Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አንዳንድ ነጥቦች ስለ ቀን ገቢ ግብር አወሳሰን

1 1,949

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አንዳንድ ነጥቦች ስለ ቀን ገቢ ግብር አወሳሰን

                                                  ታዬ ከበደ

ግብር መክፈል የዜግነት ክብርና ኩራት ነው። የመሰረተ ልማትና ሌሎች ተግባሮች የሚወሰኑት መሰረተ ልማት የሚገነባውና ፍተሐዊ የሃብት ክፍፍል እውን የመሆነው መንግስት ከህዝቡ በሚሰበስበው ግብር አማካኝነት ነው። የቀን ገቢ ግብሩ አወሳሰን ወጪን ያላካተተ ነው። አንድ በንግድ ስራ ላይ የተሰማራ አካል ወይም ግለሰብ ወጪዎቹ ያልወጡለት በቀን የሚያከናውነው አጠቃላይ ሽያጭ ማለት ነው።

ትመናውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፤ ለምሣሌ በርበሬና ቅመማ ቅመም ንግድ የተሰማራ አንድ ነጋዴ የቀን ገቢው 1 ሺህ 500 ነው ተብሎ ከተገመተበት ይህ ግምት በዓመት ተባዘቶ ይከፍላል ማለት አይደለም። በዓመቱ ውስጥ ያወጣቸው ወጪ ተሰልቶና በዓመቱ ቀናት ተባዝቶ ግብር የሚከፈልበት 10 በመቶው ብቻ ይሆናል። በዚህ ስሌት መሰረትም የነጋዴው ዓመታዊ ተከፋይ ግብር 5 ሺህ 370 ብር ብቻ ይሆናል ማለት ነው። እናም የቀን ገቢ ግብር አወሳሰንን ከዚህ አኳያ መመልከቱ ጠቃሚ ነው።

እንደሚታወቀው በአዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀፅ 3 መሰረት የግብር ከፋዮች ደረጃ ቀድሞ ከነበረው ከፍ ማለቱ ይታወቃል። በዚህ መሰረትም ደረጃ “ሀ” ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢያቸው ከአንድ ሚሊዮንና ከዚያ በላይ፣ ደረጃ “ለ” ድርጅቶችን ሳይጨምር ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ5 መቶ ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የሆኑትን ያጠቃልላል። ደረጃ “ሐ”ግብር ከፋዮች ደግሞ ድርጅቶችን ሳይጨምር ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢያቸው ከብር 5 መቶ ሺህ በታች የሆኑትን የሚይዝ ነው።

መንግስት የግብር አሰባሰብ ስርዓቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት አንድ ግብር ከፋይ ዕቃ ሸጦ ወይም አገልግሎት ሰጥቶ ያገኘውን ዕለታዊ ገቢ መሰረት ያደረገ ግብር አሰባሰብ ተከትሎ ወደ ስራ ተገብቷል። በዚህ መሰረት በ2009 ዓ.ም የአገሪቱንና የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሰረት ያደረገ አዲሱ የፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ያስቀመጣቸውንና በ2003 የቀን ገቢ ግምት መረጃ ጥናት ላይ የነበሩትን ክፍተቶች በማረም አማካይ የቀን ገቢ ግምቱ የታዩ ችግሮችን ለመሙላት ታስበ የተዘጋጀ ነው።

በፌዴራል ገቢ ግብር አዋጅ መሰረት የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በአማካይ የቀን ገቢ መረጃ መሰረት የሚስተናገዱ በመሆናቸው፤ አማካኝይ የቀን ገቢ ግምቱ መውጣቱ አስፈላጊ ሆኗል። እንዲሁም አማካይ የቀን ገቢ ግምቱ በህጉ መሰረት የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ የሌለባቸው በመሆናቸው፤ የሚጠበቅባቸውን ግብርና ታክስ በቁርጥ እንዲከፍሉ ስለሚያደረግ አዲሱ የገቢ አወሳሰን ይህን አሰራር ያስቀረ ነው። አሰራሩ በተለይም ለግብር ከፋዩ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው።

ቀደም ሲል የቀን ገቢ ግምት የነበራቸውና ጥናቱ የተሰራላቸው ግብር ከፋዮች ውጤቱ ሲተገበር ለንግድ ትርፍ ግብር ብቻ የ2009 በጀት ግብር እንዲከፍሉ ተደርጓል። ቀጥተኛ ያልሆነ ታክስን በተመለከተም ዓመቱን ሙሉ በቀድሞ የቀን ገቢ ግምት መሰረት እንዲከፍሉ ይደረጋል። ታዲያ ይህ አሰራር ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ አዲሱ የቀን ገቢ ግምት ቀጥታ ላልሆኑ ታክሶች ተግባራዊ የሚሆን መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ይገባል።

ይሁንና ቀደም ሲል ግምት ያልነበራቸውና በታሳቢም ያልከፈሉ ግብር ከፋዮች ሆነው አሁንም መረጃ ያልተሰበሰበላቸውን በተመለከተ ከተቻለ ለማሳወቅ ሲመጡ ግምት እንዲቀርብ በማድረግ ይህ ካልሆነ በግብር ማስታወቂያ ወቅት እንዲቀርብ በማድረግ ለንግድ ትርፍ ብቻ የ2009 በጀት ዓመትን እንዲከፍሉ ይደረጋል።

ቀጥታ ያልሆኑ ታክሶችን በተመለከተ የዓመቱ ሙሉ ወይም ስራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ራሳቸው በሚያሳውቁት እንዲከፍሉ የተደረገ ሲሆን፤ ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ አዲሱ የቀን ገቢ ግብር ቀጥታ ላልሆኑ ታክሶችም ገቢራዊ ይሆናል።

እዚህ ላይ ከቀን ግብር አወሳሰን ጋር ተያይዞ ግንዛቤ መያዝ ያለበት እውነታ አለ። ይኸውም በየጊዜው እያደገ ያለ ኢኮኖሚ እና የንግድ እንቅስቃሴ እድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የገቢ ግብርና የታክስ አስተዳደር አዋጆች ላይ ማሻሻያ በመደረጉ የግብር ማስከፈያ ማዕቀፎች መለወጣቸው ነው። ይህን የለውጥ አሰራር ታሳቢ ባደረገ መልኩ የገቢና የታክስ ማስፈከፈያዎቹ ተለውጠዋል። ለውጡ ግን ነጋዴውን ማህበረሰብ ለመጉዳት አሊያም ሌሎች ወገኖችን ለመጉዳት አይደለም።

እንደሚታወቀው አገራችን በፈጣን እድገት ውስጥ ትገኛለች። መሰረተ ልማቶች፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችና ሌሎች የመንግስት ወጪዎች የሚሸፈኑት ከየትም በመጣ ገንዘብ ሳይሆን ህብረተሰቡ ከሚከፍለው ግብር ነው። መንግስት መልሶ ለህዝቡ ለሚሰጣቸው አገልግሎት የሚውሉ ናቸው። የቀን ገቢ ግብር አወሳሰኑ እነዚህን እውነታዎች ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆኑን መረዳት ይገባል።

እርግጥ ግምቱ በተካሄደበት ወቅት ገማቾቹ ሰዎች ናቸውና የመብዛት አሊያም የመቀነስ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ፍትሃዊም ላይሆን ይችላል። ለዚህ ደግሞ አንዳንድ ግብር ከፋዩች ዕቃ በማሸሽ፣ የንግድ ቦታን በመዝጋት፣ መረጃን አሳንሶ በመስጠትና መሰል ችግሮችን በመፍጠር ግምቱ ሙሉ በሙሉ ፍትሃዊ እንዳይሆን የበከኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል።

ያም ሆኖ በቀን ግብረ ገቢ አወሳሰን ላይ ፍትሃዊነትን ለማንገስ መንግስት በየወረዳው የቅሬታ ሰሚ በማቋቋም የህብረተሰቡን ቅሬታ እየተቀበለ ነው። በቅሬታውም ትክክል ያልሆነን አወሳሰን በማስተካከል፣ ከገቢው በታች የሆነውንም የማረም ስራዎች እየተከናወኑ ነው። ህብረተሰቡም ይህን እውነታ ሊገነዘበው ይገባል።

በእኔ እምነት ቀደም ሲል ግብር ሳይከፍሉ ይነግዱ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለምን ግብር ከፈልን ማለት ያለባቸው አይመስለኝም። በዓለም ላይ ግብር የማይከፈልበት ስራ የለም። ይህ እውነታ እንኳንስ በምድራዊ አሰራር ቀር በሃይማኖታዊም የሚታወቅ ነው። ምክንያቱም ከኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮቶች ውስጥ አንዱ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የኢየሱስን ለኢየሱስ” ተብሎ ስለተገለፀ ነው። እናም ግብር መክፈል ከምድራዊ አስተሳሰቡ ባሻገር ሃይማኖታዊ ተቀባይነትም ያለው ነው።

ያም ሆኖ የቀን ገቢ አወሳሰኑ በነጋዴው ላይ ተጨማሪ ግብር ለመጣል አይደለም። ይልቁንም በየትኛውም ዓለም እንደሚሰራበት በመረጃ ላይ የተመሰረተ የግብር ስርዓት ለመፍጠር ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። እናም የንግዱ ማህበረሰብ ይህን እውነታ ሊገነዘብ ይገባል።

እናም በአንዳንድ ወገኖች ‘መንግስት በንግዱ ማህበረሰብ ላይ አላስፈላጊ ግብር ጨምሯል’ እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን የንግዱ ማህበረሰብ መረዳት አለበት። የቀን ገቢ ግምቱ የነጋዴውን አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴ በመረጃ የተደገፈ እንዲሆን ለማድረግ ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት እንዲፈጠር፣ ፍትሃዊ የግብር አከፋፈል ስርዓቱን እንዲጠብቅ ለማድረግ የተዘጋጀ ብቻ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።

ስለሆነም አንዳንድ የራሳቸው የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ወገኖች እውነታውን ሆን ብለው እያጣመሙት በመሆኑ ሃቁን በመረዳት ህዝቡ ከራሱ የሚሰበሰበው ገንዘብ መልሶ ጠቀሜታው ለራሱ መሆኑን ማወቅ ያለበት ይመስለኛል።

 

  1. Desalegn says

    ግብር መክፈል ለነገ የሚሆን ገንዘብ ባንክ ማስቀመጥ ማለት ነው ነገር ግን አንዳንድ ባለሙያወች በተለይ ወረዳ ላይ ብቃት ህሊና የሚባል ነገር የላቸውም የቀን ገቢ አወሰሰን ላይ ፍትሀዊነት የለም የግብር መወሰኛ መመሪያውንም ከነ ጭራሹ የማያውቁ አሉ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy