ኢትዮጵያና ሰርቶ የመለወጥ ምህዳሯ
ደስታ ኃይሉ
የኢትዮጵያ የስራ ምህዳር እየተለወጠ ነው። መስራት የቻለ ሁሉ ህይወቱን መምራት ይችላል። በዚህ ምቹ የስራ ምህዳር መለወጥ የሚችል ማንኛውም ዜጋ ራሱን ሊለውጥ ይችላል። ከዚህ አኳያ በአሁኑ ወቅት ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱና የሚመለሱ ዜጎች በአገራቸው ሰርተው ማደግና መለወጥ ይችላሉ።
መንግስት ለማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ የሚያደርገውን ድጋፍ ለተመላሾቹም እንደሚያደርግም በመግለፅ ተመላሾቹ በሀገራቸው ቢሰሩ እንደ ሳዑዲ ብዙ ገንዘብ ማግኘት ባይችሉም ራሳቸውን በተገቢ ሁኔታ ማስተዳደር የሚችሉበት ምህዳር እዚህ ሀገር ውስጥ እውን ሆኗል። ይህን እውነታ በዋነኛነት ቤተሰብ ለልጆቹ ማስረዳት ይኖርበታል።
እርግጥም አንዳንድ ቤተሰብ ልጆቻቸውን ወደ ውጭ ሀገር ልከው በሚላክላቸው ገንዘብና ድጎማ ኑሯቸውን ለማሻሻል ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የልጆቻቸውን ወጪ በማሟላት በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ባህር አቋርጠው እንዲሰደዱ ይገፋፋሉ፤ ያስገድዳሉም። ይህ አይነቱ የቤተሰብ ድርጊት ከስራ አጥ ወጣቶች በተጨማሪ ስራ ያላቸውንም ይጨምራል።
በዚህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ውስጥ ሆነው በህልም ዓለም የሚንሳፈፉት እነዚህ ግለሰቦች ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሲዳረጉ መስተዋላቸው አልቀረም። የዚህ ዓይነቱ ድርጊት እንዲከናወን አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱት መካከል የቅርብ ዘመድ አዝማዶችም ይገኙበታል።
ከቤተሰቡ ጋር ያላቸውን ዝምድናና ቀረቤታ በመልካም አጋጣሚነት በመጠቀምና ተቆርቋሪ በመምሰል ዜጎችን ከደላላ ጋር በማገናኘት በሚከፈላቸው ኮሚሽን ኪሳቸውን ሲያደልቡ ይስተዋላሉ። እናም የእነዚህ ወገኖች “የአዞ እምባ”ን የሚያየው ቤተሰብ፤ የሰዎቹ ሁኔታ ከቅርበታቸውና ከሃዘኔታ የመነጨ ስለሚመስለው ብሎም የወደፊት “ሀብታምነቱ” እየታየው ልጁን አሳልፎ በመስጠት ለአደጋ ሲዳርገው ይታያል።
እንግዲህ ልብ በሉ! በዚህ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚሰማሩትና የድለላ ተግባርን ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ያደረጉት እነዚህ ሃይሎች በርካታ እንደሆኑ ሁሉ የትስስር መረባቸውም ከቤተሰብ እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚያደርስ መገመቱ አዳጋች አይሆንም። ታዲያ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰው አደጋ በመጠንም ሆነ በአይነቱ የተለያየ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። ከመብት ጥሰት እስከ ህይወት ማጣትን በሚያስከትለው በዚህ ወንጀል ሰለባ የሚሆኑት ዜጎቻችን ቁጥር ከፍተኛነትም እንዲሁ። የሀገራችን ገጽታ መበላሸትም ሳይዘነጋ።
ከገንዘቡ በስተጀርባ በዜጎች ላይ የሚደርሰው የመብት ጥሰት፣ የአካል መጉደል፣ የጤና መታወክ አደጋም በነርሱ ዘንድ ግምት የሚሰጠው ጉዳይ አይሆንም፡፡ የሀገራችን ገጽታ መበላሸትም አያስጨንቃቸውም፡፡ በርግጥም ጭንቅላታቸው በገንዘብ ተደፍኗልና በየወቅቱ በዜጎች ላይ የሚደርሱ አደጋዎች መንስዔዎቹ እነርሱ መሆናቸውን እያወቁ ለፀፀት ሲገባቸው “የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” እንደሚባለው በተቃራኒው ጉዳዩን ለማስተባበል ሲረባረቡ መታየታቸው ግለሰቦቹ ምን ያህል በአፍቅሮተ-ነዋይ እንደታወሩ የሚያመላክት ነው፡፡
ታዲያ የችግሩን መስፋትና አደገኝነት የተገነዘበው መንግስት የዜጎችን ከአደጋ ለመታደግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ቢጀምርም ጥረቱ የተፈለገውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም። የችግሩን አደገኛነት እንደ ፊልም ካልቆጠርነው በስተቀር በአንድ ወቅት በዕቃ ታንከር ውስጥ ታሽገው ህይወታቸውን ካጡት ዜጎቻችን በተጨማሪ በባህር ላይ ተጥለው የአሳ ነባሪ ሲሳይ ለመሆን የሚገደዱ ወገኖቻችንን ስቃይና እንግልት ከራሳቸው የስደት ሰለባ ከሆኑት ወገኖች አንደበት አርምጠናል።
እርግጥ ችግሩ የእያንዳንዳችንን በር እስኪያንኳኳ ድረስ መጠበቅ የለብንም። እናም ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ጉዳዩችን ማወቅ ይገባል። እነዚህ የችግሩ ተዋናዮች ግብ አንድና አንድ ነው። ገንዘብን በማንኛውም መንገድ አግኝቶ የተደላደለ ኑሮን መምራት፡፡ በቃ! ለእነርሱ የዜጎች ስቃይና ሞት ምናቸውም አይደለም፡፡ የመብታቸው፣ የደህንነታቸውና የክብራቸው ጉዳይም አያሳስባቸውም፡፡
ታዲያ እዚህ ላይ አንድ ዕውነታን ማንሳት ይገባል—የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ስለመሆኑ፡፡ ምክንያቱም ለስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠር መንግስትነት ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋን ለመከላከልም ከግንዛቤ ማስጨበጥ እስከ ተጨባጭ ርምጃዎችን መውሰድ ደረጃም ደርሷል። እንደሚታወቀው በመላ ሀገሪቱ በተዋረድ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል፡፡ በዚህም ህበረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሔው አካል እንዲሆን በየክልሉ በርካታ ተግባራት ዕውን ሆነዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀው ግብረ ሃይልም በሀገራቸውም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር በህጋዊ ተንቀሳቅሰው መስራት የሚፈልጉ ዜጎችን በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በማስገባት በተለያዩ የስራ መስኮች የአጭር ጊዜ ስልጠና መስጠት እንዲሁም ከሥልጠናው በኋላ በሰለጠኑበት ሙያ በሀገር ውስጥ በመደራጀት ወደ ሥራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ከስራ ጋር ለማስተሳሰር ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት ለሚፈልጉ ዜጎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ፣ ለስልጠና እና መሰል ስራዎች ድጋፍ የሚውል ሐብት ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ማዘጋጀትና ሃብት የማፈላለግ ተግባራት ገቢራዊ ሆነዋል። ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተከናወኑትን ተግባራት እንደ ምሳሌ ብንወስድ እንኳን፣ ከአረብ አገር ተመላሾችን በጊዜያዊነት በመንከባከብ እንዲረጋጉ ከማድረግም አልፎ ከስደት ተመላሾች የስነ ልቦና፣ የአመለካከትና የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙና ወደ ተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ተደርጓል።
ከዚህ ጎን ለጎንም በዚህ ትውልድን ለአደጋ በሚዳርግ ተግባር የተሰማሩ ደላሎች ላይ የህግ ማስከበር ስራዎችም ተከናውነዋል። በዚህም የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ቦታዎችን መለየት ችግራቸውን መሰረት አድርጎ በተመረጡ እንዲሁም ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች የመቆጣጠር ስራ ገቢራዊ ሆኗል።
በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ሀገር የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግም ህግን መሰረት አድርጎ ነው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ተችሏል። የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎችን የሚመለምሉና የሚያዘዋውሩ ደላላዎችን፣ ተባባሪና ቤት አከራዮችን እንዲሁም አጓጓዦችን መረጃ ማሰባሰብና በመለየት በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር የመፍጠር ርምጃዎችም ሲወሰድ ቆይቷል።
ይሁንና በመንግስት በኩል ችግሩን ለመቅረፍ ይህ ሁሉ ጥረት ቢደረግም፣ ችግሩ ግን አሁንም በበቂ ሁኔታ ተፈትቷል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የህገ ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎቹ ብዛትና ዓይነት፣ የመረቡ ውስብስብነት፣ የቤተሰብ ገፋፊነትን ጨምሮ ሁሉም ለችግሩ መስፋፋት የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ነው። በኢትዮጵያን ውስጥ ሰርቶ ማደግ እንደሚቻል ሁሉም ዜጋ ማወቅ አለበት። በተለይም ቤተሰብ ይህንን ሁኔታ የችግሩ ሰለባ ለሚሆኑ ልጆቹ ማስረዳት ይጠበቅበታል።