Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቀጣናውን የሚያስተሳስር የውሃ ድር

0 307

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቀጣናውን የሚያስተሳስር የውሃ ድር

                                                         ታዬ ከበደ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። ቀጣናውን የማስተሳሰር ግብን ያነገበ ጭምርም ነው። ይህ ግድብ ምስራቅ አፍሪካን በውሃ የሚያስተሳስር ድር ነው ሊባልም ይችላል።

የህዳሴው ግድብ በመገንባት ላይ የሚገኘው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ግድቡ ቀደምት የተመጽዎችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ – ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ የይቻላል መርህን በተግባር ማዋል ያስቻለ ብሎም ከራስ አልፎ በሚደረገው ሽያጭ የህዝቡን ውለታ በዕድገት የሚመልስ በመሆኑ ታሪካዊነቱን የጎላ ያደርገዋል፡፡ ግና የምናድገው ለብቻችን አይደለም።

እኛ ኢትዮጵያውያን አብሮ መኖርን፣ ማደግንና መበልጸግን ከማንም በላይ የምንቀበልና የማንነታችን መገለጫም ነው። ልክ እንደ ሌሎች “ለብቻችን” ብለን አናውቅም። እናም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታችን ትኩረትም ማንንም ለመጉዳት ያለመ እንዳልሆነ ማንኛውም አካል ሊያውቅ ይገባል፡፡ አብሮ መብላትና ተያይዞ ማደግ የቆየ ኢትዮጵያዊ እሴት መለያ ባህሪ እንደሆነም ጭምር፡፡

ሀገራችን በተፈጥሯዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ዓለም አቀፋዊው የእኩልነትና የፍትሃዊነት መርህን መሰረት ላደረገው የኢንቴቤው የስምምነት ማዕቀፍ ተግባራዊነት በግምባር ቀደምትነት የተሰለፈችውም ለዚሁ ነው፡፡ መላው ዜጎቿም ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬታማነት ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን እያበረከቱ የሚገኙት ደግሞ ግድቡ የጋራ ተጠቃሚነትን ሙሉ ለሙሉ የሚያረጋግጥ መሆኑን ጥንቅቀው ስለሚያውቁ ነው፡፡

ግድቡ ለእኛ የላቀ ፋይዳ ስላለው ትናንት የነበረው አቋማችን ዛሬም ሊንጋደድ አይችልም። አቋማችን የትናንቱ ነው። ግድቡ ሀገራችን የተያያዘችውን የፀረ- ድህነት ትግል ከግብ በማድረስ ለህዳሴው ጉዞ ስኬት የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከቱ አያጠያይቅም፡፡ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ የሀገራችንን የኤሌትሪክ ሽፋን የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ፤ ለዘመናት መብራት እንደ ገነት ለራቀው የገጠሩ ህዝባችን ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

ይህም ለከፍተኛው የደንና የመሬት መራቆት ችግር እንዲሁም ሊከሰት የሚችለውን የአየር መዛባትና የሚያስከትለውን የድርቅ አደጋ የሚያስቀር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሃይል አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለሚደርሰው የጤና ችግር እልባት ይሰጣል፤ መሳ ለመሳም ለህክምና የሚወጣውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ይህም ፋይዳውን ድርብ ድርብርብ ያደርገዋል፡፡

ግድቡ ከዚህም የላቀ ፋይዳ አለው፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ የኤሌትሪክ ሃይልን ለጎረቤት ሀገሮች መሸጥ ይቻላል። ይህም በድህነት ለሚሰቃየው ህዝባችን ህይወትና ኑሮ መሻሻል የሚረዳ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ይሆናል፡፡ እናም ከሽያጩ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ የሀገሪቱን ዕድገት በማፋጠን ለዜጎች ኑሮ መለወጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፡፡ በመሆኑም የግድቡ ግንባታ በድህነትና በኋላቀርነት የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ ስለሆነ የህልውናችን መሰረት መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ ሊዘነጋ የማይገባው ነገር ቢኖር፤ ሀገራችን ምንም እንኳን ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ የምትከተልና ውጤታማ መሆኗ የሚታወቅ ቢሆንም ቅሉ፤ ወደ ኢንዱስትሪው መር ኢኮኖሚ መሸጋገሯ የማይቀር ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የኤሌትሪክ ሃይልን የሚጠይቅ ነው፡፡

እናም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተስተዋለ ከሚታየው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ጋር ተያይዞ ለቀጣይነቱ የህዳሴው ግድብ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ የሚሰጠው ምላሽ ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡

ስለሆነም ወቅታዊውን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከማስቀጠል ባሻገር፤ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምናደርገው ጉዞ መፋጠን አስተዋጽኦው የላቀ ነው—ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ። ለዚህም ነው ግድቡ ለሀገራዊው የህዳሴ ጉዞ ስኬት ዕድገትን የማስቀጠልና ያለማስቀጠል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ሀገር የመቀጠልና ያለመቀጠል የህልውና ጉዳይ መሆኑ ተደጋግሞ የሚገለፀው፡፡

እንደሚታወቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይነቱ የዜጎችንና የሀገራችንን ዕድገት በማፋጠን ብቻ የተወሰነ አይደለም—የጎረቤቶቻችንን ተጠቃሚነት በማሳደግ የሰላማችን ዋስትናም ጭምር እንጂ፡፡

እናም ግድቡ ከከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ለሚሰቃዩት እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ለመሳሰሉ ጎረቤቶቻችን ለችግራቸው ምላሽ የሚሰጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩተን የሚያሳድግ፣ ግንኙነታችንንም የማጠናከር ሚናው በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የግድቡ ግንባታ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር ለአካባቢው ሠላምና መረጋጋት የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡

የዘመናት የድህነት ታሪካችንን ለመቀየርና ከተጫነን ድህነት ለመውጣት በምናደርገው ትግል ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የኢፌዴሪ መንግስት በግድቡ ግንባታ ስፍራ ላይ የመሰረት ድንጋይ ካኖረበት ጊዜ ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለ አንዳች ልዩነት ስኬታማነቱን ዕውን ለማድረግና በራሳችን ተነሳሽነት ማናቸውንም ጉዳዮች ለመከወን ቃል ገብተናል፡፡ በዚህም ሁሉም የሀገራችን ህዝብ የዘመናት ቁጭትና ብሔራዊ ሀብቱ የሆነውን የዓባይ ወንዝን የመጠቀም ምኞትና ፍላጎት በአዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ተደርጓል፡፡

በህዝቦች የማይነጥፈና ሙሉ ተሳትፎ የሚገነባው እንዲሁም የዜጎች ሀብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን ገንዘብና ተሳትፎ የሚገነባ ብቸኛው የዓለማችን ፕሮጀክት ለመሆን በቅቷል፡፡ ዜጎች ከዕለት ምግባቸው ቀንሰው የሚገነቡትና እንደ አይናቸው ብሌን የሚንከባከቡት ግድብ መሆኑም ታሪካዊነቱ የትየሌለ ነው፡፡

እርግጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በብሔራዊ መግባባት መንፈስ ግድቡን ካለአንዳች ልዩነት በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ለመገንባት ሲነሱ ተርፏቸው አይደለም— በድህነት አለንጋ መገረፉ ማብቃት እንዳለበት በማመናቸው እንጂ፡፡

አዎ! ለስኬታማነቱ ህዝባዊ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ ሲነሱም የማንንም ጉትጎታ ያለመሻታቸው ለድህነት ካላቸው ከፍተኛ ጥላቻ የመነጨ መሆኑም ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡ እናም ይህ አቋማችን መቼም አይቀየርም። አይለወጥም። የትናንቱም ሆነ የዛሬው ብሎም የነገም አቋማችን አንድ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዚህ ትውልድ ዋነኛ መገለጫ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ትውልድ ደግሞ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚያምን ነው። የትውልዱ ይህ አስተሳሰብ በመንግስታችን ፖሊሲም ላይ ዕውን እየሆነ ነው። የየትኛውንም ወገን ጥቅም ሳንነካ በጋራ ተጠቃሚነት ብሎት ሁሉም ወገኖች አሸናፊ የሚሆኑበትን መንገድ የሚከተል ነው። እናም ትውልዳችን ይህን ፍትሐዊና ትክክለኛ አቋሙን የሚቀይርበት አንዳችም ዓይነት ምክንያት የለም።

ይህ አቋምም ሀገራችን በእኩልነትና በፍትሃዊነት እንድታምንና የምታካሂዳቸውን ማናቸውንም ፕሮጀክቶች ከዚህ አኳያ እንድትቃኛቸው አድርጓል። ስለሆነም በዓባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብም ይህን ዕውነታ መሰረት አድርጎ የሚከናወን በመሆኑ፤ ይህ የሀገራችን አቋም መቼም ቢሆን የሚቀየር አይሆንም። ቀጣናውን የሚያስተሳስር የውሃ ድር መሆኑም መታወቅ አለበት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy