መንግስት መረጃና ማስረጃዎችን መሰረት በማድረግ የህዝብና የመንግስትን ሀብትና ንብረት የመዘበሩ አካላትን ያለርህራሄ ለፍርድ ማቅረቡን እንደሚቀጥል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጸህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ጽህፈት ቤቱ የመንግስትን አቋም በሚተነትነው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫው፣ መንግስት በአመቱ መጀመሪያ በህዝብ ተሳትፎና ባለቤትነት የሚካሄድ ሃገራዊ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ማወጁን አስታውሷል፡፡
በተሃድሶ እንቅስቃሴው ልማታዊነትን ከማረጋገጥ በተጓዳኝ የተጠያቂነት አሰራርን ይበልጥ ለማስፈን መንግስት እየሰራ ነው ብሏል መግለጫው፡፡
ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም የመንግስት ሃብትን ለግል ጥቅም በማዋል የተጠረጠሩ የመንግስት ባለስልጣናት ፣ ነጋዴዎችና ደላሎች ሰሞኑን በቁጥጥር ስር መዋላቸውም የዚህ አገራዊ እንቅስቃሴ አካል እንደሆነ ገልጿል፡፡
ይህ እርምጃ ያለ አንዳች – ርህራሄ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያለው መግለጫው ፣የተሃድሶው ባለቤትነትና ተዋናይ በመሆን መረጃና ማስረጃ በመስጠትና በመጠቆም የጐላ ድጋፍ እንዲያደርጉ ዜጐችም መንግስት ምስጋናውን አቅርቧል፡፡