Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያና ግጭትን የማስወገድ ተግባሯ

0 384

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያና ግጭትን የማስወገድ ተግባሯ

ዳዊት ምትኩ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስወገድ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች ነው። በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከግጭት ነፃ ሆነው በኢኮኖሚ እንዲተሳሰሩ በመሰረተ ልማት፣ በኤሌክትሪክ ሃይል፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፎች የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል አድርጋ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።

መንግስት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ በቀጣናው ሀገራት መካከል ሰላም ሰፍኖ ልማታዊ ትስስር እንዲጎለብት ፈርጀ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ይህን ሲከውንም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ላይ በግልፅ እንዳስቀመጠው ሁለት መሰረታዊ ሁነቶችን ይከተላል—ውሰጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎችን።

መንግስት ሀገራዊ ህልውናን የማስጠበቁ ጉዳይ ሊሳካ የሚችለው ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች ላይ መሰረት በማድረግ ብቻ እንደሆነ በማመን ለተግባራዊነቱ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወቃል።  በመጀመሪያ ደረጃ በከፍተኛ ኋላ ቀርነትና የድህነት አዘቅት ተዘፍቃ ለቆየችው ሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ግንባታና ሰላምን የማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለመበታተን ተቃርባ የነበረችውን ሀገራችንን ለመታደግ የሚያስችል አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ወደ ተግባር የመሸጋገርን ግብ አስቀምጦ ገቢራዊ አድርጓል፡፡

የአካባቢያችን ሰላምና ልማት መረጋገጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለሀገራችን ፈጣን ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ቀጣይነት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ሁሉ፤ በአካባቢያችን የተረጋጋ ሰላምና ልማት ያለመኖርም በሀገራችን ልማታዊ ጉዞ መሰናክል መሆኑ አይቀሬ መሆኑን በመገንዘብ ለውጫዊ ሁኔታዎችም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው። መንግስት ለአደጋ ተጋላጭነታችን በምክንያትነት የሚጠቀሰውን ድህነትንና ኋላቀርነትን በመዋጋት ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆነበትን ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን እውን በማድረግ ላይ ያተኮረ የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቅረጽ ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል ህዝባዊ ንቅናቄን በመፍጠር ተግባራዊ ማድረግ የቻለውና ዛሬ ለምንገኝበት ደረጃ ላይ መድረስ የተቻለው፡፡ እንደሚታወቀው የቀደሙት መንግስታት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትኩረት ውጭውን የመመልከት አካሄድን የተከተለ ነበር፡፡

ይህ አካሄድም የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተስኖት ለከፍተኛ ድህነት ሊዳርገን እንደቻለም በአይናችን ያየነውና በጆሯችን የሰማነው ዕውነታ ነው፡፡ በተለይም ያለፋት መንግስታት የውጭ ፖሊሲ በውጭ ጠላቶች የመከበብ ስሜት ጐልቶ የሚታይበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በውጭ ተመልካችነት ላይ ተጠምዶ መቆየቱ፤ የሀገራችን ውስጣዊ ችግሮችና የአደጋ ተጋላጭነታችን እንዲጐለብት ከማድረግ ባሻገር በሀገራዊ ደህንነታችንና ህልውናችን ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ሲፈጥር መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

ታዲያ ይህን ጠንቅቆ የሚያውቀው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መንግስት ቀደምት መንግስታት ይከተሏቸው ከነበሩት ፖሊሲዎች የተለየና ለሀገራዊ ህልውናችን ወሳኝ በሆነው ውስጣዊ ችግሮች ላይ የሚያተኩር የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ መኖር አስፈላጊነቱ ከምንም በላይ መሆኑን ተገንዝቦ ትኩረት በመስጠት ተንቀሳቅሷል፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት ለሀገራችን ሰላምና ልማት  እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ጽኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ምርጫው ነው። ለምን ቢሉ የሀገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው።

ታዲያ በሀገራችን በመካሄድ ላይ ያለው የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የተጀመረው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀና ውጤቱም ለሀገራችንም ሆነ ለአካባቢያችን ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ መሆኑ የሚታበይ አይደለም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መንግስት ሀገራዊና አካባቢያዊ ሰላምን ከማስፈን አኳያ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በአካባቢያችንና በአህጉራችን ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የመጣው የኢትዮጵያ መንግስት ስኬቶች መካከልም ረጅም ኪሎ ሜትሮችን የምትዋሰነን በጎረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን ቀውስ ለማርገብ የተካሄደው ጥረትና የተመዘገበው አበረታች ውጤት ተጠቃሽ ነው፤ ዛሬ ሱዳን በአንፃራዊ ሰላም ውስጥ ናትና፡፡

ሱዳን በአፍሪካ ውስጥ በቆዳ ስፋቷ ቀዳሚ ሀገር ስትሆን ለጥ ያለና ውሃ ገብ የሆነው መልከዓ ምድሯ እንዲሁም ሰፊ የተፈጥሮ ሃብቷ ለታላቅ ዕድገት መብቃት የምትችል እንደሆነች ብዙዎቹን ያስማማ ሃቅ ቢሆንም ቅሉ፤ ሀገሪቱ ግን ለበርካታ ዓመታት በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ቆይታ ነበር። በዚህም ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቀውስ ልትዳረግ በመቻሏ ለተቀሰቀሰው አለመረጋጋት እልባት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

በጐረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት እልባት ከመስጠት አኳያ የአንበሳውን ድርሻ ከተወጡት የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል የነበረውን አለመግባባት በመፍታት፣ በዳርፉርና በአብዬ የተከሰቱ ችግሮችን በመቅረፍና የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በማሰማራት ሀገራችን የተጫወተችው ሚና እጅግ የላቀ ነው።

የኢፌደሪ መንግስት በጎረቤት ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት የሚመነጨው ሌሎች ሃይሎች እንደሚሉት ሳይሆን የጐረቤቶቻችን ሰላም ለሀገራቸን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን መፋጠን ካለው ፋይዳ አኳያ መሆኑ ለማንም የሚሰወር አይመስለኝም። ምክንያቱም እኛ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የምናደርገው ትግል ሊሳካ የሚችለው ጐረቤቶቻችን ሰላም ሲሆኑ እንደሆነ ይታወቃል።

በዚህ መርህ መሰረትም ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በህዝበ-ውሳኔ ከተለያዩ በኋላ ቀጣናውን የተቀላቀለችው አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን፤ ለነፃነቷ የታገለችውን ያህል ሰለሟን ማስጠበቅ አልቻለችም። በዚያች አዲስ ሀገር ውስጥ በተቀናቃኞች መካከል በየወቅቱ እየተከሰተ ያለው ችግር ህዝቦቿ ከነፃነታቸው ማግኘት የሚገባቸውን ትሩፋቶች እንዳያጣጥሙ እንቅፋት ፈጥሯል።

በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ዶክተር ሪክ ማቻር ሳቢያ እያሰለሱ የሚከሰቱት ግጭቶች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት የዳረጉና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ደግሞ የስደት ሰለባ ያደረጉ ናቸው። ይህ ደግሞ ሀገራችንን ጨምሮ ሰላም ወዳድ ኃይሎችን በአያሌው እያሳሰበ ነው።

አገራችንም እስካሁን ድረስ እያካሄደች የነበረውን ብርቱ ጥረት በተጠናከረ ሁኔታ የሚጠይቅ ነበር። ያም ቢሆን መንግስት ከመነሻው ጀምሮ ለደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን እስከ ዛሬ ድረስ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ይህን ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ሁኔታ ላይ የሚገኝ ይመስለኛል። እናም በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች አማካኝነት የተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት ተጥሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ቢቀጥፍም ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ከኢጋድ ጋር በመሆን ግጭቱን ለመፍታት ጥረት እያደረገች ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy