Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በሙስና የተጠረጠሩ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ ነጋዴዎችና ደላሎች ቁጥር 45 ደረሰ

0 559

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ደላሎችና ነጋዴዎች ቁጥር 45 ደርሷል።

በዛሬው እለት ከሰዓት በኋላ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የወንጀል ችሎት በጽህፈት ቤት የቀረቡ ተጠርጣሪዎች ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሶስት፣ ከስኳር ኮርፖሬሽን ሶስት እንዲሁም አንድ ባለሃብት ናቸው።

ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የቤቶች ልማት ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፀዳለ ማሞ፣ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ማስተባበሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ ሽመልስ አለማየሁ፣ የመሬት ዝግጅት እና መሰረተ ልማት ዲዛይን ረዳት ሃላፊ ወይዘሮ ሳባ መኮንን እንዲሁም የስራ ተቋራጭ ባለሃብት የሆኑት አቶ የማነ ግርማይ ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ከሰባት አመት በፊት በተከናወነ የመንገድ ፕሮጀክት ስራ ላይ ከአራተኛ ተጠርጣሪ አቶ የማነ ግርማይ ጋር በመመሳጠር፥ ውል ሳይደረግ በተደረገ የኮንክሪት ሙሌትና ሌሎች ስራዎች ፕሮጀክቱ ደረጃውን ሳይጠብቅ መከናወኑን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አብራርቷል።

በዚህም 39 ሚሊየን 727 ሺህ 693 ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ገልጿል።

ከስኳር ኮርፖሬሽን ደግሞ፥ የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ የቀድሞ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘነበ ይማም፣ የተንዳሆ ኤሌክትሪክ መሃንዲሶች ቡድን መሪ አቶ አስናቀ ምህረት እና የቀድሞ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የእቃ አቅርቦትና ፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ተድላ ናቸው።

አቶ ዘነበ ይማም በመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲሰሩ ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸውና የህንድ ኩባንያ ከሆነው ስታር ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር በመመሳጠር፥ ለእቃ ግዢ ከአሰራር ውጪ 1 ሚሊየን 164 ሺህ 465 የአሜሪካ ዶላር ክፍያ በመፈጸም ተመሳሳይ መጠን ያለው ብር ጉዳት በማድረስ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

የቀድሞው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የእቃ አቅርቦትና ፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ ተድላ ደግሞ በፋብሪካው በ2004 ዓ.ም ለቀረበው የአርማታ ብረቶችና ሲሚንቶ ከህንድ ኩባንያጋር በመመሳጠር ክፍያ ተቀንሶ በአይነት መመለስ ሲገባው ሳይመለስ በመቅረቱ ባደረሱት ጉዳት ተጠርጥረው መያዛቸውን ፖሊስ አስረድቷል።

በተጠርጣሪው ድርጊት ሳቢያም 31ሚሊየን 330 ሺህ ብር በህዝብና በመንግስት ሃብት ላይ ጉዳት ደርሷልም ነው ያለው ፖሊስ።

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ኤሌክትሪክ መሃንዲሶች ቡድን መሪ አቶ አስናቀ ምህረት፥ ከታዘዘው የኤሌክትሪክ ሃይል መጠን ያለው ጄኔሬተር አቅርቦት ውጪ በማቅረብ በፋብሪካው ላይ 221 ሺህ 375 ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

ፖሊስ ለተጨማሪ የምርመራ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ፖሊስ ያቀረበው የተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ አግባብ ባለመሆኑ ዋስትና ሊፈቀድልን ይገባል ሲሉ የፖሊስን የጊዜ ቀጠሮ ተቃውመዋል።

የተጠርጣሪዎችንና የመርማሪ ፖሊስን ጉዳይ ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ የተርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው አለመቀበሉን በመግለጽ፥ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተጠርጣሪዎች አደረሱ የተባለው ጉዳት ተነጥሎ እንዲቀርብ እና የ14 የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ለነሃሴ 8 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

ከስኳር ኮርፖሬሽን የቀረቡ ተጠርጣሪዎችን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄን በተመለከተም የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ ሃሙስ እለት ፍርድ ቤት ከቀረቡ ተጠርጣሪዎች መዝገብ ጋር አብሮ የሚታይ በመሆኑ የዘጠኝ ቀን ጊዜ በመስጠት ለነሃሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ ከቤተሰብ እና ከጠበቃ ጋር የመገናኘት መብታቸውን ፖሊስ እንዲያከብር አዟል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy