Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአማራ ክልል የህዝብን ቅሬታ ችግር ለመፍታት በተደረገው ጥረት ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸው ተገለጸ

0 720

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአማራ ክልል ህዝብን ባሳተፈ መልኩ ለህግ የበላይነት መረጋገጥና የቅሬታ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት አስታወቀ።

የምክር ቤቱ 5ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ማምሻውን ተጀምሯል።

አፈ-ጉባኤው አቶ ይርሳው ታምሬ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት በክልሉ የተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር በመወያየት የተነሱ ቅሬታዎች በሚመለከተው አካል እንዲፈቱ ለማድረግ ሰርተዋል።

“በበጀት ዓመቱ ሊከናወኑ የተያዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት በተገቢው ፍጥነት እንዲከናወኑ አስፈፃሚውን አካል በመከታተልና በመቆጣጠር ህዝባዊ ውክልናቸውን ተወጥተዋል።” ብለዋል።

በተለይም በዓመቱ መጀመሪያ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ በሰለጠነ መንገድ እንዲፈተና ዘላቂነት ያለው የሰላም ዋስትና እንዲሰፍን ለማድረግ አባላቱ ተግተው ሲሰሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የቅሬታ ምንጭ የሆኑ አብይ ጉዳዮችን በመለየትም በየአካባቢው መፍትሄ እንዲያገኙ ድጋፍና ክትትል መደረጉን አብራርተዋል።

አባላቱ በ31 ከተሞችና ወረዳዎች እንዲሁም በ64 ቀበሌዎች በአካል በመገኘትም ከመራጩ ህዝብ ጋር ውይይት በማድረግ በተነሱ ችግሮች ዙሪያ የአስፈፃሚው አካል መፍትሄ እንዲሰጥ ድጋፍ ማድረጋቸውንም አቶ ይርሳው ተናግረዋል።

የሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራትና የህዳሴውን ጉዞ ያለምንም መንጠባጠብ በተቀመጠው አቅጣጫና ፍጥነት እንዲተገበርም ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ መከናወን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ እስከ ሐምሌ 11/2009 ዓ.ም በሚያደርገው ቆይታም በ6ኛ መደበኛ ጉባኤው ቃለ ጉባኤ፣በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ያደርጋል።

በተጨማሪም የጠቅላይ ፍርድ ቤትን የ2009 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም፣የኦዲት ሪፖርት፣የቀጣይ ዓመት በጀት እንዲሁም የተሻሻለውን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ተወያይቶ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

በመጨረሻም ልዩ ልዩ ሹመቶችና ስንብት ይከናወናል ተብሎ አንደሚጠበቅም ከምክር ቤቱ  የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy