Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በግብርናው ዘርፍ  የተገኘው ስኬት በኢንዱስትሪውም ይደገማል!

0 287

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በግብርናው ዘርፍ  የተገኘው ስኬት በኢንዱስትሪውም ይደገማል!

ወንድይራድ ኃብተየስ

አገራችን ባለፉት አስራ አራት ዓመታት ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ባለሁለት አሃዝ  የኤኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የቻለችው በግብርናው ዘርፍ በተመዘገበው  ለውጥ ሳቢያ እንደሆነ በዕርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በርካታ የህብረተሰብ ክፍል  በዚህ ክፍለ ኢኮኖሚ  የተሰማሩ በመሆናቸው በዚህ ዘርፍ የሚመዘገብ ለውጥ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። ለዚህም ነው መንግስት   ይህ ዘርፍ የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ነው በማለት  በተደጋጋሚ የሚገልጸው። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የዛሬ 26 ዓመታት ማለትም በ1983 ዓ ም የአገራችን   የዋና ዋና ሰብሎች  ዓመታዊ የምርት መጠን 52  ሚሊዮን ኩንታል የነበረ ሲሆን   መንግስት ለዘርፉ  በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ይህን አሃዝ   በ2002 ዓ.ም  ወደ 191 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ ተችሎ ነበር። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማጠቃለያ 270 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ማሰባሰብ በመቻሉ አገሪቱ በምግብ ራሷን ችላለች። ይህ ትልቅ ስኬት ነው።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ  የመንግስት ዋንኛ ተኩረት የምግብ ፍላጎትን  በቤተሰብ ደረጃ  ማሳካት ነው። በአገር ደረጃ ማሳካት የተቻለውን የምግብ ፍላጎት አቅርቦት    በቤተሰብ ደረጃ በመድገም የተረጂነት ስሜትን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በመስራት ላይ ነው።  ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት  በ2008- 09 ዓ.ም  የምርት ዘመን   ከ323 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰብል ማሰባሰብ  ተችሏል። በዘንድሮው የመኸር ምርት ይህን አሃዝ ወደ 345 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ እየተሰራ ነው።

ከላይ  ለማሳየት እንደተሞከረው በአገራችን የግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ዕድገት አስመዝግቧል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረት ያደረገው   አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚተዳደርበትን የግብርናውን ዘርፍ በመሆኑ  ዕድገቱ  የሁሉንም  አርሶ አደሮችን ህይወት ዳሷል ማለት ይቻላል። የአርሶና አርብቶ አደሩ ህይወት በአብዛኛው ተቀይሯል። በርካቶቹ ከጎጆ ቤት ወደ ቆርቆሮ ቤት ተሸጋግረዋል። ልጆቻቸውን በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን በግል ኮሌጆች ጭምር ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ በማድረግ  በማስተማር ላይ ናቸው። ጥቂት የማይባሉ አርሶና አርብቶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት ገብተዋል።   

በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2008ና 2009 የምዕራባዊያኖች ኤኮኖሚ በቀውስ በተመታ ጊዜ  የበርካታ የታዳጊ አገሮች በተለይ በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተንጠለጠለ ኤኮኖሚ ያላቸው የአፍሪካ አገሮች ችግር ላይ ወድቀው ነበር። ይሁንና የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ባለሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገብ ችሏል።  የኢትዮጵያ ዕድገት የጠንካራ ፖሊሲ ውጤት ነው ሲሉ አንዳንድ የኢኮኖሚ  ባለሙያዎች  ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።  ለዚህም በአስረጂነት  የሚያነሱት ኢትዮጵያ  እዚህ ግባ የሚባል የተጥሮ ሃብትም ይሁን ቴክኖሎጂ አቅም ሳይኖራት ላለፉት አስራ አራት ተከታታይ  ዓመታት ፈጣን የኤኮኖሚ  ዕድገት ማስመዝገብ  የቻለችው መንግስት በተከተለው ትክክለኛ ፖሊሲ ነው ይላሉ።

አገራችን ይህን ፈጠን የኤኮኖሚ ዕደገት ማስመዝገብ   የቻለችው በተዓምር  ሳይሆን መንግስት በተከተለው ስኬታማ የኤኮኖሚ ፖሊሲ መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው።  በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የመንግስት ትኩረት  የግብርናውን እና የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማስተሳሰር  በአገሪቱ  የኢንዱስትሪ አብዮት ማስፋፋት ላይ ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው መንግስት የነደፈው 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትና 17 የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ ናቸው።  ሰሞኑን እንኳን  አገራችን  በቀናት ልዩነት  ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብታ  ለባለሃብቶች አዘጋጅታለች።  የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት  በራሱ ስኬት ነው ይባልም የስኬት መንደርደሪያ  እንደሆነ ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።  መንግስት እየተከተለ ያለው  ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር  አገራችንን   በሁሉም ዘርፎች  ተጨባጭ ለውጥ እንድታስመዘግበ አግዟታል።

በመንግስት ወጪ የሚለሙት ፓርኮች ሁሉም መሰረተ ልማት የተሟላላቸው በመሆናቸው ባለሃብቶች ለግንባታ የሚያወጡት ወጪም ሆነ የሚያባክኑት ጊዜ የለም።  በመሆኑም ባለሃብቶች  ቀጥታ ወደ ልማት የሚሸጋገሩ ሁኔታዎች  በመፈጠራቸው ሳቢያ  በቦሌ ለሚ ቁጥር አንድና በሃዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርኮች  የተሰማሩ ባለሃብቶች በአጭር ጊዜ ወደ ምርት በመሸጋገራቸው ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠራቸው ባሻገር ለአገሪቱ የውጭ  ምንዛሬም ማስገኘት ጀምረዋል። ባለሃብቶቹም ትርፋማ መሆን ችለዋል።

አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች  የተሟሉላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከመገንባት ባሻገር    ባለሃብቶች ወደ  ፓርኮች እንዲገቡ መንግስት  በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው። ለአብነት  የብድር አቅርቦት፣  የታክስ እፎይታ ጊዜ መስጠት፣ የገበያ አማራጮችን ማመላከት፣  በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል የሰው ሃይል  አቅርቦት በስፋት ማቅረብ ጥቂቶቹ ናቸው። በዘንድሮው ዓመት ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች  ብቻ   ከመጀመሪያ ዲግሪ በላይ  በሆነ ደረጃ   ከ150 ሺህ በላይ  ወጣቶችን ማስመረቅ ተችሏል።  

የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ዓለም ዓቀፍ ተወዳደሪነት ለማሳደግ መንግስት የተሟላ መሰረተ ልማት ከማቅረብ ባሻገር  በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል የሰው ሃይል በአንጻራዊነት በአነስተኛ ክፍያ ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታዎች እንዲመቻቹ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችንና የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትን  ገንብቷል።  የኢንዱስትሪውን ዘርፍ  ከፍተኛ  የሰለጠነ የሰው ሃይል የሚፈልግ ዘርፍ ነው። ይህ ዘርፍ ከተወለደበት የምዕራብ አገራት ወደ ምስራቁ እንዲንቀሳቀስ ያስገደደው በዋነኝነት  ተወዳዳሪ የሰራተኛ ክፍያ ፍለጋ ነበር። የምስራቁ ጎራ በወቅቱ ሁኔታዎችን አመቻችቶ በመቀበሉ አሁን ላይ  እጅን ተቀይሮበታል።  አሁን ላይ ኢትዮጵያ ይህን ዘርፍ በማማለል ላይ ትገኛለች። የኢፌዴሪ  መንግስት በዚህ ዘርፍ የተሻለ ልምድ ካላቸው የምስራቅ ኤዥያ  አገራት (ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር፣ ማሌዥያ፣ ቬትናም ወዘተ) ልምድ በመቅሰም ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ዘርፉ  የሚመራበት ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ በመተግበር ላይ ይገኛል።   

የኢንዱስትሪ  ፓርኮችን መንግስት በራሱ ወጪ በመገንባት  ሁሉም መሰረተ ልማቶች እንዲሟላላቸው በማድረግ እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶች በአንድ መስኮት እንዲያገኙ ማድረግ በመጀመሩ የበርካታ  ዓለም ዓቀፍ ብራንድ አምራች የሆኑ ኩባንያዎችን ቀልብ መሳብ ችሏል። የምዕራቡ ዓለም ታዋቂ  ኩባንያዎች ሳይቀር በሃዋሳና ቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ  የኢንዱስትሪ ፓርኮች  ገብተዋል።    

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ እንዳስቀመጠው የመንግስት ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫ ግብርናውንና ኢንዱስትሪውን ማስተሳሰር ነው። ኢንዱስትሪው የግብርናውን እንዲሁም ግብርናው የኢንዱስትሪውን ምርት መጠቀም ሲችል ሁለቱም ዘርፎች ተያይዘው ያድጋሉ። አገርም ተጠቃሚ ትሆናለች። ይህ ካልሆነ ግን  አሁን ባለው ሁኔታ  ግብርናው እጅግ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ  አምራች ኢንዱስትሪው  ለውጥ የማያመጣ ከሆነ አርሶና አርብቶ አደሩ ለምርታቸው የተሻለ ዋጋ ማግኘት የማያስችላቸው ሁኔታ ስለሚፈጠር ግብርናው በራሱ ዕድገቱ ይገታል። በመሆኑም ሁለቱን ዘርፎች ማመጋገብ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚና አለው።

ኢትዮጵያን ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መዳረሻነት  ተመራጭ የሚያደርጋት ሌላው ጉዳይ በተመጣጣኝ ክፍያ የሃይል አቅርቦት ማስፋፋት መቻሏ  ነው። ኢትዮጵያ ከማንኛውም አገራት በላይ ለሃይል አቅርቦት መስፋፋት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ላይ ነች። በዕትዕ ሁለት መጨረሻ የአገሪቱን  የሃይል አቅርቦት ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች  በመተግበር ላይ ናቸው።  ኢትዮጵያ የምትገነባው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ታዳሽ ሃይልን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ቀጣይነቱም ሆነ አዋጭነቱ  አጠራጣሪ አይደለም።  

በኢትዮጵያ ከየትኛውም የአፍሪካ አገር በተሻለ ርካሽ የኤሌክትሪክ ሃይል ክፍያ ያለ በመሆኑ  አገራችን ለኢንዱስትሪው  ዘርፍ  ምቹ መዳረሻ እንደምትሆን በዕርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ፓርኮች በሚገነቡባቸው አካባቢዎች  የጥሬ ዕቃ አቅርቦትም ሆነ ምርቶችን ለማጓጓዝ እንዲያመች የባቡር ትራንስፖርት እንዲስፋፋ ማድረጉ  የአገራችንን ምርቶች ዓለም ዓቀፍ  ተወዳዳሪነት ያሳድገዋል።  በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት አገራችን በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችው ተጨባጭ ዕድገት በኢንዱስትሪውም ዘርፍ  በመድገም የአገራችንን የኢኮኖሚ ስርዓት ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ የሚያደርገውን   ማዋቅራዊ ሽግግር  ማሳካት ይቻላል።     

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy