Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስደት ይቁም

0 809

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስደት ይቁም

                                             ይነበብ ይግለጡ

የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ ያለው ትልቁ ጸጋ ሀገር ነው፡፡ ሀገር በእናትም በአባትም ትመሰላለች። የሀገር ፍቅር፤ የወገን ፍቅር የምንለው የተለያዩ ተፈጥሮዎችዋን፣ ሕዝብዋን፣ ባህሏን፣ ቋንቃዋን፣ እምነቶችዋን፣ የመልክአምድር አቀማመጧን ወዘተ ከማፍቀር፣ ከመውደድ፣  በውስጣችን ስር ሰዶ የኖረውን፣ የሚንቀለቀለውን ሀገራዊ ፍቅር ከመግለጽም ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው፡፡

ሀገርም ሆነ ወገን በምንም መልኩ መተኪያ የላቸውም፡፡ የሰው ሀገር የራስ ሀገር ሊሆን ከቶም አይችልም፡፡ በራስ ሀገር አገኘንም አጣንም፤ ጠገብንም ተራብንም፤ ደላንም አልደላንም ሙሉ ነጻነታችን የሰውኛ ክብራችንና መብታችን የተጠበቀ ነው፡፡ በራስ ሀገር አፍጣጭና ገላማጭ፤ አሳቃቂ የለብንም፡፡ ሀገር ለቀህ ውጣ የሚል አይኖርብንም፡፡ በራስ ሀገር ከሰማይዋ ስር በየትኛውም አካባቢ የመስራት፣ የመኖር፣ የመንቀሳቀስ፣ ሰርተን የማግኘት፣ ሀብት የማፍራት መብት አለን፡፡ ሀገሬ!! ፍቅሬ!! ክብሬ!! እንዲሉ፡፡

በሀገራችን የቱንም አይነት ችግር ይኑር ወልደን ከብደን ትውልድ ተክተን በአቅማችን እየሰራን የመኖር ያለአፍጣጭ ያለገልማጭ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት አለን፡፡ ሀገር ፍቅር ነች፡፡ ሀገር ክብርና ነጻነት ነች፡፡ ሀገር ለፍቅርዋ መተኪያ የሌላት የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ አንድ ግዜ ብቻ የሚፈጠርባት ወደር የማይገኝላት ነች፡፡ የእኛ ሀገር ኢትዮጵያ ደግሞ እናትነትዋ ከሁሉም ታላቅ ነው፡፡

ዛሬ በያዝነው መንገድና ጎዳና በብዙ መልኩ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ነን፡፡ ከድህነትና ከኃላቀርነት ጋር የተያያዝነውን ትግል በአሸናፊነት ለመወጣት ረዥም ርቀት ተጉዘናል፤ ብዙም ይቀረናል፡፡ ኢትዮጵያ አለም በመሰከረላት ሁኔታ በአለም ፈጣን ኢኮኖሚ ውስጥ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡ የአፍሪካ የኢንዱሰትሪ ማእከል ለመሆን በማቀድ ታላላቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባች ነች፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ የነግቤ ግድብ፤ ቀድሞ ያልነበረ ነው። ቀላል የከተማ ባቡርና የረዥም ርቀት ተጉዋዥ ባቡር፤ ድንቅና አለም ደጋግሞ የመሰከረለት ዛሬም እየመሰከረለት ያለ አየር መንገድ ባለቤቶችም ነን፡፡

ኢትዮጵያ የቀድሞ ስሟን በተግባር ቀይራ ዛሬም ከድርቅና ከድህነት ጋር እየታገለች ግስጋሴዋን በአሸናፊነት ወደፊት እየቀጠለች ያለች ሀገር ነች፡፡ አምና ድርቅ ቢገጥመን፤ ያውም በሀምሳ አመታት ታሪክ ውስጥ እጅግ አደገኛ ብለው ነጮቹ የፈረጁትን፣ የመከትነው እንደ ሀገር በራሳችን አቅም ነው፡፡ የለጋሾች እርዳታ የተጠበቀውን ያህል ባልሆነበት ሁኔታ ውስጥም ለዜጎች ፈጥኖ መድረስ ተችሎአል፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ያስገኘውን አቅም በመጠቀም ችግሩን እየተቋቋምነው እንገኛለን፡፡

ይህ ሁሉ ተግቶ በመስራት የተገኘ ትሩፋት ነው፡፡ ከመሰደድ፣ ጉልበትን ለባእድ ሀገር ከመሸጥ፣ በሀገራችን ሰርተን ለሀገራችን ደክመን፣ ለፍተን ይህችን ለምለም ሀገር ታላቅ፣ ኃያልና ገናና ማድረግ እንችላለን፤ እየሆነችም ነው፡፡

ማንም እንደሚያምነው፤ በስደት ውስጥ ክብር የለም፡፡ በስደት ውስጥ ሰብአዊ ክብርም ሆነ መብት የለም፡፡ ስደት ከባርነት ሕይወት የተሻለ ሆኖ አያውቅም፡፡ ስደት ታላቁ ሰብአዊ ክብር የሚዋረድበት ነው፡፡ በስደት ተከብሮ መኖር ሕልም ነው፡፡ መከበር፣ በነጻነት መኖር ያለው፣ ሚኖረውም በሀገር ነው፡፡

በስደት ውስጥ የከፋ ውርደት ከሰውነት ክብር ይልቅ እንደ እንስሳ የመቆጠር፣ የመደብደብ፣ የመገረፍ፣ በሴትነትም የመደፈር ከሰብአዊ ክብርና ከሴትነትም በዘለለ መጫወቻ መሆንም አለ፡፡ ሆኖም ታይቷል፡፡ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እህቶቻችንን ለወሲብ ንግድ እንደ ሸቀጥ ሲሸጡዋቸው፣ ሲለውጡአቸው፣ በወሲብ ንግድ በባርነት በማያውቁት ቦታ ሲሸጡ ሰምተናል፤ አይተናልም፡፡ እንደ ሀገር፣ እንደ ሕዝብ ከዚህ በላይ ሞት የለም፡፡

አብዛኛው ስደተኛ የኢኮኖሚ ስደተኛ ነው፡፡ በሀገሬ በቂ ስራ የለም፤ የትም ሄጄ ሰርቼ ሕይወቴን ልለውጥ ከሚል መነሻ ያገኘውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ሕይወቱንም ለከፋ አደጋ አጋልጦ በሕገወጥ የሰዎች  አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በድብቅ እየተላከ  በአውሬም ተበልቶ፣ በባሕርም ሰምጦ፣ ሞቶ የቀረውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ከዚህ ላየ አንድ ማሰብ ያልቻልነው ትልቅ ጉዳይ እንዳለ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ እሱም ሀገራችንን ማልማት፣ መለወጥ፣ ማሳደግ የምንችለው እኛው እራሳችን ብቻ መሆናችን ነው፡፡ የሀገሪትዋ ዜጎች ተግተው ፈግተው ሀገራቸውን ለመለወጥ ካልሰሩ የውጭ ሰው መጥቶ   ሀገራችንን ሊያለማ ሊያሳድግ አይችልም፡፡ ባለቤቶቹ ባለጉዳዮቹ እኛና እኛ ብቻ ነን፡፡

ለንደንም ሆነች ኒውዮርክ፣ ሮማም ሆነች ቤጂንግ በአንድ ጀምበር አልለሙም፤ አላደጉም፡፡ ለዘመናት የየራሳቸው ዜጎች ከድሕነት ለመውጣት ታላቅ መስዋእትነት ከፍለው በብዙ ችግርና መስዋእትነት ውስጥ አልፈው ለታላቅነት ያበቁአቸው ሀገሮች ናቸው፡፡ እነቻይና  ለታላቅነት የበቁት የሚበላ፣ የሚላስ፣ የሚቀመስ ባልነበረበት ሰአት፤ ያገኙአትን ቀምሰው በመዋልና ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው በመስራት ነው ዛሬ ማእዳቸው ተትረፍርፎ፣ ገበታቸው ሞልቶ የሚታየው።

አመትባል፣ ቅዳሜ፣ እሁድ፣ ቀን ነው ማታ ሳይሉ ሰርተው ነው አለምንም እስከማስደመም የደረሱት፡፡ ሀገርን የሚለውጠው ስራ እንጂ መሰደድ አይደለም፡፡ ሁሉም ዜጋ ስደትን ሊጸየፍ ይገባል፡፡ ውርደትን፣ የክብር መነካትን ከጠዋቱም ከፍጥረታችን ጀምሮ የምንቀበል ህዝብ አይደለንም፡፡ ከነድሕነታችን ክብራችንን ስማችንን ወዳድ፣ የተለየ የሀገር ፍቅር ያለን፣ ኩሩና ታላቅ ሕዝብ ነን፡፡ በታሪካችን ውስጥ ስደትን አናውቀውም ነበር፡፡

በተለያዩ የፖለቲካ ምክንያቶች ይሰደዱ የነበሩት ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ዛሬ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ስደትን አፍቃሪና አንጋሽ፤ ስደትን እንደመንግስተ ሰማያት የሚቆጥር፣ ከሀገሩ ወጥቶ ለመሰደድ እንቅልፍ አጥቶ የሚያድር ሰው የበዛበት አሳፋሪ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ለምን ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ምክንያቶች ሊደረደሩ ይችላሉ፡፡ በሀገር እየኖሩ በሀገር ላይ እየሰሩ ሀገርን መለወጥ ማሳደግ ከምንም በላይ ታላቅ ተግባር መሆኑን ሁሉም ሰው ሊረዳው ይገባል፡፡ የሰው ሀገር የሰው እንጂ በምንም ተአምር የእኛ ሀገር ሊሆን አይችልም፡፡

በጉልበት ስራና በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው ሕይወታቸውን ለመለወጥ ከሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን በላይም እጅግ አስገራሚ ስደት አለ፡፡ ይህችው ድሀ ሀገር ያላትን አካፍላ ያስተማረቻቸው ለከፍተኛ የአካዳሚክ ማእረግ የበቁ ምሁራኖቻችንም ከድሮ እስከ ዘንድሮ የሀገራቸውን ድሕነት ጠልተው ሰርተን እንለውጣት፣ እናሳድጋት ማለት ተስኖአቸው፣ በእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ምክንያት በብዛት ተሰደው፣ በአውሮፓ ዜግነት አግኝተው  እውቀታቸውን ሸጠው ከፍተኛ ተከፋይ ሁነው የተንደላቀቀ ሕይወት ይኖራሉ፡፡ ያሳዝናል።

በጀርመን፣ በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ በሌሎችም ሀገራት ስመጥር የሆኑ፣ በሙያቸው የተከበሩ፣ አንቱ የተባሉ ሳይንቲስቶች፣ መሐንዲሶች፣ ኬሚስቶች፣ ኢንጂነሮች፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የጠፈር ተመራማሪዎች፣ የልዩ ሙያ ጠበብቶች ስንትና ስንት የተደነቁ፣ የተከበሩ፣ የበቁ፣ የረቀቁ ኢትዮጵያውያን ምሑራን ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ሀገሬን፣ ወገኔን በሀገሬ ኖሬ ልለውጥ፣ ላሳድግ አላሉም፡፡ ፖለቲካዊ ምክንያት ማንዘባዘቡ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሀገርን በሙያ ማገልገልና ፖለቲካ ምንም አያገናኛቸውም፡፡ መንግስት ይመጣል፤ መንግስት ይሄዳል፡፡ ሀገር ግን አታልፍም፡፡ ትውልድም እንደ ዥረት ነው፤ ይቀጥላል፡፡ ቆም ብለን ማሰብ  ያቃተን ይሄንን ነው፡፡

በድሕነት ያስተማረችና ያሳደገች፣ ለትልቅነት ያበቃች ኢትዮጵያ በልጆችዋ እውቀት የሚያድገውና የሚከብረው ሌላ ሀገር፣ ሌላ ሕዝብ ነው፡፡ ይሄ ለወደፊቱም ትልቅ ውይይትና መፍትሄ የሚፈልግ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ቅጠል ሸጣ፣ የቀን ስራ እየሰራች፣ ገበሬ አርብቶ አደር ሁኖ፣ አነስተኛ የመንግሰት ሰራተኛ ሁኖ ያስተማረን፣ ያሳደገን ሀገርና ቤተሰብ እውቀት ካገኙ በኋላ ትንሽ ላገልግል፣ ልስራ፣ ልለውጥ ሳይሉ መሰደድ፣ ለሰው ሀገር ጉልበትና እውቀትን እየሸጡ የራስን ድሎትና ምቾት ብቻ በመፈለግ መኖር ከራስ ወዳድነት በላይ የሀገርና የወገን ፍቅር መገለጫ ከቶውንም ሊሆን አይችልም፡፡ አባቶቻችን እናቶቻችን እንደዚህ አልነበሩም፡፡

ይህ ራስን ብቻ በጽኑ ፍቅር የመውደድ መገለጫ ነው፡፡ ቻይናን ቻይና፣ አሜሪካንን አሜሪካ፣ እንግሊዝን እንግለዝ አድርገው ለታላቅነት ያበቁአቸው የራሳቸው ዜጎችና ሕዝቦች ናቸው፡፡ የሌላው ሀገር ስደተኛ በጉልበትና በእውቀቱም ጭምር አግዞአቸዋል፡፡ ከአፍሪካ በባርነት የሄዱ ጥቁሮች በጉልበት ስራው ታላቅና ተኪ የሌለው አስተዋጽኦ አድርገው እነዚህን ሀገራት ለውጠዋቸዋል፡፡

የእኛ ነገር በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ያስለቅሳልም፡፡ ሀገርን መለወጥ፣ ማሳደግ፣ እውቀትን ለወገን አካፍሎ ተተኪውን ትውልድ እያስተማሩ ለትልቅነት ማብቃት የሚቻለው እውቀት ያለው በእውቀቱ፣ የሌለው በጉልበቱ ተሰልፎ ሀገሩን ተረባርቦ ማልመትና ማሳደግ ሲችል ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሀገሬ ሀገሬ ቢባል ትርጉም አይኖረውም፡፡ ስራን ሳይንቁ መስራት ገጠር ከተማ የሚባል ምርጫ ሳይኖር፣ ይሄ ስራ ለእኔ ይመጥናል፣ አይመጥንም የሚባል ዝባዝንኬ ውስጥ ሳይገባ በሀገር ላይ የትም ይሁን የትም ስራን በባለቤትነት ስሜት ቀን ከሌት መስራት ብቻ ነው ሀገርን ሊያሳድግ የሚችለው፡፡

እኛ ስራ መራጮች ነን፡፡ ስጋዊ ምቾት ፈላጊዎችም ነን፡፡ በዚህ ደግሞ ሀገርን ማሳደግ፣ መለወጥ፣ ወደተሻለ ምእራፍ ማሸጋገር ከቶውንም አይቻልም፡፡ መስራት፣ መስራት፣ መስራት፣ ቀን ከለሊት በአላት፣ ሰሞናት፣ ሕማማት ሳይባል መስራትና መስራት ብቻ ነው ሀገርን የሚያሳድገው፡፡ እኛ ጋ ስራን እንደአቅሙ ሰርቶ ከሚኖረው በላይ የማይሰራው፤ ስራ ቢገኝም ይሄን አልሰራም በሚል እንዲሁ ሲንገላወድ የሚውለው ይበዛል፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ እንደ አቅም ተሰርቶ፣ ውሎ የሚገባበት ስራ አይጠፋም። ዛሬ ብዙ አይነት ስራዎችና የስራ መስኮች አሉ፡፡ ትልቁ ችግር ስለስራ ያለን አመለካከት ገና አልተለወጠም፡፡ ስራ የለም በሚል ሲያማርር ቁጭ ብሎ ወግ ሲቀጭና ሲፈጭ የሚውለው ይበዛል፡፡

በግንባታው፣ በግብርናው፣ በአነስተኛና ጥቃቅኑ፣ በኮንስትራክሽኑ፣ በማአድኑ፣ በወተት ሀብቱ፣ በእንሰሳት እርባታና በአትክልት ዘርፉ፣ በደን ልማቱ፣ በመስኖ ስራው፣ በግድብ ስራው ወዘተ እጅግ ብዙ የሚሰራባቸው፣ የሚታደግባቸው፣ ራስን ከመቻል አልፎም ለቤተሰብ የሚተረፍባቸው የስራ መስኮች ሞልተው ተርፈዋል፡፡ አስተሳሰባችን መለወጥ አለበት፡፡ ሁሉንም ሰው ተሸከርካሪ ወንበርና ቢሮ አስቀምጦ የሚሰራ ስራ ብቻ አይደለም ሀገርን የሚያሳድገው፡፡

ሀገርን የሚያሳድግ ስራ ያለው መስክ ላይ ነው፡፡ በግንበታው፣ በኮንስትራክሽኑ፣ በኢንዱስትሪው፣ በፋብሪካው፣ በሆቴሉ ዘርፉ፣ በትራንስፖርቱ፣ በአርብቶ አደሩ፣ በአርሶ አደሩ፣ በመንገድ ስራው፣ በግድብ ግንባታው፣ በቤት ልማቱ  ወዘተ ወዘተ ያለው የስራ እድል ሰፊ ነው፡፡ ሁለም ቢሮ ቁጭ ተብሎ የሚሰራ ስራ ፈላጊ ከሆነ፤ ሌሎቹን ታላላቅ፣ ሀገርን የሚለውጡና የሚያሳድጉ ስራዎችን ማን ይስራቸው ብለንም እኮ መጠየቅ አለብን፡፡ የቢሮ ሰራተኞችን ብንመለከት የመስክ ስራዎችን የሚመሩበት የሚያቀናጁበት እቅድ የሚያወጡበት አስተባብረው የስምሪቱን ሂደት የሚቆጣጠሩበት  ዋና ራስ ሁነው አጠቃላዩን የሀገሪቱን የስራ ሂደት መልክ የሚያሲዙበት አሰራር ነው ያላቸው፡፡ ሌላውም ይህንኑ ነው መከተል ያለበት።

ስደትን መጠየፍ ይገባናል፡፡ በሀገራችን ሰርተን ማደግ ሰርተን መለወጥ እንችላለን፡፡ ዝቅ ብለን ሰርተን ነገ ቀና ብለን መራመድ፣ ኮርተን መኖር እንችላለን፡፡ በተፈጥሮ ሀብት፣ በማእድን፣ በአየር ንብረት፣ በውሀ ሀብት የታደለች ግን ደግሞ የበለጠ ሰርተን ልንለውጣት፣ ልናሳድጋት የሚገባን፣ የምታኮራ ሀገር አለችን ብለን ማሰብና ከመቸውም በላይ ሀገርን የሚለውጥ ስራ ለመስራት መዘጋጀት አለብን፡፡ አሁን የያዝነውን የልማትና የእድገት ጎዳና ጠብቀን፣ ተደማምጠን፣ ተከባብርን፣ ልዩነቶቻችንን አቻችለን፣ ለጋራ ሀገራችን መቆም ከቻልን አዋራጁን የዜጎቻችንን ስደት ያለምንም ጥርጥር እንገታዋለን፡፡

የእኛ መሰደድና መንከራተት፣ በየሰው ሀገር መዋረድ አብቅቶ ያደገችና የበለጸገች ሀገር ሲኖረን የሌላው አለም ሕዝብ እንጀራና ስራ ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ይሰደዳል፡፡ ይህን የምናይበት ግዜ ደግሞ ሩቅ አይሆንም፡፡

የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በሕገወጥ መንገድ ወደሀገሬ የገቡ ስደተኞች በ90 ቀናት ግዜ ውስጥ ሀገሬን ለቀው ይውጡልኝ ካለበት የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን የሚመራ ከፍተኛ የልኡካን ቡደን ልኮ፣ የሳኡዲ ባለስልጣናትን አነጋግሮ፣ ዜጎቹንም በያሉበት ሄዶ በማወያየት ወደሀገራችሁ በሰላም ግቡ፤ ሀገር ባፈራው፣ በሀገር አቅም ሰርታችሁ መኖር ትችላላችሁ፤ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ነው፡፡

በሳኡዲ አረቢያ የብዙ ሀገር ስደተኞች አሉ፡፡ የየትኛውም ሀገር ስደተኛ መንግስት ለዜጎቹ ተጨንቆ፣ ተጠቦ፣ ዜጎቹን ከዚያች ሀገር ጉዳት ሳይደርስባቸው ለማውጣት የሚችለውን ሁሉ በማድረግ የተረባረበ አንድም የለም፡፡ ይህም ሁኖ የሚታየውንና አለም የሚከታተለውን ገሀድ የወጣ ጥረትና ልፋት ጥላሸት ለመቀባት የሚንከላወሱ መርገምቶች አሉ፡፡ የዚህ መነሻ ደግሞ ጭፍን ጥላቻ ነው፤ ጥላቻ ሀገር አይገነባም፡፡ አያሳድግም፡፡ ለምንም ለማንም አይጠቅምም፡፡ በጥላቻ የለማ፣ ያደገ ሀገርም ሆነ ሕብረተሰብም በአለም የለም፡፡ በመሆኑም አይበጀንም፡፡

መንግሰት ሲሳሳት፣ ከመንገድ ሲወጣ፣ ኢፍትሀዊ ነገር ሲፈጽም መውቀስ፣ መተቸት፣ መንቀፍ፣ ከስህተቱ እንዲወጣ፣ እንዲታረም፣ የተሻለውን መንገድ፣ ለሁላችንም የሚበጀውን አቅጣጫ እንዲከተል የማድረግ ግዴታም የዜግነት ኃላፊነትም አለብን፡፡ ምክንያቱም በማሰረጃ ላይ የተመሰረተ ትክክለኛውን ሁኔታ ገላልጦ የሚያሳይና የመፍትሄ መስመሩንም የሚያመላክት ወቀሳና ትችት ለራሱ ለመንግስትም ለሕዝብም ይበጃልና ነው፡፡

ሀሰት፣ ውሸት፣ የፈጠራ ታሪክና ውንጀላ፣ ስሜታዊነትና ጥላቻ ለሀገር አይጠቅምም፡፡ በሳኡዲ አረቢያው የሕገወጥ ስደተኞች ከሀገሬ ይውጡልኝ ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግስት ያለውን አቅም ሁሉ ተጠቅሞ ዜጎቹን ከችግርና ከአደጋ ለመታደግ በሰፊው ተንቀሳቅሶአል፡፡ እዛው ሳኡዲ አረቢ በሚገኘው ኤምባሲያችን አማካኝነት ቀድሞ ከሀገር ሲወጡ ምንም ማስረጃ ላልነበራቸው ዜጎቻችን የዜግነት መለያ የሆነውን የኢትዮጵያ ፓስፖርት ሰጥቶአል፡፡ በአውሮፓላን ከፍለው መመለስ ላልቻሉት ዜጎች እስከተወሰነ ኪሎ ድረስ ያፈሩትን እቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገራቸው ይዘው እንዲገቡም አድርጎአል፡፡ የተወሰነ አቅም ላላቸው ደግሞ ግማሽ ከፍለው እንዲገቡ አድርጎአል፡፡ በዚሁ መሰረትም እስከአሁን 46ሺህ ያህል ዜጎቻችን በሰለም የሀገራቸውን መሬት ለመርገጥ በቅተዋል፡፡ የአዋጁ ቀን ሊጠናቀቅ ትንሽ ቀን ሲቀረው በብዛት መመዝገብ በመጀመራቸው 100ሺ ያህል ዜጎች ቪዛ አግኝተው ወደሀገራቸው ለመመለስ ተዘጋጅተው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ እዚህ እንደ ሳኡዲ አረቢያ ሰርተው ብዙ ብር ለማግኘት ባይችሉም በሀገራቸው በነጻነት ሰርተው በመንቀሳቀስ መኖር ይችላሉ፡፡ መንግስት ለማንኛውም ዜጋ የሚያደርገውን ድጋፍና እርዳታ ያደርጋልና ብር ማፈሱ ቀስ ብሎ ይደርሳል።

አዋጪ የስራ መንገድ የመቀየስ፣ በተናጠል ሳይሆን በኮኦፐሬቲቭ እየተደራጁ ትላልቅ ድርጅቶችን መክፈት፣ መስራት፣ ትርፋማ መሆን፣ መለወጥ የዜጎች የራሳቸው ኃላፊነት ነው የሚሆነው፡፡ ከሀገር ውጭ ሰርተው ከሚያገኙት ገንዘብ በላይም ሀገር ትበልጣለች፡፡ ገላማጭ፣ ከሳሽ፣ ሰብአዊ ክብራቸውን የሚያዋርድ፣ የሚያንገላታ፣ የሚያሳቅቅ፣ አንገት የሚያስደፋ፣ ተደብቆ፣ ተሸማቆ የሚያስኖር ምንም ነገር በሀገር የለም፤ አይኖርምም፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy