Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምን አለኝ ሀገሬ

0 281

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምን አለኝ ሀገሬ

                                                                                       ይነበብ ይግለጡ

የሀገርን ፍቅር፣ ታላቅነት፣ መተኪያ የለሽነት፣ እንዲሁም የሰውኛ መብትና ክብር የበለጠ አግዝፎ ለመረዳት የሚቻለው በሰው ሀገር ተሰደው በሚኖሩበት ወቅት ነው፡፡ ስደት አስከፊና የመከራ ሕይወት ነው፡፡ ስደት ሁለተኛ ዜጋ ሁነው የሚታዩበት፤ በሀገር ሁነው የነበረው ክብርና ኩራት የሚገፈፍበት፤ ሰብአዊ መብት የሚጣስበት፤ የጉልበት ብዝበዛ የነገሰበት ከጥንቱ የባርነት ዘመን ያልተለየ ዘመናዊ ባርነት ነው፡፡ ስደት በአካልም ሆነ በመንፈስም ዝቅተኛነትንና ተገፊነትን የሚያስከትል፤ ሙሉ ነጻነትና ክብር የሌለበት ሕይወት ነው፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ ነው አርቲስቱ ምን አለኝ ሀገሬ ሲል ያዜመው፡፡  የገዘፈ እውነት ነው ምን አለኝ ሀገሬ፡፡

ኑሮ ቢደላም ባይደላም በሀገር ላይ በሙሉ ነጻነት ሰብአዊ መብት ተከብሮ መኖር ይቻላል፡፡ አብዛኛው ወደ ውጭ ሀገራት የሚደረገው ስደት የራሱ መነሻ ገፊ ምክንቶች አሉት፡፡ በአብዛኛው  ስራ ማጣት፣ በሀገሬ ሰርቼ አላገኝም የሚል ተሰፋ መቁረጥ፤ ከዚህም ባለፈ የትም ይሁን የት ሰርቼ አገኛለሁ፤ ያልፍልኛል የሚል ከኢኮኖሚ ፍላጎት ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በውጭ ሀገራት ሰርተው ለመኖር ለሚፈልጉ ዜጎች ቀድሞ በነበሩት ስርአቶችም ሆነ በአሁኑ መንግስት እንዲህ በስደት የሄዱ ዜጎች ጉዳይ የሚደርስባቸው ፈተናና መከራ የሀገርን ስምና ክብር የሚነካ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ትኩረት ያላገኘ ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሰውን እንደባሪያ ዘመኑ ግዜ በመሸጥ የተካኑ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በብዛት መቀፍቀፍና ይሄንኑም ስራ የመደበኛ ሕይወታቸው አካል አድርገው ከዜጎች ከፍተኛ ገንዘብ እየገፈፉ ወደተለያዩ ሀገራት በስውር ለአደጋ በሚጋለጡበት መልኩ ሲልኩ ኖራዋል፡፡

የሀገርን ድንበር በመጣስ ዜጎችን ወደሌላ ሀገር በሕገወጥ መንገድ በማስገባት የሌላ ሀገርን ድንበር ጥሰው እንዲገቡ በማድረግ በዚህ አጋጣሚ ሕይወታቸው አደጋ ላይ የወደቀ፤ በአውሬ የተበሉ፣ በባሕር ሰምጠው የቀሩ፣ በነጣቂ ሽፍቶችም የተገደሉ ዜጎችን ለመቁጠር ያስቸግራል፡፡

ዜጎቻችን በብዙ አጎራባች ድንበሮች ወጥተዋል፡፡ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ የመን፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ወደላይ ግብጽ፣ ሊቢያ ምን የሌሉበት አለ፡፡ ከሊቢያ ወደኢጣሊያ ወደብ ላምባዱሳ ለመድረስ በሚደረገው የተጨናነቀ የአሮጌ ጀልባዎች ጉዞ በአብዛኛው በባሕር አደጋ ሰምጠው ከሞቱት የአፍሪካ ስደተኞች ውስጥ የእኛም ይገኙበታል፡፡ ከጅቡቲ ወደ የመን፣ ከሶማሊያ ወደ የመንና ወደ ተለያዩ የአረብ ሀገራት በባሕር በሚደረገው አሰቃቂ ጉዞ በርካታ ዜጎቻችን ሕይወታቸው አልፎአል፡፡

አንዳንዴ ይሄን ያህል ሕዝብ እንደማእበል በየማእዘናቱ የውጭ ሀገር ስራ ፍለጋ በሚል ድንበር አልፎ ሲወጣ ለመከላከል ያልተቻለው ለምንድነው? የሚል ጥያቄም ያጭራል፡፡ ግድ የለም በወቅቱ በዚህ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ስላልተሰራ ብቻ ነው በሚል እንውሰደው፡፡ ችግሩ እየገዘፈ ከመጠን በላይ ትኩረት እየሳበ የመጣው ዜጎቻችን በሄዱበት ሀገር የሚፈጸምባቸው ኢሰብአዊ ድርጊት፤ ድብደባ፤ ግርፋት፤ ሰቆቃ፤ ከፎቅ ላይ እየተወረወሩ እንዲሞቱ መደረጉ፤ በጥይት መገደላቸው ወዘተ እየከፋ በመሄዱ ነው፡፡ በዚህ ዘግናኝ ድርጊት  ሕዝብ ተንሰቅስቆ አለቀሰ፡፡ አሁንም ምን አለኝ ሀገሬ የሚያስብለው በዚህና በሌሎችም ተደራራቢ ምክንያቶች ነው፡፡

ድሕነታችንን ለመቅረፍ መንግስትና ሕዝብ የመረረ ትግል በማድረግ ታላላቅ ሀገራዊ ተስፋ ያስጨበጡ የልማትና የእድገት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ድሕነት አዋራጅ፣ አንገት አስደፊና ሰብአዊ ክብርን የሚነካ ነው፡፡ ዜጎች ከመሰደድ ይልቅ ትልቅ ትግል ማድረግ የሚገባቸው ሌት ተቀን ሰርተው ሀገራቸውን ከድህነት ማላቀቅ ነው፡፡ ሌሎች ሀገራትና ሕዝባቸውም መራራ ትግል አድርገው ነው ዝቅ ብለው ሰርተው ተርበውም ሆነ ተጠምተው የነገን ታላቅ ተስፋ ሰንቀው ሀገራቸውን ለታላቅነት ያበቁት፤ ከድህነትም የወጡት፡፡

እኛም በብዙ መስፈርት ለምለም ተፈጥሮ ያዳላት፣ የተለያየ ለሰው ልጅ ተስማሚና አመቺ የተፈጥሮ የአየር ንብረት ያላት፣ በጋ ከክረምት የማይነጥፉ ወንዞች፣ ምንጮችና ኃይቆች ያሏት፤ ሰርተን፣ ለፍተን ልናለማት፣ ልናሳድጋት፣ ልንለውጣት የምንችል ታላቅ ሀገር ባለቤቶች ነን፡፡ በስደት ሀገር ጥሎ ከመሄድ፣ ውርደትን በፈቃደኝነት ከመቀበል፣ በሰው ሀገር ጉልበታችንን እየሸጥን በባርነት ከመገዛት፣ በሀገራችን ሰርተን ማደግ መለወጥ እንችላለን፤ ሀገራችን ስታድግ ገቢያችን ኢኮኖሚያችን ያድጋል፤ ሕይወታችን ይለወጣል ብለን ማሰብ መቻል ይጠበቅብናል፡፡

በስደት ሕይወት ውስጥ በሰው ሀገርና መሬት  ስለሰብአዊ መብትና ከብር ማውራትም ሆነ መነጋገር አይቻልም፡፡ ያውም በሕገወጥ መንገድ ተገብቶ ምንም አይነት የሰውኛ መብት መከበር ጉዳይ ሊነሳ አይችልም፡፡ በስደተኞች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃና ግፍ አሁንም መልሰን ምን አለኝ ሀገሬ እንድንል የሚያስገድደን፡፡

ወደውጭ ሀገር ወጥቶ ለመሰራት የሚፈልጉ ዜጎች ሕጋዊ ሁነው፣ መንግስት አውቆት፣ ተመዝግበው ለስራ ቢሄዱ ምንም አይነት ግፍና በደል አይፈጸምባቸውም፡፡ ጉዳያቸውን የሚከታተለው፣ የዜጎቹን መብት የሚያስጠብቀው፣ በሚደርስና በሚፈጸም በደል ለዜጎቹ ጥብቅና ቆሞ የሚከራከረው መንግስት ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህ ነው በሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ስውር ድርጊት ተገፋፍቶ መሰደድ ሰፊ ችግሮችን ስለሚያስከትል ሕጋዊ ሁኖ መውጣት ከተለያዩ አደጋዎች ዜጎችን መጠበቅና መከላከል የሚያስችል ሕጋዊ ዋስትና ያለው መሆኑ የሚገለጸው፡፡

ዛሬ በሀገራችን ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን ሕብረተሰቡ በተለያዩ ክልሎች እየጋለጠና የልጆቹን ሕይወት እየታደገ ይገኛል፡፡ ይሄ ተግባር በስፋትና በጥልቀት መቀጠል ይገባዋል፡፡ ስለሚያስከትለው ሰፊ አደጋ ለሕብረተሰቡ ሰፊ ግንዛቤ የሚፈጥሩ መድረኮችን በማዘጋጀት ውይይቶች ማካሄድ ተገቢ ነው፡፡ ውይይቱ በህሕዝባዊ ድርጅቶች፣ በመንግስት ተቋማት እና በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥም መቀጠል አለበት፡፡ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች አማካይነት በሕገወጥ ስደትና በሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ላይ ሰፊ የማጋላጥ ስራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

በደቡብ ክልል የሀገር ሽማግሌዎችን የእድር ዳኞችን የማሕበረሰቡን ተወካዮች በማስተባበር ሕገወጥ የሰዎችን ዝውውር ለመከላከል ሕዝቡን እንዲያስተምሩ ለማድረግ ተችሎአል፡፡ በትምህሕርት ቤቶች በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ክበባትን በማቋቋም ችግሩ በሰዎች ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳትና መወሰድ ስላለበት ጥንቃቄ ለተማሪዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ፓስፖርት ለማውጣት ወደኢምግሬሽን ለሚሄዱ ዜጎች ስለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አስከፊነት በአንጻሩም በሕጋዊ መንገድ መስራት የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራበት ይገኛል።

በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በኮሌጆችና በዩኒቨርሲቲዎች፣ ቀበሌዎች፣ በሕዝባዊ ማሕበራት፣ በእድሮች ወዘተ ሰፊ ስራ መሰራት ይጠበቅብናል፡፡ በዚህ መልኩ ሕብረተሰቡን ሰፊ ግንዛቤ በማስጨበጥ ሕገወጥ ስደትንና ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን መከላከልና መግታት፤ ለሕግ ተጠያቂነትም ማቅረብ ይቻላል፡፡

ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ክቡር የሆነውን ዜጋ ስግብግብ ለሆነውና መቼም በቃኝን ለማያውቀው የገንዘብ ፍላጎታቸው ሲሉ እንደ ባሪያ ንግድ ዘመን ሰውን እየለወጡ ለወሲብ ባርያነትም እህቶቻችንን እየሸጡ፤ ለአደጋም አሳልፈው በመስጠት ሕይወታቸው እንዲቀጠፍ እያደረጉ እነሱ ተንደላቀው የሚኖሩበት ዘመን ከእንግዲህ ያበቃና የተከተተ መሆኑን ሊያውቁት ይገባል፡፡

ዜጎች ወደሚፈልጉት ሀገር በሕጋዊነት ሄደው መንግስት አውቆት መብትና ክብራቸው ተጠብቆ የትም መስራት ይችላሉ፡፡ መስራት እስከወሰኑ ድረስ በመንግስት እውቅና አግኝቶ መብቶቻቸውና ክብራቸው ተጠብቆ ሊሰሩ የሚችሉበት ሕጋዊ አሰራር ተዘርግቶአል፡፡ አዲሱ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ይህንኑ ውጭ ሀገር ሄደው ለመስራት የሚፈልጉ ዜጎችን መብትና ነጻነት የሚያስከብር ነው፡፡ ዜጎች አዋጁን ከሚገኝበት እየገዙ ቢያነቡት ስለጉዳዩ ያላቸውን ግንዛቤ የበለጠ ያዳብሩበታል፡፡

በአሁኑ ሰአት ከሳኡዲ ተመላሾች በብዛት ወደ ሀገራቸው እየገቡ ይገኛሉ፤ እሰየው ነው፡፡ ስንማጸን የቆየነውም የምታኮራ ሀገርና የሚያኮራ ወገን አላችሁ፤ በሰው ሀገር የሚፈጸምባችሁ ግፍና በደል እንኳን እናንተን የእኛንም ሕሊና አድምቶታል፤ ሰላምና እረፍትም ነስቶታል፡፡ ወደሀገራችሁ፣ ወደወገናችሁ ተመለሱ፤ ከውርደት የከፋ ነገር የለምና ይብቃ፤ ምን አለኝ ሀገሬ ምን አለኝ ወገኔ ብላችሁ ወደቤታችሁ ተመለሱ ነበር መንግስትም ሕዝብም ሲሉ የነበረው፡፡

ዛሬ ላይ በብዛት መመለሳቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ በሀገር ላይ እንደ አቅማችን በሙሉ ነጻነት አንገታችንን ቀና አድርገን ደረታችንን ነፍተን መኖር እንችላለን፡፡ ሳንሳቀቅ አዩኝ አላዩኝ ሳንል ተያዝኩ አልተያዝኩ ሳንል በሀገራችን መሬት በነጻነት እየተንጎማለልን የመኖር መብታችን የተከበረ ነው የሚለውን አስተሳሰብ ዜጎች ማሳደግ ይገባቸዋል፡፡

ከስደት ተመላሾች ከመንግስት ብዙ ሊጠብቁ አይገባም፡፡ ከሌላው ዜጋ የተለየ የሚደረግላቸው ነገር የለም፡፡ ትልቁ ነገር በአላቸው አቅምም ሆነ ተደራጅተው ስራ በመፍጠር ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁልግዜም የመንግስት ድጋፍ ከጎናቸው የመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡

መንግስት በሕገወጥ መንገድ ከሀገር ወጥተው የነበሩ ዜጎችን ቦታው ድረስ ሄዶ ቪዛ ሰጥቶ ችግርና ፈተና ውስጥ እንዳይወድቁ፤ በሰላም ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ያደረገው ርብርብ የሚያኮራ ነው፡፡ ማንም የሌላ ሀገር መንግስት ዜጎቹን በሰላም ከሳኡዲ አረቢያ ለማውጣት የሰራ የለም፡፡ እንደገናም የተሰጠው የግዜ ገደብ እንዲራዘም ጥያቄ በማቅረብ ይሁንታን አግኝቶ ከዛም ወዲህ በርካታ ዜጎች እየተመዘገቡ በመምጣት ላይ ናቸው፡፡

አሁንም ከስደት ተመላሽ ዜጎች ከመንግስት ብዙ ነገር ተስፋ አድርገው ሊጠብቁ አይገባም፡፡ ይልቁንም ያፈሩትን ገንዘብ 20 እና 30 በመሆን አቀናጅተው አክሲዮን በመፍጠር በተለያዩ ሰፊ የስራ መስኮች መርጠው መሰማራት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ ጥሪታቸውንም ለበለጠ ምርታማና አትራፊ ስራ ላይ ሊያውሉት ይችላሉ፡፡ ከራሳቸውም አልፈው ለሌሎች ዜጎች የስራ መስክ ሊፈጥሩ የሚችሉበት እድልም አላቸው፡፡ መንግስት ይህን በመሰለ አበረታች ተነሳሽነት ውስጥ ለሌሎች ዜጎች እንደሚያደርገው ሁሉ ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡

ስደትን መከላከል እንጂ ልናበረታታው አይገባም፡፡ በሰው ሀገር የስራን ክብደት ያዩት ዜጎቻችን የዛን ያህል በሀገራችን ላይ ብንሰራ ሙሉ በሙሉ ሕይወታችንን እንለውጣለን ብበሚል ብርቱ መንፈስበ  በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባቸዋል፡፡ ጠንክሮ መስራት ራስን ቤተሰብን ሀገርንም ይለውጣል፡፡

ሳኡዲ አረቢያ የቀንደኛ የዋሀቢ እስላማዊ አክራሪ እምነት ተከታዮች ዋነኛ ሀገር ናት፡፡ የእኛዎቹም የዋሀቢ አክራሪዎች ቀደም ባሉት አመታት አትዮጵያን በዋሀቢ እምነት እናጥለቀልቃለን በማለት ሲዲ እያስቀረጹ የአሸባሪዎችን ወታደራዊ ልምምድና የጥፋት ስምሪት ወደኢትዮጵያ በመላክ በአዲስ አበባና በክልሎች ሲያሰራጩ የነበረው ከሳኡዲ አረቢያ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው የዋሀቢ ቁንጮ የሆነው ኢማም መዋቅሩን ለማስፋፋት ሴት ከወንድ መልምሎ የአረቦችን ገንዘብ በመሰብሰብ ሁከትና አመጽ በሀገራችን ለማስፋፋት ሲሰራና ሲያሰራጭ የነበረው ሳኡዲ አረቢያ ሁኖ ነበር፡፡ ከመስጊዱ ሁከትና ብጥብጥ ጀርባ የእነዚሁ ኃይሎች እጅ እንደነበረ መንግስት ያውቃል፡፡ ተጨባጭ መረጃዎችም አሉት፡፡ በስደት ተመላሾች ስም ሌላ ጥፋት ውስጥ እንዳንገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ግድ ነው፡፡ (በዚህና በተመላሾች ስም ኢትዮጵያዊነትን በመጠቀም ሰርገው ሊገቡ የሚችሉ ሀይሎች ሊኖሩ ስለመቻላቸው፣ ሊወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄና ሌሎች ርእሰ-ጉዳዮችን በተመለከተ በሌላ ፅሁፍ እንመለስበታለን፡፡)

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy