Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በኢንዱስትሪ ፓርኮች እየደመቀች ያለች ሀገር

0 380

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በኢንዱስትሪ ፓርኮች እየደመቀች ያለች ሀገር

                                                     ዘአማን በላይ

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በፍጥነት እያደገ ነው። በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ምጣኔ ሃብታዊ ኃይል እንደሚሆን የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን እየገለፁ ነው። ለዚህ ደግሞ የሃዋሳን ጨምሮ ሰሞኑን የተመረቁት የመቐለና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በፍጥነት ማስፋፋቱ ምጣኔ ሃብቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ መቻሏን መገናኛ ብዙሃኑ አስታውቀዋል። አያይዘውም መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ካለው ፍላጎት በመነጨ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን በራሱ ወጪ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በዚህም ባለፉት አስርት ዓመታት የሀገሪቷ ምጣኔ ሃብት በአማካኝ በ10 ነጥብ ስምንት በመቶ ማደጉንም አመልክተዋል።

አዎ! የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት የከተሞችን ዕድገት ያፋጥናል፣ በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ህይወት ይቀይራል፣ የስራ ዕድልን በመፍጠር ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ያደርጋል፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ይስባል፣ የሀገራችንን ገፅታ ይቀይራል፣ የወጪ ምርት በዓይነትና በብዛት እንዲያድግና የውጭ ምንዛሬን ከፍ ያደርጋል፣ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ለገቢ ምርት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ያስቀራል።

ከዚህ በተጨማሪ ግብርናውንና ኢንዱስትሪውን በማስተሳሰር የአርሶና የአርብቶ አደሩን ገቢ የማሳደግ ሚና ይኖረዋል። ይህ ሚና በጥቅሉ ሲታይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር እየተካሄደ መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።

በኢትዮጰያ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ማምረት ስራ እየገቡ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሀገሪቱ በአፍሪካ የዘርፉ እምብርት ለመሆን የያዘችውን እቅድ እውን የሚያደርጉ ናቸው። ፓርኮቹ ሀገሪቱ ለምታካሂደው የኢኮኖሚ ተሃድሶ ስኬት ፈር ቀዳጅ ናቸውም ነው ያሉት።

ለአብነት ያህል ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተመረቀው የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ፤ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ስም ካላቸው ሀገራት ተርታ ሊያሰልፋት እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።

ፓርኩ የስራ እድል ከመፍጠርና የኢኮኖሚ እድገት ከማምጣት ባለፈ የአስተሳሰብ ባህልን ሊቀይር የሚችል ነው። ታዲያ በመቐለ ፓርክ የመሰረተ ልማት ማሟላት፣ አቅም ያላቸውን የግል ባለሃብቶች መሳብና ወጣት ባለሃብቶችም ወደ ፓርኩ እንዲገቡ የማበረታታት ቀሪ የቤት ስራዎች ይጠብቁታል።

ፓርኩ በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባ ሲሆን፥ ዛሬ የተመረቀው በ75 ሄክታር ላይ የተገነቡ 15 ሼዶች ያሉት ነው። ይህም ለአካባቢው ነዋሪዎች ህይወት መለወጥ የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል።

በ92 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የተገነባው ፓርኩ ከሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር ተዳምሮ ሀገሪቱ በ2025 የኢኮኖሚ ሽግግር ለማድረግ ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ድርሻ አለው። ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ዋና የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪ ዘርፍ መናኸሪያ በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የወጪ ንግዱ ድርሻ ከፍ እንዲል የሚያደርግ መሆኑን መረጃዎች ያሰረዳሉ።

የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማቱን በበላይነት ከሚመራው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የኢንዱስትሪ ፓርክ ማለት በአንድ በተከለለ አካባቢ ወይም ቦታ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የሚቋቁሙበት ሆኖ ልማቱን ለማፋጠን ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች በሕግ አግባብ የሚሰጡበት ማዕከል ነው። በዚህ አግባብ የሚገነባ ማንኛውም የኢንዱስትሪ ፓርክ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት የግድ ይለዋል።

በዘመናዊ አሰራር ውስጥ የሚታወቀውን የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥ አሰራርንም ይከተላል። በፓርኩ ውስጥ የሚገነቡት ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙባቸው የጋራ መገልገያዎች፣ መጋዘን፣ የብክለት ማጣሪያና ማስወገጃ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የቢሮ መገልገያ ህንፃዎች፣ የሕክምና ማዕከል፣ ትምህርት ቤት፣ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት፣ መዝናኛዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ለኢንዱስትሪዎቹ የሚያገለግሉ መሰል ተቋማትን የሚያካትቱ አገልግሎት መስጫዎች ይኖራቸዋል። ይህ በመሆኑም ፓርኩ በውስጡ የተገነቡት ኢንዱስትሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በጤናማ ሁኔታ የእርስ በእርስ ውድድር የሚያደርጉበት አካባቢ ነው ማለት ይቻላል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው።

ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።

በሀገራችን እየተከናወኑ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል።

ርግጥም ልማቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የጎላ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሚከናወኑ ስራዎችን በሂደት በሀገር ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና በሀገር በቀል ተቋማት አማካኝነት እንዲከናወኑ መሰረት ይጥላል።

ሀገሪቱ ውስጥ እየተሰሩ ያሉት የፓርኮች ልማት ምክንያት ከይዞታቸው ለሚነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነው። በመሆኑም ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በመልሶ ማስፈር የድርጊት መርሃ ግብር መሰረት ተገቢውን ካሳና ምትክ ቦታ የመስጠትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዩች በተገቢው ወቅት እንዲፈፀሙላቸው ተደርጓል።

አዳዲስ የሚገነቡትም ፓርኮች ለህብረተሰቡ ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸው። ፓርኮቹ ምንም እንኳን ለአካባቢው ነዋሪዎች ጠቀሜታ ያላቸው ቢሆንም፤ በፓርኮቹ ግንባታ ሳቢያ ከየአካባቢያቸው ለሚነሱ ዜጎች በመሰረታዊ ሁኔታ እንዲቋቋሙና ከሚገነቡትም ፓርኮች ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ እየተደረገ ነው። በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ለምርት የተዘጋጁት የመቐለና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም ወደ ማምረት ስራ የገባው የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክና ሌሎች በመላ ሀገሪቱ በመገንባት ላይ የሚገኙት ፓርኮች የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በሂደት ከግብርናው የምጣኔ ሃብት ምጣኔ ሃብታዊ ሽግግሩን እንደሚረከብ የሚያሳይ ነው። ይህ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲፋጠን ሁሉም የድርሻውን በመወጣት የመንግስትን ጥረት መደገፍ ይገባል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy