Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በሣዑዲ የሚቀሩ ዜጎች ለሚጠብቃቸው ኃላፊነቱን በግላቸው ይወስዳሉ

0 797

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በሣዑዲ የሚቀሩ ዜጎች ለሚጠብቃቸው ኃላፊነቱን በግላቸው ይወስዳሉ

ብ. ነጋሽ

በሣዑዲ ዐረቢያ በህገ ወጥነት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን የአገሪቱ መንግሥት ባወጣው የውጡልን አዋጅ መሠረት ወደአገራቸው ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት አራት ወራት አስቆጥሯል። የሣዑዲ ዐረቢያ መንግሥት ህገ ወጥ የውጭ አገር ዜጎች ይውጡልን የሚለውን አዋጅ ያወጣው መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር። አዋጁ ህገ ወጥ የውጭ አገር ዜጎቹ፣ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በ90 ቀናት ማለትም እስከ ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ ነበር። የኢፌዴሪ መንግሥት በዚህ ጊዜ ውስጥ ውጡልን የተባሉትን ዜጎቹን ወደ አገር ቤት ለመመለስ የተደራጀ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ እስከ ሰኔ 20 ወደ አገራችን እንመለሳለን ብለው ተመዝግበው ከነበሩት 110 ሺህ ኢትዮጵያዊያን መካከል 45 ሺህ ገደማዎቹን ብቻ ነበር ማስመለስ የቻለው። ጭራሽ ወደ አገራቸው ለመመለስ ያልተመዘገቡት ደግሞ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ እንደሆነ ይገመታል። በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግሥት የሣዑዲ ዐረቢያ መንግሥት ያስቀመጠውን የጊዜ ገደብ እንዲያራዘም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ በተጻፈ ደብዳቤ ጠይቋል። የሣዑዲ ዐረቢያ መንግሥት በዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ከሰኔ 18 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ የጊዜ ገደቡን በ30 ቀናት አራዘመ።

የጊዜ መራዘሙ ያስገኘውን እድል በመጠቀም ኢትዮጵያዊያኑን ወደ አገራቸው የማስመለሱ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህ በተራዘመ የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ አገራቸው ለመመለስ ተመዝግበው የጉዞ ሰነድ የወሰዱ ዜጎች ቁጥር ወደ 130 ሺህ ከፍ ብሏል። ወደ አገር ቤት የተመለሱት ደግሞ 60 ሺህ ደርሷል።

እርግጥ ቀደም ባሉት ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ጥረት በተደረገባቸው ጊዜያት በተወሰነ ደረጃ የትራንስፖርት መጨናነቅ እንደነበረ ይታወቃል። ይህ ችግር በተለይ የመመለሻ ጊዜው ከተራዘመ በኋላ ተፈቷል። ኢትዮጵያዊያኑ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከመንግሥት በተጨማሪ ወደ ሣዑዲ ዐረቢያ ተጉዞ የነበረ የኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራ ማህበር የልዑካን ቡድን የቅስቀሳ ስራ ሲሰራ ነበር። ማህበሩ እንዳስታወቀው ቀደም ሲል የነበረው የትራንስፖርት ችግር ተፈትቷል። ይሁን እንጂ በአዋጁ የተቀመጠው ቀነ ገደብ በ30 ቀናት መራዘሙን ተከትሎ በኢትዮጵያውያኑ ዘንድ መዘናጋት  መፈጠሩንና፣ የዚህ ምክንያት ደግሞ ህገ ወጥ ደላሎች መሆናቸውን ማህበሩ አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የተራዘመው የውጡልን አዋጅ ሊጠናቀቅ ሣምንት ሲቀረው የአዋጁ አስፈጻሚ የሆኑ የሣዑዲ ዐረቢያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ በርካታ ዜጎቻቸው በህገ ወጥነት በሣዑዲ ዐረቢያ ከሚኖሩ አገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያይተዋል። የአዋጁ አስፈጻሚ የሆኑት የሣዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት በዚህ ወቅት በቀሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ አገራት ዜጎች በሙሉ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በአዋጁ የተሰጠውን የጊዜ ገደብ አክብረው ከሣዑዲ ዐረቢያ የማይወጡት ላይ፣ በጸጥታ ሃይሎች የቤት ለቤት አሰሳ ተካሂዶ በህግ እንዲጠየቁ እንደሚደረግ በአዋጁ ላይ መደንገጉ ይታወቃል። አዋጁን አክብረው አገሪቱን ለቀው በማይወጡ ሰዎች ላይ የእሥራትና የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣል ነው አዋጁ የሚደነገገው። አዋጁ እንደሚለው ከ15 እስከ 50 ሺህ ሪያል የገንዘብ መቀጫ ይጣልባቸዋል። ይህ ሆኖም በግዳጅ ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል።

አዋጁ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ ለህገ ወጦች ከለላ የሰጠ ወይም የቀጠረ ግለሰብ ወይም ተቋም በአገሪቱ የወንጀል ህግ መሰረት እንዲጠየቅ እንደሚደረግም አዋጁ ይገልጻል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በህገ ወጥነት ተደብቀው የሚኖሩ ዜጎችን በበር ከበር አሰሳ በመያዝ የሚታጎሩባቸው 98 እሥር ቤቶች ተዘጋጅተዋል።

እንግዲህ ይህን ጽሁፍ በማዘጋጀበት ወቅት፣ በ30 ቀናት የተራዘመው የጊዜ ገደብ ሊያበቃ ሦስት ቀናት ብቻ ነው የቀሩት። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ እንኳን ሁሉንም በህገ ወጥነት በሣዑዲ ዐረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ቀርቶ፣ ወደ አገራቸው ለመመለስ በመመዝገብ ፈቃደኝነታቸውን ካሳዩት መካከል የቀሩትን 70 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ዜጎች እንዲመለሱ የማድረጉ ጉዳይ አዳጋች ነው።

ኢትዮጵያውያኑ የሣዑዲ ዐረቢያ መንግሥት ያወጣው የምህረት አዋጅ ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜ የቀሩት በመሆኑ እድሉን  ሊጠቀሙበት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ሰሞኑን በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ አሳስበዋል። የሥራና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሣዑዲ ዐረቢያ እየኖሩ ወደሀገራቸው ያልተመለሱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከ60 ሺህ በላይ እንደሚደርስ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ የሣዑዲ ዐረቢያ የምህረት አዋጅ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ ዜጎች ቀነ ገደቡ አብቅቶ ለችግርና ለእንግልት ከመዳረጋቸው በፊት ወደአገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አስተላልፈዋል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያዊያኑ በበቂ ሁኔታ አለመመለሳቸው  አሳሳቢ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።  “የምህረት አዋጁ ከተጠናቀቀ በኋላ ነገሮች በእኛ ቁጥጥር ሥር አይሆኑም” ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፣ ሣዑዲ ዐረቢያ በህገ ወጥ መንገድ የገቡ የውጭ አገር ዜጎችን በኃይል ለማስወጣት መዘጋጀቷን አስታውቀዋል። በቀሪዎቹ አራት ቀናት በዚያ የሚገኙ ዜጎችን ሙሉ በሙሉ ለመመለስ አዳጋች ቢሆንም ጊዜውን ተጠቅመው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ተስፋ መኖሩንም አስረድተዋል። አሉ ያሏቸው ተስፋዎች ምን እንደሆኑ ግን አልገለጹም።

እንግዲህ፤ ከላይ የተጠቀሱት እውነታዎች የኢፌዴሪ መንግሥት በሣዑዲ ዐረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሃገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ የተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ዜጎቻቸው በሣዑዲ ዐረቢያ ከሚኖሩ አገራት መንግሥታት በተለየ ልዩ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ያመለክታሉ።

ይሁን እንጂ በሣዑዲ ዐረቢያ ይኖራሉ ተብለው ከሚገመቱት አራት መቶ ሺህ ገደማ ኢትዮጵያዊያን መሃከል ወደሃገራቸው ለመመለስ የፍቃደኝነት ዝንባሌ የታየባቸው ቀርበው የተመዘገቡት ብቻ ናቸው። እነርሱም 130 ሺህ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥም በወቅቱ ወደሃገራቸው መመለስ ላይ ማመንታት ታይቷል። እስካሁን የተመለሱት ኢትዮጵያዊያን ከ60 ሺህ የማይበልጡ መሆናቸው ይህን ያሳያል።

ማንም ሊገምት እንደሚችለው የሣዑዲ ዐረቢያ መንግሥት ባወጣው አዋጅ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ተጠናቅቋል። ሁሉንም በዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደአገር ቤት ተመልሰዋል ተብሎ አይታሰብም። ያበቃለት ይመስላል። የተለየ ሁኔታ ካልተፈጠረ በሰተቀር ወደ አገራቸው ለመመለስ ተመዝግበው እስካሁን እያመነቱ የቆዩትን በሙሉ መመለስ የሚቻልበት እድል እጅግ በጣም ጠባብ ነው።

በአጠቃላይ አሁን ያለው ሁኔታ የኢፌዴሪ መንግሥትና የኢትዮጵያ ህዝብ በሣዑዲ ዐረቢያ በሚኖሩ ዜጎች ላይ እንዲደርስ የማይፈልጉት ሥቃይ፣ እንግልትና ለሰብአዊ መብት ጥሰት መጋለጥ መድረሱ አይቀሬ የመሆን እድሉ እየሰፋ ነው። ከአራት ዓመት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ የተፈፀመው ዘግናኝና ማንም ሊያስታውሰው የማይፈልገው ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

የሣዑዲ ዐረቢያ መንግሥት ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ካበቃ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንዳስታወቁት፣ ሁኔታዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥጥር ውጭ ይሆናሉ። የኢፌዴሪ መንግሥት በሉዓላዊት ሣዑዲ ዐረቢያ ህግ የማስከበር ርምጃ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ይህን አድርጉ፣ ያን አታድርጉ ማለት አይችልም።

የኢፌዴሪ መንግሥት በአዋጅ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ካበቃ በኋላ ምናልባት ማድረግ የሚችለው ተግባር፣ ኢትዮጵያውያኑ በፀጥታ አስከባሪዎች ከየተሸሸጉበት ሲለቀሙና በእሥር ቤት ውስጥ ሲታጎሩ በዓለም አቀፍ ህጎችና ስምምነቶች ላይ የሰፈሩ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ድንጋጌዎች እንዲከበሩ በመጠየቅ የተገደበ ነው። ከዚያ በመለስ በኃይል ወደ አገራቸው ሲመለሱ አገር ቤት ሆኖ ይጠብቃል። ይህ ደግሞ የሁሉም አገር ቤት የምንገኝ ዜጎች የሞራል ግዴታ ነው።

የኢፌዴሪ መንግሥት ዜጎቹ እንግልትና ሥቃይ ሳይደርስባቸው፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ሳይጋለጡ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማስቻል ያደረገው ጥረት በማንኛውም ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ባለ መንግሥት ያልተደረገና ዜጎችን የሚያኮራ መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ሆኖም የመንግሥትን ጥረት ችላ በለው የቀሩ ዜጎች ጉዳይ አሁንም ተጨባጭ መላ የሌለው አሳሳቢ ነው።

የኢትዮጵያዊያኑ ጉዳይ አሳሳቢነት፣ መንግሥት አሁንም ዜጎቹን ባለው ክፍተት ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኢትዮጵያውያኑ ቀነ ገደቡ ካበቃ በኋላ ለሚጠብቃቸው የህግ ተጠያቂነትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለሚደርስባቸው ሥቃይ፣ እንግልትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ኃላፊነቱን በግላቸው የሚወስዱ መሆኑ መታወቅ አለበት።   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy