Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትራንስፎርሜሽኑ የስኬት ሃዲደ ነክሷል

0 348

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ትራንስፎርሜሽኑ የስኬት ሃዲደ ነክሷል

ኢብሳ ነመራ

የኢትዮጵያ  ኢኮኖሚ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት በአማካይ ባለሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገብ ችሏል። በዚህም፣ ከዚያ ቀደም ለዘመናት  በማሽቆልቆል ሂደት ላይ የነበረው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ የእድገት ትንሳኤ አግኝቷል። በዚህ እድገት የዜጎች የድህነት ደረጃ ማሻሻል አሳይቷል። ሰሞኑን በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማሕበራዊ ጉዳይ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ፣ ኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በፊት 44 በመቶ የነበረውን የሃገሪቱን ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎች ምጣኔ ወደ 22 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሏን የኢፌዴሪ ፕላን ኮሚሽን ባቀረበው የኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት አተገባባር ሪፖርት አስታውቋል።

ስለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ምስክርነት የሰጠው የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ አይደለም። የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተለው ልማታዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የማይዋጥላቸው የዓለም ባንክንና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋምን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ምስክርነታቸውን መስጠት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል።

የዓለም ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው የዓለም ሃገራት የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ ሪፖርት፣  በ2017 ዓ/ም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ከአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚሆን አስታውቋል። እንደ የዓለም ባንክ ትንበያ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት 8 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ያስመዘግባል።

በአፍሪካ ከኢትዮጵያ በመቀጠል ታንዛንያ 7 ነጥብ 2 በመቶ፣ አይቮሪኮስት 6 ነጥብ 8 በመቶ እንዲሁም ሴኔጋል 6 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ከሁለተኛ እስከ አራተኝነት ያለውን ደረጃ ይይዛሉ ብሏል የዓለም ባንክ። የዓለም ባንክ ሪፖርት እነዚህ የአፍሪካ ሃገራት የሚያስመዘግቡት የኢኮኖሚ እድገት መነሻ፣ በመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት፣ በግብርናና በአገልግሎት ዘርፍ ያስመዘገቡት ጉልህ እድገት መሆኑን ያመለክታል።

በተመሳሳይ፣ ኢትዮጵያ የኬንያን የኢኮኖሚ ዕድገት በመብለጥ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚው የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት እንደምትሆን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በያዝነው ዓመት መተንበዩ ይታወሳል። በኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ያላቸው እየተጠናከረ የሄደ ተሳትፎ፣ የውጭ ባለሐብቶች በቀዳሚነት የቻይና ባለሐብቶች ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረጋቸው ሃገሪቱ በኢኮኖሚ ዕድገት የመሪነት ደረጃውን እንድትይዝ ያደረጉ ምክንያቶች በሚል ተጠቅሰዋል።

አሁን የሃገሪቱን ኢኮኖሚ የመሪነት ሚና ከግብርና ወደኢንደስትሪ ለማሸጋጋር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተዘጋጀቶ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል። የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በ2007 ዓ/ም ተጠናቋል። አሁን 2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግበራ ወቅት ላይ እንገኛለን። የኢኮኖሚ መሪነቱን ሚና ወደማምረቻ ኢነደስትሪ ማሸጋጋር በዘረፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንትን ይሻል። በዋናነት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዋቅራዊ ሽግግሩን በማሳካት ረገድ የጎላ ሚና ይኖረዋል።

በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግስት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ የሚያስችሉ በርካታ ማበረታቻዎችን አዘጋጅቷል። ከዚህ በተጨማሪ በማምረቻ ኢንደስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ የውጭ ባለሃብቶች በፋብሪካ ግንባታ ሂደት የሚገጥማቸውን ውጣ ውረድ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት የሚያስችሉ፣ እንዲሁም ለምርትና ለገበያ ቅልጥፍና አመቺ መሰረተ ልማትና አገልግሎቶች የተሟላላቸው የኢንደስትሪ ፓርኮችን እየገነባ ነው።

በዚህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እድገት እያሳየ ነው። የተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት ድርጅት ከአንድ ወር በፊት ባወጣው የዓለም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ሪፖርት፣ በፈረንጆቹ 2016 ዓ/ም ወደ አፍሪካ የፈሰሰው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ቢቀንስም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ግን በ46 በመቶ እድገት ማሳየቱን አስታውቋል።

ድርጅቱ የ2017 ዓ/ም ኢንቨስትመንት ትንበያን በተመለከተ ያወጣው ሪፖርት፣ በ2016 ዓ/ም ኢትዮጵያ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ማግኘቷን አስታውቋል። በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ ያገኘችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ እድገት የታየበት ብቻ ሳይሆነ፣ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማያውቅ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል። በ2016 በምስራቅ አፍሪካ 7 ነጥብ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የተገኘ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ወደኢትዮጵያ የሄደ መሆኑን ነው ሪፖርቱ ያስታወቀው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያገኘችው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን ከ2015 ዓ/ም ጋር ሲነጻጻር በ46 በመቶ እድገት አሳይቷል ይላል የድርጅቱ ሪፖርት።

ይህ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እድገት በኢኮኖሚ ወስጥ የማምረቻ ኢንደስትሪው የመሪነት ድርሻ እንዲኖረው በማድረግ ትራንስፎርሜሽኑን በማሳካት ረገድ የማይተካ ሚና አለው። የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጥ በማምጣት የማምረቻ ኢንደስትሪው የመሪነት ሚና እንዲኖረው ለማሰቻል እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መሃከል ሌላው የሚጠቀስ ተግባር የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ ነው።

የኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰሞኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደንብ አጽድቋል።  ደንቡ የሃገሪቱን የኢንዱስትሪ ፓርክ የኢንቨስትመንት መጠን የሚያሻሽሉ መሠረታዊ አሰራሮችን በመዘርጋት በፓርክ ውስጥ በሚሰሩ ፋብሪካዎና ከፓርክ ውጭ በሚገኙ አምራቾች መካከል የምርት ግብአትና የገበያ ትስስር በመፈጠር የሃገር ውስጥ እሴት የሚጨምርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያግዛል ተብሏል።

ደንቡ አምራች ድርጅቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በመሳብ ሃገሪቱን ተወዳዳሪ የሚያደርግና፣ የተወዳዳሪነት አቅሟን የሚያጠናክር፣ በዋናነት የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ የማሳደግ ክህሎት ሽግግርና ሌሎች መሠረታዊ ዓላማዎችን የሚያሳካ መሆኑን የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዳመነበትም ተገልጿል።

እንደዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እመነት ደንቡ ዘግይቷል። ደንቡ የኢንደስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደስራ መግባት በጀመሩበት ወቅት መዘጋጀት ነበረበት። ያም ሆነ ይህ በሃገሪቱ የማምረቻ ኢንደስትሪ ፓርኮች ተገንብተዋል። ወደስራ የገቡ ፓርኮችም አሉ። በመገንባት ላይ የሚገኙም አሉ። እስካሁን የተገነቡትና በቀጣይነትም የሚገነቡት የኢንደስትሪ ፓረኮቸ የወጪ ንግድ ምርቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ የሚገኙ ሰባት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አሏት።. የኢትዮጵያ የኢንደስትሪያል ፓርኮች ቦርድ ሰሞኑን እንዳስታወቀው፣ የሃገሪቱን የማመረቻ ኢንደስትሪና ኤክስፖርት ዘርፎችን ለማሳደግ እስከ እስከቀጣይ ዓመት ማለትም እስከ 2010 ዓ/ም ማገባደጃ ድረስ የኢንደስትሪ ፓርኮችን ቁጥር 15 ለማድረስ እቅድ ተይዟል።

ኢትዮጵያ የኢንደስትሪ ፓርኮቿን ቁጥር የማሳደግ እቅዷ መድረሻ በ2017 ዓ/ም የማምረቻ ኢንደስትሪ ዘርፉ ሃገሪቱ ከምታመነጨው አመታዊ አጠቃላይ ሃብት (GDP) 20 በመቶው እንዲሁም ከወጪ ንግድ የ50 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው ለማስቻል መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።

2010 ዓ/ም ጥር ወር ላይ የቂሊንጦ ፋርማሲቲካልና የቦሌ ለሚ ቁጥር 2 የኢንደስትሪ ፓርኮች ስራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚያው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የባህር ዳርና የጅማ ኢንደስትሪያል ፓርኮች፣ በሰኔ ወር የደብረ ብርሃንና አረርቲ ኢንደስትሪያል ፓርኮች ፋብሪካዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። የድሬዳዋና የአዳማ ኢንደስትሪያል ፓርኮችም እንዲሁ ግንባታቸው ይጠናቀቃል ተብሏል።

በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት የተመዘገበውን እድገት ከማስቀጠል ባሻገር ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ አምጥቶ አምራች ኢንደስትሪው የመሪነቱን ቦታ እንዲረከብ ለማድረግ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ነድፋ ተግባራዊ እያደረገች ነው። ከላይ ከብዙ በጥቂቱ የተጠቀሱት አስረጂዎች መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ኢኮኖሚውን ትራንስፎርም የማድረጉ ሂደት የስኬት ሃዲድ ነክሷል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy