Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አዲስ አበባ የእኛ ብቻ ሳትሆን የመላው ዓለም ናት

0 541

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አዲስ አበባ የእኛ ብቻ ሳትሆን የመላው ዓለም ናት!

ወንድይራድ ሀብተየስ

አዲስ አበባ የአዲስ አበባዊያን ብቻ ሳትሆን የሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ እንዲሁም የመላው አፍሪካዊያን  እና የዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ጭምር  ነች።  አዲስ አበባችን ከኒዮርክ፣ ከጄኔቭ  በመቀጠል በሶስተኝነት የምትጠቀስ   የዲፕሎማቲክ  ከተማ ነች።  ይሁንና አዲስ አበባችን የእነዚህ ሁሉ አህጉርና ዓለም ዓቀፍ ዲፕሎማቶችና ድርጅቶች መቀመጫ ትሁን እንጂ ለረጅም ጊዜ ምግባሯን የሚመጥን መሰረተ ልማት የተሟላላት ከተማ አልነበረችም። አሁን ላይ አዲስ አበባ ፈርሳ የምትገነባ ከተማ ለመሆን በቅታለች። አዲስ አበባ በተጨባጭ መቀየር ጀምራለች። አሁን ላይ መዲናችን ማንንም ማማለል የምትችል ከተማ ለመሆን በቅታለች።    

ከሃምሳ ዓመታት በላይ  አዲስ አበባችን  የአፍሪካ መዲና በመሆን ከአንድ ቢሊዮን ለማያንሱ  አፍሪካውያን የሚኮሩባት ሁለተኛ አገር በመቆጠር  በማገልገል ላይ ያለች ከተማ ነች።  ባለፉት 54 ዓመታት የአፍሪካ መሪዎች በአዲስ አበባ ስብሰባ ሲያካሂዱ አንድም  የከፋ ሳንካ ገጥሟቸው አያውቅም። ይህ ስኬት በጸጥታ ሃይሉ ጥንካሬ ብቻ የመጣ ሳይሆን  በዋናኝነት  በህዝቡ ሰላም ወዳድነት ነው። ኢትዮጵያዊያን እንግዳ ተቀባይነታችንንና ሰላም ወዳድነታችንን በተግባር አሳይተናል። በዚህ ሁላችንም ልንኮራ ይገባናል። የሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች መገኛ ትንሿ ኢትዮጵያ – አዲስ አበባ።

ሰሞኑን የትምክህትና  ጠባቡ ሃይል   የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከአዲስ አበባ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም በተመለከተ እርስ በርስ ሲናቆሩ ተመልክተናል።  እጅግ የሚገርም ነው። እነዚህ ጽንፈኛ ሃይሎች ዕርስ በርስ የሚባሉት ምንም በማይመለከታቸው ጉዳይ  ነው። አዲስ አበባ የሁሉም ናት። እነዚህ ሃይሎች  “የዘሬ በቀር ያንዘረዝረኝ”  እንደሚባለው ሆኖባቸው እንጂ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያዘጋጀው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከአዲስ አበባ ሊያገኝ የሚገባው ጥቅም ረቂቅ አዋጅ ማንንም የሚጎዳ አይደለም።  

አዲስ አበባ ተሳስበን ተሳስበን ተቻችለን መኖር የምንችል ከሆነ ለሁሉም ትበቃለች። ይሁንና የጥበትና ትምክህት ሃይሉ እየረጩት ባለው መርዘኛ ፖለቲካ ለማንም የማትጠቅም ደካማ ኢትዮጵያን ለማምጣት ነው።  እነዚህ ሃይሎች ለአገራችን አንድነት ለህዝቦች አብሮነት ጸር ናቸው።  የአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት  መሃከል  ያለው ግንኙነትን የሚወስነው ህገመንግስቱ ላይ በሰፈረው መርህ  ብቻ ነው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 49 ንኡስ አንቀጽ 5፤ በኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃከል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ልዩ ጥቅም እንደሚኖረው በግልጽ አስፍሯል። አሁን ላይ  መንግስት ረቂቅ ህግ ያዘጋጀው ይህን ታሳቢ አድርጎ ነው። በረቂቅ ህጉ ላይ ከሰፈሩት ነገሮች መካከል አንዱ ቋንቋ ነው።

በአዲስ አበባ የሚኖሩ ነበር የኦሮሞ ተወላጆች እንዲሁም አዲስ አበባ የሚሰሩ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሰራተኞች ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የማስተማር ህገመንግስታዊ መብት አላቸው። ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ቢማሩ  የተሻለ ውጤት  ማስመዝገብ እንደሚችሉ በዓለም ዓቀፍ  ደረጃ  ስለታመነበት ማንኛውም ህጻን በአፍ መፍቻ ቋንቋው እንዲማር  ሁኔታዎች ተመቻችተዋለ። በዚህ መሰረት የኦሮሚያ ክልል የትምህርት መስጫ ቋንቋ ኦሮሚኛ በመሆኑ በአዲስ አበባ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆችም   በቋንቋቸው  እንዲማሩ እድሉ የተፈቀደላቸው።  የአዲስ አበባ አስተዳደርም  በኦሮሚኛ  መማር ለሚፈልጉ የከተማዋ ነዋሪዎች  የኦሮሚኛ  ትምህርት ቤት የማቋቋም  ሃላፊነት እንዳለበት መወሰኑ አግባብነት ያለው አካሄድ ነው።

በረቂቅ አዋጁ ላይ የተካተተው ሌላው ጉዳይ የኦሮሚኛ ቋንቋን ከአማርኛ በተጓዳኝ የአዲስ አበባ አስተዳደር የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል የሚል ነው። እንግዲህ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት የማግኘት መብታቸው በኢፌዴሪ ህገመንግስት ተረጋግጧል። በዚህ መሰረት በኦሮሚያ ክልል መሃከል በምትገኘው አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ የሚኖሩና የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች በቋንቋቸው አገልግሎት የማግኘት ህገመንግስታዊ መብት አላቸው። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መስሪያ ቤቶች ኦሮሚኛ ከአማርኛ በተጓዳኝ የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል የተደነገገው ለዚህ ነው።

ይህ ማለት ግን ኦሮሚኛ አማርኛን ተክቶ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል ማለት  አይደለም። አሁን ትምክህተኛው አካል ይህን ይዞ ሌሎች ብሄሮች ጉድ ፈላባችሁ በማለት የተሳሳተ መረጃ ለህብረተሰቡ ለማቀበል በመሯርጥ ላይ ነው። አማርኛ አሁንም ያገለግላል። ተጨማሪ የሆነው ኦሮሚኛ ነው።  እንደሰማነው  አማርኛ ተናጋሪዎች በሚበዙባቸው  የሰሜን አሜሪካ ግዛቶች አማርኛ የስራ ቋንቋ ሆኗል። አማርኛ ባህር ተሻግሮ በባዕድ አገር የስራ ቋንቋ ሆኖ ሳለ ኦሮምኛ በአገሩና በምድሩ ላይ ይህን እድል ቢያገኝ የሚበዛበት አይደለም።  በቅን ልቦና ከተመለከትነው።

ሌላው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታና የእጣ ሲያድል መቆየቱ ይታወቃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የእጣ አሰጣጥ  ላይ ሴቶቸ 30 በመቶ፣  የአስተዳደሩና የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የመንግሥት ሠራተኞት ደግሞ 20 በመቶ ልዩ ኮታ ተይዞላቸው የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። አሁን ላይ  ይህ ለአዲስ  አበባና ፌዴራል መንግስት ሰራተኞች  የተሰጠጠው  እድል አዲስ አበባ ለሚገኙ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ሰራተኞችም ይሰጣቸው ነው። ይህ ምን አድሎ ያስብላል። እንደእኔ እንደኔ  ከዚህ ቀደም የነበረው አሰራር ነው አድሎን ፈጥሮ የነበረው። ምክንያቱም መንግስት ሰራተኛ ከሆነ የፌዴራል ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ሆነ የኦሮሚያ ተለይቶ መታየት የለበትም ባይ ነኝ።  አሁን ላይ  ይተግበር የተባለው ሌሎች አዲስ አበባ ከተማ ያሉ  የመንግስት ሰራተኞች  የሚያገኙትን ዕድል የኦሮሚያም ክልላዊ መንግስት ሰራተኞችም ያግኙ ነው።

እንግዲህ ከላይ ያነሳናቸው አኳር ጉዳዮች በየትኛው መስፈርት ይሁን አድሏዊ የሚያስብሉት።  በቅርቡ  በኢንጂነር ይልቃል ጌትነት የሚመራው ሰማያዊ ፓርቲ ረቂቅ አዋጁን ሲያብጠለጥለው ተመልክቼ  እጅግ ገርሞኛል።  ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት  “በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተረቀቀ የተባለው አዋጅ በጥድፊያ የወጣ፣ግልፅነት የጎደለው፣ህገ መንግስቱን የጣሰ፣ በመረጃና በጥናት ላይ ያልተመረኮዘ፣ አጠቃላይ የዴሞክሰራሲ መርሆና ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 49 አላማ ጋር በእጅጉ የተቃረነና ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት አገዛዙ የተነሳበትን የፖለቲካ ትኩሳት ለማብረድ በማሰብ የተቀነባበረ ግልብ ሴራ ነው”  ሲሉ መግለጫ ሰጠተዋል። አዋጁ ኢንጂነሩ እንደሚሉት አይደለም። እንደእኔ እንደኔ ረቂቅ አዋጁ የሁሉንም ዘላቂ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ሆኖ አገኝቼዋለሁ።

ይህ  ረቂቅ ሰነድ ህገመንግስታዊ መሰረት ያለውና ማንንም ለመጥቀምም ሆነ ለመጉዳት ታስቦ የተዘጋጀ  አይደለም።  የህገ መንግስቱ አንቀፅ 49/5 ዓላማ የአገልግሎት አቅርቦትን፣የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምናን እና የጋራ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን አፈፃፀም የተመለከተ ነው። ይህን በህግ አግባብ መተርጎም  ቅን አስተሳሰብ ያለው ማንኛው ሰው ሊደግፈው የሚችል ሰነድ  ነው።  ሁሉም  ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሰራር መዘርጋት ክፋት የለውም። መንግስትም የተከተለው ይህን አሰራር ነው። አንድ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ  እንገነባለን የምንል ህዝቦች የሚያዋጣን ሁሉም  እኩልና ዘላቂ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሰራር መተግበር  እንጂ የአንዱ ጥቅም በሌላው መስዋዕትነት የሚገኝ መሆን የለበትም ባይ ነኝ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy