Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትኩረት ለወጣቱ

0 759

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ትኩረት ለወጣቱ

ዳዊት ምትኩ

ወጣቶች ይህን አገር በቀጣይ የሚረከቡ ናቸው። ዛሬ እነርሱን በተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኙ ማድረግ ነገ አገራችን የምትፈልገውን የሰው ሃይል ማብቃት ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለወጣቶች ትኩረት ሰጥቷል። ግና ትኩረቱ ሁሉን አቀፍ ሊሆን ይገባል።

ወጣቶቹም ቢሆኑ በመንግስት የሚደረግላቸውን ድጋፍ በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል። መንግስትም ድጋፉን ካደረገ በኋላ ክትትል ማድረግ ይኖርበታል። በአሁኑ ወቅት በተለይም እንደ ኦሮሚያ ባሉ ክልሎች እየተሰራ ያለው ተግባር ጥሩ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። ይህን መሰሉ ትኩረት በሁሉም ክልሎች ውስጥ ተፈፃሚ መሆን ያለበት ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ መነሻው በመገባደድ ላይ ባለው የ2009 ዓ.ም መግቢያ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾ ጉዳዩን አስመለክተው ያደረጉት ንግግር ነው።

በወቅቱ ፕሬዚዳንቱ ለህዝብና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ “…የሀገራችን ወጣቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ገንቢዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ዛሬ በምንገኝበት ወቅት የራሳቸው ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሏቸው በመሆኑ እነዚህን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት ይሰጠዋል” በማለት ተናግረዋል።

ይህ የመንግስት አቋምም ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት ዕድል የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋም እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ መግለፃቸው ይታወሳል።

ይህ ጥረት ይሳካ ዘንድም የፋይናንስ አቅርቦትን ማስፋት፣ አዳዲስ የኘሮጀክት ሃሳቦችን ማመንጨትና አሳታፊ የአፈፃፀም ስርዓት መገንባትን ድግ እንደሚልና መንግስትም በያዝነው ዓመት በሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በማቋቋም ስራውን በ10 ቢሊዮን ብር እንደሚጀምር ማስታወቃቸውም አይዘነጋም። የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀየሰው ይህ ኘሮግራም በየጊዜው እየተገመገመ አስፈላጊው የማስተካከያ ርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም ማስታወቃቸው እንዲሁ የሚታወስ ነው።

እርግጥ ይህ የ10 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቀቃሽ ፈንድ በቅርቡ በመንግስት ከፀደቀ በኋላ ወደ ስራ ለመግባት ተችሏል። በፌዴራል ደረጃ ከተያዘው ከዚህ ተንቀሳቃሽ ፈንድ በተጨማሪ ክልሎች የራሳቸውን በጀት በማከል የወጣቱን የስራ አጥነት ሁኔታ ለመቀነስ ርብርብ እየተደረገ ነው። ያም ሆኖ አሁንም የበረታ ጥረት ያስፈልጋል።

ታዲያ እነዚህ መንግስታዊ ጥረቶች ሀገራችን የአፍሪካ ህብረት በወጣቶች ላይ ከያዘው አቋም ጋር አንድ የሆነ አስተሳሰብ ቀደም ብላ ማራመዷን የሚያሳይ ይመስለኛል። ህብረቱ በወጣቶች የስራ ፈጠራና ተጠቃሚነት ዙሪያ የያዘው አቋም የሀገራችንን ፕሮግራም የሚያጠናክር መሆኑ ግልፅ ነው። እናም በወጣቶች የስራ ፈጠራና ተጠቃሚነት ዙሪያ የተያዙ አቋሞች ተጠናክረው ለወጣቱ ብሩህ ተስፋ ማምጣት ይኖርባቸዋል።

እርግጥ ወጣቶች የዚህች ሀገር ገንቢዎች ናቸው። ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ፋና ወጊዎች ሆነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሀገርን ማበልፀግ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል።

እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው ሀገር በወጣቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ከወጣቱ አፍላ ጉልበት የሚያገኘውን ልማታዊ ፋይዳ ማረጋገጥ ካልቻለ ሁለት ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ።

የመጀመሪያው በርካታ ቁጥር ያለው ስራ አጥ ወጣት ይፈጠርና ይህ ስራ አጥ ኃይልም የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው የውስጥና የውጭ ሃይሎች መጠቀሚያ ሆኖ ለሁከትና ብጥብጥ በር የሚከፍት ሲሆን፤ ቀጣዩ ደግሞ ሀገራት ከወጣቱ ማግኘት የሚገባቸውን የልማት ተጠቃሚነት ዕውን ማድረግ አይችሉም።

እርግጥ ስራ የሌለው ወጣት ማናቸውንም ጉዳዮች እንደ ስራ ሊመለከት ይችላል—የሁከት ተግባርንም ቢሆን። ይህ ደግሞ የተረጋጋ ሰላምና የልማት ስራ የሚከናወንበትን ሀገር ሊረብሽና ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል። ለዚህ አባባሌ በቅርቡ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የሁከት ተግባር ሁነኛ አስረጅ ይመስለኛል። ወጣቶች በየአካባቢያቸው ካለው የመልካም አስተዳደር ችግር በተጨማሪ በሚፈለገው መጠን ስራ ሳይፈጠርላቸው በመቆየቱ፤ ለሀገራችን የውጭ ጠላቶች ለሚላላኩ የጥፋት ሃይሎች ፀረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ሰለባ ሆነው ነበር።

እናም አስቀድሞ ወጣቱን በሚፈለገው መጠን በስራ እንዲታቀፍ ማድረግ ቢቻል ኖሮ፤ የተከሰተው ጥፋት ዕውን አይሆንም ነበር። ምክንያቱም ከሀገራዊ ልማት ተጠቃሚ የሆነ ወጣት በምንም መልኩ የሀገሩን ጥቅም በመፃረር የሌሎች ባዕዳን ሃይሎች መጠቀሚያ ሊሆን ስለማይችል ነው።

እናም የኢፌዴሪ መንግስት ወጣቱን አቅም በፈቀደ መልኩ አደራጅቶ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ፕሮግራም ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ይመስለኛል። ወጣቱ ኃይል አፍላ ጉልበት ያለው በመሆኑ፤ ሀገራት ይህን ለስራ ዝግጁ የሆነ ጉልበት በሚገባ መንገድ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይህን ጉልበት አጣጥሞ በተገቢው መንገድ መጠቀምም ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።

ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ናቸው። እነርሱን በማናቸውም ሀገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ በማስገባት ማሳተፍ ስራዎችን በአፍላ ጉልበት እንዲሁም በፈቃደኝነትና በፍላጎት ስሜት ሊተገብሩት ይችላሉ።

ይህ ደግሞ የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም በወጣቶች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ውጤቱ መልሶ የሚከፍለው ሀገርን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

በሌላ በኩልም ወጣቱ የመንግስትን ትኩረትና የተመደበለትን ተንቀሳቃሽ ፈንድ በአግባቡ ለመጠቀም ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል። በእኔ እምነት ራስን ለስራ ማዘጋጀት አንድን ችግር ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደመሄድ ያህል ይቆጠራል። እናም ወጣቱ አስቀድሞ ራሱን ለማንኛውም ስራ ማዘጋጀት አለበት። ማንኛውም ስራ ከችግር መውጫ ቀዳዳ መሆኑን ማመን ይኖርበታል። በአጭሩ ወጣቱ ስራን ሳይንቅና ምናልባትም በስደት ቢሄድ ለባዕድ ሀገራት ሊያበረክተው የሚችለውን የጉልበት ስራ ዓይነት ጭምር ስራዎችን አክብሮ በመስራት የመንግስትን ትኩረት አሟጦ ሊጠቀምበት ይገባል። “ስራ ክቡር ነው” የሚለውን አርማ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ ይጠበቅበታል። ያኔ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ከምንም በላይ እያሰበችለት ያለችውን ሀገሩን መጥቀሙ አጠያያቂ አይሆንም።

ከዚህ በተጨማሪም ወጣቱ ስራ ፈጣሪ እንጂ ስራ ጠባቂ ሊሆን አይገባም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የፌዴራል መንግስትና ክልሎች ወጣቱ በስራ ውስጥ እንዲያልፍ ተንቀሳቃሽ ፈንድ አዘጋጅተዋል።

ወጣቱ በዚህ ፈንድ እንደምን ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ እንደሚችል ማሰብ ይኖርበታል። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ውስጥ የተመቻቸ የስራ ምህዳር አለ። ዋናው ነገር ይህን ምቹ የስራ ድባብ በፈጠራ ክህሎት አጅቦ እንዴት ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ማወቁ ላይ ነው። እናም ወጣቶችም በተፈጠረላቸው ምቹ ዕድል ሊጠቀሙ ይገባል። ሁሉም ክልሎችም ለወጣቱ የሚፈለገውን ያህል ትኩረት መስጠትም ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy