Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በግብር ስም የሚካሄድ ኪራይ ሰብሳቢነት

0 457

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በግብር ስም የሚካሄድ ኪራይ ሰብሳቢነት

ዳዊት ምትኩ

ከግብር ሁኔታ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች አስፈራሚ ተግባሮችን ሲያከናውኑ ተስተውሏል። ግብር መክፈል የዜግነት ክብር ቢሆንም፤ አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች ልማታዊ ነጋዴውን ጭምር በማሳሳት ግብርን በመቃወም ስም ዕቃዎችን ያለ አግባብ በመጋዘኖች በማከማቸት አሊያም ህዝባዊ አገልግሎትን በማቋረጥ ሆን ብለው የገበያ እጥረትን ለመፍጠር ያደረጉት ተግባር ፈፅሞ የተሳሳተ ነው።

እነዚህ ነጋዴዎች በዚህ ተግባራቸው በአንድ በኩል ዋጋ በማስወደድ የራሳቸውን ህገ ወጥ ትርፍ ለማግኘት የሞከሩ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የፀረ ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያ ሆነው አገራችን ውስጥ ምሬት በመፍጠር አመፅ እንዲነሳሳ ለማድረግ ጥረዋል። ታዲያ ይህን በግብር ስም የሚካሄድ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር መድፈቅ ይገባል። እንዲህ ዓይነቱ አሰራር አንዱን ጥሎ በሌላው ማጣት ላይ የሚደረግ የዜሮ ድምር ጨዋታ ስለሆነ መቆም ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን በአሁን በምትገኝበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ልዩነትን በሠላማዊ መንገድ መፍታት፣ መቻቻልን መሰረት ማድረግ እንዲሁም አንዱ ሲያገኝ ሌላው በልማታዊ ውጤቱ መጠን የሚያገኝበት ሁኔታ በመኖሩ ነው፡፡

ዳሩ ግን በዜሮ ድምር ውጤት አሰላለፍ፤ አንዱ ሲያገኝ የሌላው የማግኘት መብት በዚያው መጠን ይዘጋል፡፡ እናም በዚህ የጥሎ ማለፍ ውድድር ውስጥ መቻቻል የሚባል ነገር ከቶውንም ሊታሰብ አይችልም፡፡

ታዲያ ውድድሩ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ውስጥ የተንሰራፋ ከሆነ፤ ፖለቲካው ራሱ የዜሮ ድምር ጨዋታና ፀረ- ዴሞክራሲያዊ ከመሆን የዘለለ ዕጣ ፈንታ ሊኖረው የሚችል አይመስለኝም፡፡ በመሆኑም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ የዜሮ ድምር ውጤት የጥሎ ማለፍ የንግድ ውድድር እንዲዘጋ፣ በአስተሳሰቡ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች እጆቻቸው ሊሰበሰብ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ አሊያ ግን በሰበብ አስባቡ አንድ የሚያነጋግር ጉዳይ በተፈጠረ ቁጥር በኪራይ ሰብሳቢነት አባዜ መታመሱ በማንኛውም መስፈርት ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብና ተግባር የህዝቡን ሃብት ከመዝረፍ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው፡፡ እርግጥም የዘረፋ ድርጊትን ከኪራይ ሰብሳቢነት ለይቶ መመልከት አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አንድ ግለሰብ ሊኖረው የሚችለው የመዝረፍ ዕድል ሌላውም እኩል በሆነ ሁኔታ ሊያገኘው ስለማይችል ነው፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ ሁሉም እኩል ይዝረፍ እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል። ካለይ እንዳልኩት የኪራይ ሰብሳቢነት አሰራር የዜሮ ድምር ጨዋታ ነው። በዚህ ጨዋታ  በዝርፍያው ውስጥ አንዱ ሲያገኝ የሌለው የማግኘት መብት በዚያው መጠን እንደሚዘጋ በግልፅ የሚመላክት ነው፡፡

ለምሳሌ ያሀል አንድ ባለሃብት ከመንግስት ሃላፊ ጋር ተመሳጥሮ በእከክልኝ ልከክልህ የጥገኝነት ቀመር የ10 ሚሊዮን ብር ዕቃ ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሲያስገባ፤ በዚያኑ ያህል ይህን ዕቃ በህጋዊ መንገድ አስገብተው ግብር እየከፈሉ የሚነግዱ በርካታ ዜጎችን ከገበያው ውድድር ውጪ ማድረጉ አይቀርም፡፡

ታዲያ በእንዲህ ዓይነቱ በአቋራጭ የመበለፅግ ፍላጎት ተጠቃሚዎቹ ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ናቸው፡፡ እናም አብዛኛው ህዝብ የበይ ተመልካች ሆኖ በልማት ውጤቱ መጠን ሃብት የሚያፈራበት ሁኔታ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ሰሞኑን በአንዳንድ ኪራይ ሰብሳሰቢ ነጋዴዎች የተካሄደው ተግባር ማሳያ ነው፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ፀረ-ዴሞክራሲ በመሆኑም በመስማማት ላይ ተመርኩዞ ሊሰራ አይችልም፡፡ ከዚህ ይልቅ የመጠቃቀም ሰንሰለቶችን ከላይ እስከታች በመዘርጋትና ደጋፊን በማብዛት ዝርፊያን የማጧጧፍ አማራጭን ይከተላል፡፡

በሰንሰለቱ የታችኛው ጫፍ ላይ ያለው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ሆኖ እንዲሰማው የማድረግ አቅጣጫን የሚከተለው ይህ የዝቅጠት አደጋ፤ በተግባር ሲፈተሽ ምንም እንኳን ዝቅተኛው ክፍል አንድ ዓይነት ታንኳ ላይ የተሳፈረ ቢሆንም፣ ከበላዩ ጋር ከተጋጨ በቀጥታ ከትስስሩ ውጭ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

ታዲያ ይህን መሰሉ አስተሳሰብ በሰፈነበት ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲን መዝራት፣ በምድረ በዳ ላይ እህል በትኖ ሰብል ለማጨድ የማለም ያህል ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ሀገር ዴክራሲን ለማጎልበት ከፈለገ በቅድሚያ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር ማምከን ይኖርበታል፡፡

መንግሥት እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም ይሁን ነገ የሚያካሂዳቸው ማናቸውም የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት የዚህ መሰረታዊ እውነታ ውጤቶች መሆኑን ለመገንዘብ የሚያስቸግር አይመስለኝም።  

ሁላችንም እንደምንረዳው፤ በማንኛውም የመንግሥት የስራ ኃላፊነት ያሉ ግለሰቦች ህዝብን እንጂ ራሳቸውን ለመጥቀም አይደለም ወንበር ላይ የሚቀመጡት፡፡ እርግጥ ህዝብን ለማገልገል ቆርጠው የተነሱና ዴክራሲያዊ አስተሳሰብ ያላቸው ባለስልጣናት መኖራቸው አይታበይም፡፡

ምናልባትም እነዚህ ባለስልጣናት በሰሞኑ የኪራይ ሰብሳቢዎች ተግባራት ውስጥ አይሳተፉም ብሎ መደምደም አይቻልም። ያም ሆኖ አሁንም የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነቱን እንዳይዝ መንግስት ብርቱ ቁጥጥር ማድረግ አለበት። ህጋዊ እርምጃዎችንም መውሰድ ይገባዋል።

በተለይም መንግሥት የሁለተኛውን የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት ሰፋፊ ስራዎችን ጀምሮ እያካሄደና በህዝቡ ከፍተኛ የለውጥ ስሜት ውጤት እያገኘ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር እንደ አላስፈላጊ ችካል ደንቃራ ሆኖ አላላውስ ማለት አይኖርበትም፡፡ በመሆኑም በጥገኝነት ላይ የጀመረውን የማጥራት ዘመቻ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

በመሆኑም በሙስና በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የወሰደው አግባብነት ያለው እርምጃም “የጨለማው ዓለም ደራሲያን” እንደሚያስወሩት የፈጠራ ልቦለድ ሳይሆን፤ ህዝቡ በእጅጉ የተደሰተበት ተግባር ነው፡፡

በቀጣይነትም መዋቅሮቹን በጥልቀት በማጥናትና በመፈተሽ፤ የህዝቡን ተጠቃሚነት በይበልጥ ከሚያረጋግጠው የልማት ዕቅድ መንገድ ላይ ጥገኞችን ጥግ በማስያዝ ገለል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ግብር መክፈል የአገር ኩራት ሆኖ ሳለ፤ በግብር መክፈል ሰበብ ዕቃ መደበቅና ማከማቸት እንዲሁም የዋጋ ንረት ለመፍጠር መሞከር ዋነኛው የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግስትም የማያወላውል እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy