Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ኢትዮዽያ  በአቢይ ምርቶች የመጨረሻ ጥግ የደረሰች ሃገር”

0 737

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ኢትዮዽያ  በአቢይ ምርቶች የመጨረሻ

ጥግ የደረሰች ሃገር”

ስሜነህ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት በማደግ ላይ እንደሚገኝ እና በቀጠናው ትልቁ ምጣኔ ሀብታዊ ኃይል እንደሚሆን Deutsche Welle በድረገጹ ባስነበበው ትንታኔ አስታውቋል። “ኢትዮጵያ ኬንያን የበለጠችበት ምክንያት መንግሥት ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችን እያካሄደ በመሆኑ እና ሸቀጦች በሀገር ውስጥ መመረት በመጀመራቸው ነው” ሲል የድረገጹ ትንታኔ አመላክቷል። የሐዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክን ጨምሮ በርካታ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ በመከናወን ላይ መሆናቸውን ያስታወቀው ይህ ትንታኔ መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ባለው ፍላጎት ምክንያት ትላልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በከፍተኛ ሁኔታ በመገንባት ላይ ይገኛልም ብሏል።  ባለፉት አሥርት ዓመታት የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በአማካኝ በ10.8 በመቶ ማደጉን የጠቆመው ድረገጹ ጥያቄው ይህ የሀገሪቷ እድገት ምን ያህል ዘላቂ ሆኖ ይቀጥላል የሚለው ነው ሲል አቅርቧል።

የዓለም ባንክ የሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሮች ቦርድ የኢትዮጵያን የልማት ፍላጎት ለመደገፍ የአምስት ዓመቱን የዓለም አቀፍ አጋርነት ማዕቀፍ (CPF) ማጽደቁን በድረገጹ ይፋ አድርጓል። በርካታ ባለድርሻ አካላት በማዕቀፉ ላይ ሰፊ ምክክር ማካሄዳቸውን ያስታወቀው የባንኩ ድረገጽ ማዕቀፉ በሁለተኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ጋር አብሮ ሊሄድ እንደሚችል ጠቁሟል። የዓለም አቀፍ አጋርነት ማዕቀፉ ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የልማት አቅጣጫን እንድትከተል የሚደግፍ መሆኑን ያስታወቀው ባንኩ ማዕቀፉ መሠረታዊ ትምህርት ላይ በማተኮር፣ የገበያ ተደራሽነትን በማሳደግ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድልን በመፍጠር፤ እንዲሁም በከተማም ሆነ በገጠር ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማስፋፋት መዋቅራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ለማበረታታት እንደሚረዳ አመላክቷል። ኢትዮጵያ ባለፉት አሥርት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ሰብአዊ ልማት ላይ አስደናቂ ዕድገት አምጥታለች ያለው የድረገጹ ዘገባ የሀገሪቷ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ባለፉት አሥርት ዓመታት በአማካኝ በ10.5 በመቶ አድርጓል ሲል አሞካሽቷል።

ይህ ተረክም የኢትዮጵያ እድገት ሊሞካሽ ከቻለባቸው ምክንያቶች መካከል ዋነኛ አስረጅ የሆኑትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች  የተመለከቱ ሰሞንኛ አስረጂዎች በመጥቀስ የመሞካሸቷን ተገቢነት በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚያጠይቅ ነው።

በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት በመላ አገሪቱ መንግስት 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችና 17 የግብርና ማቀነባበሪያ ቀላል ኢንዱስትሪዎች በመገንባት ላይ ይገኛል። ከነዚህ መካከልም ትናንትና እና ከትናንት በስቲያ የኮምቦልቻና የመቀሌ የኢንዱስተሪ ፓርኮች ተመርቀዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት  ከኢንዱስትሪያላይዜሽን መስፋፋትና  የከተሞች ዕድገት ጋር ተያይዞ  የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ከመቀየር፣ ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማስገኘት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከመሳብ እና የአገራችንን ገጽታ ለመቀየር፣ የወጪ ምርት በዓይነትና በብዛት በማሳደግ እና የውጭ ምንዛሬን በማሳደግ   እንዲሁም  የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት  ለገቢ ምርት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት፤ ግብርናውን እና ኢንዱስትሪውን በማስተሳሰር የአርሶ እና የአርብቶ አደሩን ገቢ በማሳደግ በአጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ  በማሳደግ ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ጠበብቶች ይመሰክራሉ።

በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምረቃ ስነስርዓት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፥ የኢንዱስትሪ ፓርኩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ መጠናቀቁ ለአገራችን የኢንዱስትሪ ልማትና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲሁም ለደሴና አካባቢው ልማት የጎላ አስተዋጾ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኩ በኮምቦልቻ መገንባቱ በውጭ ንግድ ምርት ላይ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ከተማዋ ከጅቡቲ ወደብ ከ480 ኪሎሜትር በማይበልጥ ርቀት ላይ በመገኘቷ በወደቡ በኩል ለሚደረገው የንግድ ልውውጥ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። የፌደራል መንግስት ከያዛቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ይህንን ኢንዱስትሪ ፓርክ ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን አስቀድሞ በማሟላቱ፤ እንዲሁም ክልሉ እና የአካባቢው ህዝብ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ከተማዋ ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ተመራጭ እንድትሆን አድረጓታል፡፡

የኢንዱስትሪ ሼዶችን መገንባት ብቻውን ግብ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በተገነቡት የማምረቻ ህንጻዎች ውስጥ ባለሃብቶች በመግባት ከሚፈጥሩት የስራ እድል ባለፈ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩላቸውን እንዲወጡ  መንግስት በትኩረት የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

በኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ፓርክ ምረቃ ላይ እንደተገለጸው ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ባለሃብቶች የምርት ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ የአካባቢው ህብረተሰብ፣ የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የሐይማኖት አባቶች የሰላም እና የመረጋጋት ስራን በመስራት የድርሻውን ሊወጡ ይገባል፡፡ በሃገሪቱ እየተገነቡ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጤታማ እንዲሆኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በ90 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተገነባው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለ20 ሺህ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይገመታል፤ በኢንዱስትሪ ፓርኩ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችም ወደ ስራ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

የኮምበልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የተካሄደው በ75 ሄክታር መሬት ላይ ነው። የፓርኩ ዋና ትኩረት ጨርቃ ጨርቅና አልባሳትን በማምረት የወጭ ንግድን ማጠናከር ሲሆን፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ በተገነቡት ዘጠኝ ሼዶች ለ20 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ያስችላል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኩም የአሜሪካ፣ የኮሪያና የጣሊያን ኩባንያዎች ገብተው ለመስራት ጥያቄ ማቅረባቸው በምረቃ ስነስርአቱ ላይ ተመልክቷል። የኮምበልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጅቡቲ ወደብ በ480 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ በኩባንያዎች ተመራጭ መሆኑም ነው የተመለከተው። የሌሎቹንም እዚህ ጋር መመልከት ስለመሞካሸታችን ተገቢ አስረጅ ይሆናል።  

380 ኪሎ ሜትር  የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጂቡቲ ወደብ ያለው ርቀትሲሆን፤ 480 ኪሎ 678 ኪሎ ሜትር  የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጂቡቲ ወደብ ያለው ርቀት ነው ። 750 ኪሎ ሜትር  መቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጂቡቲ ወደብ ያለው ርቀት ሲሆን ፤ 863 ኪሎ ሜትር    ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጂቡቲ ወደብ ያለው ርቀትነው። 985 ኪሎ ሜትር   ደግሞ ባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጂቡቲ ወድ ያለው ርቀት መሆኑ ተመልክቷል።

የጨርቃ ጨርቅና ልብስ ስፌት ኢንዱስትሪው መንግሥት በአፍሪካ በቀላል አምራች ኢንዱስትሪው መስክ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ያደርጋሉ ተብሎ ከሚነገርለት መካከል መሆኑ  ምናልባትም ትልቁን ድርሻ የሚወስድ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በመጪው አምስት ዓመት ጊዜ ውስጥም ከዚሁ ከጨርቃ ጨርቅና ስፌት ዘርፍ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ በወጪ ንግድ በኩል እንዲገኝ ታቅዷል፡፡ ከዘርፉ የሚጠበቀው ጠቅላላ ምርት 2.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመትም የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ይፋ አድርጓል፡፡

በመጀመርያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የድርና ማግ፣ የስፌት ወዘተ. የባህል አልባሳትን ጨምሮ ፋብሪካዎች አምርተው ወደ ውጭ የሚልኩት ምርት በ2007 ዓ.ም መጨረሻ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንዲያስገኝ ይጠበቅ ነበር፡፡ ሆኖም ውጤቱ 98 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ያስገኘ ሆኗል፡፡ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ የሚያወጣ ምርት በጠቅላላው ሲጠበቅ ውጤቱ ግን 689 ሚሊዮን ዶላር ብቻ በመሆን የመጀመርያው አምስት ዓመት ዕቅድ ተደምድሟል፡፡ በዚህም ሳያበቃ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ወደ 90 ከመቶ ለማድረስ ይታሰብ ነበር፡፡ እርግጥ ከአምስት ዓመት በኋላም አሁን ያሉት 130 ፋብሪካዎች በአማካይ እያመረቱ ያሉት ከሙሉ አቅማቸው 35 እስከ 40 ከመቶ ያህሉን ብቻ በመጠቀም ነው፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ያለፉትን አምስት ዓመታት ለመድገም ግድ የሆነበት የጨርቃ ጨርቅና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ባለፉት ዓመታት የወጠናቸው ግቦች ያልተሳኩት ‹‹ከአቅም በላይ ስለተለጠጡ›› ብቻ እንዳልሆነ ይከራከራል፡፡ ዕቅዱ ሲታለም ታሳቢ አድርጓቸው ከነበሩት መካከል በዓለም ላይ ግዙፍ መሆኑ የሚነገርለት የህንድ ኩባንያ በዋቢነት ይጠቀሳል፡፡

ለዘርፉ ዕቅድ ታሳቢ ከነበሩት ውስጥ አንዱ ኤስቪፒ ቴክስታይል ግሩፕ የተባለው ኩባንያ በህንድ ያለው አቅም ሲታይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በጠቅላላ ቢደመሩ እንኳ የኩባንያውን 40 ከመቶ የማይደርሱበት አቅም ያለው ግዙፍ ኩባንያ መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው፡፡

በመሆኑም ይህ ኩባንያ ቢያንስ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር መነጋገር እንደጀመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይሁንና ኩባንያው ‹‹በ2003 ዓ.ም መጨረሻ ወይም በ2004 መጀመርያ ገደማ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ምርት ወደ ውጭ እንደሚልክ ይጠበቅ ነበር፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መጨረሻ ማለትም በ2007 ዓ.ም ይኸው ኩባንያ ብቻ 700 ሚሊዮን ዶላር የማስገኘት አቅም እንዳለው በመንግስት በኩል ተረጋግጦ ነበር፤ ይህንን የመሳሰሉ አራት አምስት አቅም ያላቸው ኩባንያዎችን መሳብ ቢቻል ኖሮ ዕቅዱን ለማሳካት ብዙም እንደማይከብድ ይገልጹና አሁን ለምረቃ የበቁት ፓርኮች እንዲህ አይነቶቹን በመሳብ ያለጥርጥር ውጥኑን ለማሳካት እንደሚያስችሉ ይጠቅሳሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን  የኩባንያው የመውደቅ ምክንያት ውስጣዊ ሳይሆን በዓለም በተከሰተው የፋይናንስና የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ እንደሆነ ተነግሯል፡፡   

በዚህም ተባለ በዚያ ያለፈው አምስት ዓመት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው መስክ ውጤታማ አልነበረም፡፡ በዕቅዱ መጨረሻ ዓመት የሚጠበቀው አንድ ቢሊዮን ዶላር ነበር፤ ነገር ግን የተገኘው መቶ ሚሊዮን ዶላር ገደማ ብቻ ነው። ምንም እንኳ የህንዱ ኤስቪፒ ግሩፕ ባጋጠመው የፋይናንስ ቀውስ ዳፋ ያቀደውን አለማሳካቱ፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪም ችግር ውስጥ ቢጥለው ከዚህ ኩባንያ ውጭ ይጠበቅ የነበረው መጠን እንኳ አለመገኘቱ ግን ሌላው ዘርፉ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ ምላሹና ተስፋው ደግሞ እነዚህ የተመረቁ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን እንደሚሆኑ አያጠራጥርም ፡፡

ኢንስቲትዩቱ የጠቀሳቸው እና  የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ያሰበውን እንዳያሳካ እክል ከሆኑበት ማነቆዎች መካከል የመሬት፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውኃ አቅርቦት በፍጥነት ለማግኘት አለመቻል፣ ለጥሬ ዕቃም ሆነ ለማሽነሪ ግዥ የሚውል የብድርና የውጭ ምንዛሪ እጦት ሲሆኑ፤ እነዚህ ማነቆዎች በእነዚህ ፓርኮች መፍትሄ ያገኛሉ፡፡  

ያም ሆኖ ግን አሁንም መንግሥት ተጨማሪ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባትና እየተገነቡ ያሉትን በፍጥነት አጠናቆ ሥራ ማስጀመር ጠበቅበታል።

ኢንዶኔዥያ የሚገኘው የታል ማምረቻ ፋብሪካ ሃዋሳ ወደሚገኘው የማምረቻ ፓርክ በመምጣት ቲሸርቶችን እያመረተ ወደ ዩ ኤስ አሜሪካ መላክ ጀምሯል። ይህንኑ መነሻ በማድረግ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የተገኙ ሃብቶችን ለግድብ፣ ለመንገድና የባቡር መስመር በማዋል ኢትዮዽያ እመርታዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማስመዝገቧን ያተተው ፋይናንሺያል ታይምስ እኤአ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ተከታታይ አመታት የ10 በመቶ አማካይ ዕድገትን በማሳየት በምስራቅ አፍሪካ በግዙፍ ኢኮኖሚዋ የኬንያን ቦታ መረከቧን አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምን ዋቢ በማድረግ ፅፏል።    

ኢትዮዽያ የኤሺያን አይነት የኢንዱስትሪ አብዮት ለማቀጣጠል እየጣረች እንደሆነና ከባንግላዴሽና ከቻይና በመቀጠል የአለም የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለመሆን እየሰራች ትገኛለች። የታል የአልባሳት አምራች ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢትዮጵያን ሲገልጻት “ኢትዮዽያ  በአቢይ ምርቶች የመጨረሻው ጥግ የደረሰች ሃገር ናት” ብለዋል።

የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለኢንዱስትራላይዜሽን ስትራቴጂ በአቅርቦት የተሟላና አውራ የኢንዱስትሪ መንደር ነው ያለው ዘገባው በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ መንደሩ በመግባት የማምረት ስራ መጀመራቸውን አስነብቧል።

“በቂ የሰው ሃይል፣ ለወጪ ንግድ የተመቸ ቅርበት ያለው ወደብ፣ አዋጭ የጉልበት ዋጋ፣ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የሚያስችል ፖሊሲ ያለው መንግስት እንዲሁም ወደ አውሮፓና አሜሪካ ገበያ ለመግባት ከቀረጥ ነፃ የገበያ ዕድል የምታመቻች ሃገርን ስንፈልግ ቆይተናል።” በማለት የታል ካምፓኒ ሠራተኛ የሆኑት ሚስተር ሊ መናገራቸውንም ጭምር። 

ከአለም የሃይል ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ርካሽ የኤሌክትርክ ሃይል ዋጋ ማለትም 0.03 የዶላር ሳንቲሞችን በኪሎ ዋት የሚተመንባት ሃገር መሆኗ ደግሞ ሌላው ሎተሪ ነው፤ ሲሉ ባለሃብቶቹ ይናገራሉ።  መሰረቱን በኒውዮርክ ያደረገውና በሃዋሳ ኢንዱስትሪ መንደር ማምረቻውን የከፈተው ፒቪኤች (PVH) የተሰኘው የአልባሳት አምራች ፋብሪካ የሰፕላይ ዋና ኦፊሰር ቢል ማክሬይዝ መንግስት በገባው ቃል መሰረት የሃይል አቅርቦት እንዳቀረበላቸው መናገራቸውም ተመልክቷል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የመቀሌና የኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ መንደሮች በቅርቡ ወደ ምርት እንደሚገቡ ፋይበር ቱ ፋሽን የተሰኘው ድረ ገፅ መዘገቡ የሚታወስ ነው። የሃዋሳን የኢንዱስትሪ መንደር ፕላን መሰረት በማድረግ የተገነቡት የኢንዱስትሪ መንደሮቹ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ የውጭ ኢንቨስትመንት  እንዲጨምር እንደሚያደርጉት ተጠብቋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ታዋቂ ከሆኑት ቫኒቲ ፌይር እና ኤች ኤንድ ኤም የአለም ጨርቃጨርቅና አልባሳት ድርጅቶች ጋር ወደ ሁለቱ የኢንዱስትሪ መንደሮች ገብተው በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ ምክክር እያደረገ መሆኑንም መረጃው አክሎ ገልጿል።

እኤአ ከ2015 እስከ 2020 ዓ.ም ውስጥ ተፈፃሚ በሚሆነው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ኢትዮጵያ ለምትገነባቸው የኢንዱስትሪ መንደሮች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ የግንባታ ጨረታ ማውጣቷንም የወጣው መረጃ ያመለከተው ሰሞኑን ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት የሃዋሳን አይነት የኢንዱስትሪ መንደር በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች ለመገንባት ዕቅድ ይዟል። ለግንባታ ዘጠኝ ወራትን ብቻ የፈለገው የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለ60 ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል፤ ለ150 ሺዎች ደግሞ ቀጥተኛ ያልሆነ ስራን ፈጥሯል። በዚህ ዓመት ስራ ለማስጀመር ትልም የተያዘላቸው ሌሎች ዘጠኝ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም በግንባታ ላይ ናቸው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy