለጠ ጥልቀት እንዲያገኙና ዳር እንዲደርሱ ብሎም ተቋማዊ ባህል ሆነው እንዲዘልቁ የማድረጉ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡

ከታክስ አሰባሰብ ስርዓቱ ጋር በተያያዘም፣ ሥርዓቱን የማሻሻልና በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ የማድረግ ስራዎች ዕውን እንዲሆኑ በትጋት ይሰራል። በዚህ መሰረትም የግብር ከፋዩ ገቢና ንብረት በትክክል የሚታወቅበት እንዲሁም ህጋዊ ዕውቅና እና ጥበቃ የሚያገኝበት ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ተዘርግቶ ገቢራዊ ይሆናል፡፡

የጉምሩክ ሥነ ሥርዓቱንም ልማታዊውን ባለሃብት ከማደናቀፍ ይልቅ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያደርግ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ለማድረግ ታስቧል፡፡ የሽያጭ ማሽኖችን መጠቀምና ግብይት የማካሄድ ሥራ በሁሉም የንግድ ማህበረሰብ አካላት ተግባራዊ ይሆናል፡፡ በዚህ መረጃ ላይ በመመስረት ፍትሃዊ የታክስ አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ግብር ከፋዩን የማስተማርና በመጨረሻም በህዝቡ ተሳትፎ የታጀበ ፈጣን የህግ ማስከበር ሥራ በማከናወን በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ፈጣን ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ይደረጋል፡፡

ይህ ብቻ አይደለም። ከመሬት አቅርቦት ጋር በተያያዘም ሰፊ ዕቅድ ተይዟል። የከተማ መሬትና በመሬቱ ላይ ያለውን ንብረት በዘመናዊ መረጃ ሥርዓት የመመዝገብና የማወቅ፣ በመሬቱ ላይ ማን ምን መብት እንዳለው የተሟላና ወቅታዊ መረጃ የመያዝ፣ ሕጋዊ ዕውቅና እና ጥበቃ እንዲያገኝ የማድረጉ ተግባር በተሟላ ሁኔታ እውን እንዲሆን ይደረጋል፡፡

በመረጃው ላይ በመመርኮዝም መሬት ይበልጥ ልማታዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል የአቅርቦት ሥርዓት እንዲኖር ይደረጋል፡፡ መሬትን ጨምሮ የገቢና የንብረት መረጃና የንግድ እንቅስቃሴ መረጃ ሥርዓት ለመፍጠር ዕቅድ ተይዟል።

እርግጥ ይህ አሰራር በኢኮኖሚውና በፖለቲካው መስክ ግልፅነትና ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ የሚጫወተውን ሚና የላቀ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ መንግስት ሁሉን አቀፍ ርብርብ እንደሚያካሂድ በዕቅዱ ላይ ተመልክቷል፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ አንድ ዕውነታን መዘንጋት አይኖርብንም። እርሱም የህግ የበላይነት ጉዳይ ነው። በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ የህግ የበላይነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። እናም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በፍትህ አስተዳደር ስርዓቱ ውስጥ ያሉትን ከሙስና እና ከአድልኦ የፀዳ አሰራርን በማስወገድ ተግባሩን ውጤታማ ማድረግ ይገባል።

ታዲያ ይህ ተግባር እውን የሚሆነው በህዝቡ የነቃ ተሳተፎ መሆኑ አይታበይም። እርግጥም የህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ መሆኑ አጠያያቂ አይመስለኝም። የህዝቡ በመልካም አስተዳደር ላይ ተሳተፎ ማድረግ ለውጤታማነቱ ወሳኝ መሆኑ የሚታበይ አይደለም።

እናም ይህን ለውጤቱ መገኘት ቀናዒና ለተጠቃሚነቱ ታታሪ የሆነን ህዝብ ይዞ ከግብ የማይደርስ ልማት አይኖርም። ይህን ለሀገሩ ሰላም የሚተጋን ህዝብ ይዞ የውጭ ኃይሎችን ሴራና የተላላኪዎቻቸውን መልዕክት ሀገር ውስጥ ሳይገባ መንገድ ላይ ማስቀረት የማይቻልበት ምክንያት የለም። የሀገራችንን ሁለንተናዊ ችግሮች ከህዝቡ ጋር በመሆን ማስተካከል ይቻላል። ህዝብን በመልካም አስተዳደር ላይ ማሳተፍ በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመት ከተገኘው ውጤት ይበልጥ ማስመዝገብ የሚቻል ይመስለኛል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy