Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መድረክ አዲስ የሥራ አስፈፃሚ አመራር አባላትን መረጠ

0 449

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ፓርቲ አዲስ የሥራ አስፈፃሚ አመራር አባላትን መረጠ።

መድረክ ዛሬ የምርጫ ቦርድ ተወካዮች በተገኙበት ባካሄደው 13ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዶክተር ሚሊዮን ቱማቶን የግንባሩ ሊቀ መንበር አድርጎ መርጧል።

በተጨማሪም መምህር ጎይተኦም ፀጋዬ የድርጅት ጉዳይ ሓላፊ፣ የግንባሩ ሊቀ መንበር የነበሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የውጭ ግኑኝነት ሓላፊ፣ አቶ ሙላቱ ገመቹ የህዝብ ግንኙነት፣ ራሄል ዋለ የፋይናንስ አስተዳደር እና አቶ ካሕሳይ ዘገየ የግንባሩ ፀሓፊ ሆነው ተመርጠዋል።

ፓርቲው አዲስ የኦዲት ቁጥጥር አባላት የመረጠ ሲሆን፤ አቶ አለሙ ከይራ ሰብሳቢ፣ ክንፈ ገብረዮሃንስ ፀሓፊ እና አቶ ለገሰ ላንቃሞ አባል ሆነዋል።

አምስቱ የሥራ አስፈፃሚ አመራር አባላት የግንባሩ ምክትል ሊቃነ – መናብርት ሆነው ፓርቲውን ያገለግላሉ።

አዲሶቹ ተሿሚዎች በጠቅላላ ጉባኤ ፊት ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

የፓርቲው አዲሱ የመድረክ ሊቀ መንበር ዶክተር ሚሊዮን ቱማቶ ከምርጫው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ፓርቲው በአገሪቷ ህገ መንግስት መሰረት ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል።

ግንባሩ ልማትና ዴሞክራሲን ይበልጥ ለማጎልበት የድርሻውን እንደሚወጣ የገለፁት ዶክተር ሚሊዮን “ከጠላትነት የፀዳ ተቃውሞ ለማካሄድ እንተጋለን” ብለዋል።

የድርጅት ጉዳይ ሓላፊና ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር በመሆን የተመረጡት መምህር ጎይተኦም ፀጋይ በበኩላቸው  ፓርቲው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

ግንባሩ አሁን እየተካሄደ ወዳለው የኢህአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርድር እንደማይመለስ ያረጋገጡት መምህር ጎይተኦም ፓርቲያቸው ከገዢው ፓርቲ ጋር የሁለትዮሽ ድርድር ለማድረግ እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ግንባሩ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ባለፈው ዓመት የሥራ አፈፃፀም እና የኦዲት ሪፖርቶች ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።

የፋይናንስ ችግር እና የተግባር አመራር ድክመት የፓርቲው ቁልፍ ችግሮች እንደነበሩ በሪፖርቱ ተገልጿል።

ግንባሩ የኢትዮጵያ ማህበረ ዴሞክራሲ የደቡብ ህብረት አንድነት ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ ንዴሞክራሲን ንሉኣላዊነትን ፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባል ፓርቲዎችን ያቀፈ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy