Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ሁለተኛው የልማት ዕቅድ

0 314

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ሁለተኛው የልማት ዕቅድ

ዳዊት ምትኩ

ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የኢትዮጵያ መገለጫ እየሆነ ነው። የውጭ ባለሃብቶችን ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እየሳበ ነው። መንግስትም የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ራሳቸውን ጠቅመው የሀገሪቱንም ኢኮኖሚ እንዲሳድጉ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። በራሱ ወጭ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባ ባለ ሃብቶችን እየጋበዘ ነው። ይህ ጥረት የሁለተኛው የልማት ዕቅድ መሰረት ነው።

እንደሚታወቀው የሀገራችን ኢንዱስትሪ በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለህዳሴ ጉዟችን ወሳኝ ትርጉም አለው። በመፈጠር ላይ ያለው ቀጣይና ተከታታይ ዕድገት ዘላቂ እንዲሆንና የህዳሴ ጉዟችንን መደላድል ለማስፋት በዕቅዱ ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርበታል። ይህም ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን ዕውን ለማድረግ የሚከናወነው ስራም ሀገራችን ለነደፈችው ራዕይ የሚጫወተው ሚና ሊተካ አይችልም። እንዲያውም የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል።

ይህ ዕውነታም የሀገር ውስጥና የውጭ ቀጥተኛ በአዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም ሆነ በነባር ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የምርታማነት የጥራትና የተወዳዳሪነት ደረጃ እመርታና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ በከፍተኛ ደረጃ መንቀሳቀስ እንዲቻል ያደርጋል። እናም በልማት ዕቅዱ ዘመን በኢኮኖሚው ላይ የሚታይ መዋቅራዊ ለውጥን ለማስጀመር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በየዓመቱ ቢያንስ የ24 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርበታል። ይህ ማለት በ2012 ዓ.ም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያለውን ድርሻ ወደ ስምንት በመቶ ከፍ እንዲል ያደርገዋል።

ይህ ለውጥም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ድርሻ በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት በአራት እጥፍ እንዲያድግ በማድረግ ወደ መጀመሪያው የመካከለኛ ጉዞ መንገድ ለመድረስ ለታለመው ዕቅድ እስከ 18 በመቶ የማድረስ ግብን ዕውን ይጥላል። ሀገራችን ለያዘችው የመካከለኛ ገቢ ራዕይን ለማሳካትም መደላድል ይፈጥራል። መዋቅራዊ ለውጡን ገቢራዊ በማድረግ ረገድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚናው ሁነኛ ማሳያ ነው። ዛሬን ከነገ ጋር ብናስተያየው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ከአስር በመቶ አይበልጥም።  ሆኖም ይህን አሃዝ በ2012 ዓ.ም ላይ ወደ 25 በመቶ ከፍ ለማድረግ ታስቧል— አምስት ቢልዮን ዶላር ገቢ እንዲያስገኝ ለማድረግ በማሰብ። የዚህ ድምር ውጤትም ወደ መካከለኛ ገቢ እናመራለን ብለን ባሰብንበት በ2017 ዓ.ም 40 በመቶ እንዲደርስ ትልም ተይዟል። እርግጥ ይህ ዕቅድ ግዙፍና ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ሆኖም በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እንዳሉት፤ ዕቅዶች ወገባችንን የሚያጎብጡን ቢሆኑም እንኳን ጠንክረን ከሰራን የማናሳካበት ምክንያት ሊኖር የሚችል አይመስለኝም።

እናም በጠንካራ ስራ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት ይቻላል። ለዚህም አሁንም የተነሳሁበትን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍን ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል። ይኸውም በዘርፉ የሚደረገው የሰው ኃይል ሽግሽግ ሁነኛ ተጠቃሽ ነው። አሁን ባለው አሃዝ መሰረት በመካከለኛና በከፍተኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የተሰማራው የሰው ኃይል ከ350 ሺህ የሚበልጥ አይደለም።

ታዲያ በሁለተኛው ‘ዕትዕ’ እና ከእርሱም ቀጥሎ ባሉት አምስት ዓመታት (በድምሩ በቀጣዩቹ አስር ዓመታት) አሃዙን በአራት እጥፍ ለማሳደግና አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማድረግ ውጥን ተይዟል። ከዚህ ውስጥ የሁለተኛው ‘ዕትዕ’ ድርሻ የተያዘውን የአስር ዓመት ዕቅድ በግማሽ ማሳካት ነው። ይህም ወደ 750 ሺህ ዜጎች በዘርፉ እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠርን ያጠቃልላል። ይህ ዕውን ከሆነም አሁን ያለውን የሰው ኃይል ሽግሽግ በእጥፍ ማሳደግ የሚቻል ይመስለኛል።

ታዲያ ይህን ውጥን ዕውን ለማድረግ ርብርብ ማድረጉ አጠያያቂ አይሆንም—በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በማሳተፍና በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ የዕቅዱን ገቢራዊነት ማረጋገጥ መቻሉ አጠያያቂ የኒሆን አይመስለኝም። እርግጥ መንግስት የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከወዲሁ እያከናወና ያለውና በዕቅድ ደረጃ የያዛቸው የተለያያዩ የተጠቃሚነት ማዕቀፎች ሃቁን የሚያሳዩ በመሆናቸው በቀሪው የልማት ዕቅዱ ዘመን ተጠናክረው ከቀጠሉ ስኬቱን ማረጋገጥ ይቻላል።

እርግጥ በዕቅዱ ላይ በዘርፉ የተጠቀሱትን ስኬቶች እውን ለማድረግ በሁለት ዘርፎች ትልሞች ተይዘዋል—በጥቃቅንና አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ትኩረት ለመስጠት። ይህ ሁኔታም በሁለቱም ዘርፎች ውስጥ ኤክስፖርት መር የኢንዱስትሪ አቅጣጫን ለመከተልና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ በሚደረገው ሽግግር ውሰጥ የራሱን ሚና ይጫወታል።  

እንደሚታወቀው በሀገራችን ውስጥ ያለው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሰረቱ ይህን ያህል የሚያስመካ አይደለም—ጠባብ ነው። ያም ሆኖ ግን ሀገራችን በዘርፉ ለውጥ እንድታመጣ በዋነኛነት ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ይኖርባታል። በተለይም በማደግ ላይ የሚገኘው የሀገራችን ባለሃብት የለውጡ ተሳታፊ እንዲሆን እንዲሁም በተመረጡ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ተግባሩ እንዲከናወን ማድረግ ያስፈልጋል።

እናም ከሀገር ውስጡ ባለሃብት በተጨማሪ የውጭ ባለሃብቶች በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚኖራቸው የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተሳታፊነት የማይናቅ ቦታ ይኖረዋል። ይህም የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን ጉልህ ሚና አለው።

ይህን መሰረታዊ ዕውነታ በመመርኮዝም በዕቅድ ዘመኑ በሁሉም ዘርፎች ጥንቃቄ በተሞላው ሁኔታ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ብርቱ ጥረት ይደረጋል። በተለይም  ከፍተኛ አቅምና ፍላጎት እንዲሁም በአፈፃፀማቸው ጥሩ ስምና ዝና ያላቸውን የውጭ ኩባንያዎች በመመልመልና የማግባባት ስራ በማከናወን የዘርፉን ዕድገት እንዲያሳድጉት ማድረግ እንዲገባ ተጠቅሷል።  

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንጂ ለብቻው ተፈፃሚ እንዲሆን ብቻ አይደለም። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን ዕውን ከማድረግ አኳያ መቆራኘት ይኖርበታል። ይህን ዕውን ለማድረግም በአሁኑ ወቅት ያሉትም ይሁኑ በቀጣይ ወደ ስራ የሚገቡት ኢንዱስትሪዎች፤ የቴክኖሎጂ አቅማቸውን፣ ምርታማነታቸውን፣ የጥራት አመራር አቅማቸውን ብሎም ተወዳዳሪነታቸውን በቀጣይነት መገንባት ይችሉ ዘንድ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግላቸዋል።  

ከዚህ ጎን ለጎንም የሳይንስ፣ የቴክኖሎጅና የኢኖቬሽን አቅምን ለማሳደግ ከሀገሪቱ የዕድገት ፍላጐት ጋር የተጣጣመ የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማድረግ በዕቅዱ ላይ ተቀምጧል። ይህን ለማከናወንም በተለይ ለሀገር ውስጥ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።

ስለሆነም በዘርፉ እስካሁን ድረስ የተደራጁ የኢንዱስትሪ ልማት ደጋፊ ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች አቅማቸው ይበልጥ እንዲጎለብትና ጥራት ባለው የትምህርት ማሳለጫዎች እንዲደጉ ይደረጋል። ከውጭ መሰል ተቋማት ጋር የሚኖራቸው ቁርኝትና እንዲጠናከር አሰራራቸውም እንዲዘምን ለማድረግ ታስቧል።

በመሆኑም ተስማሚና የተሻሻሉ ቴክኖሎጅዎችን የማፈላለግ፣ የመምረጥ፣ የማለማመድና የመጠቀም ብሎም የማሻሻል ስራዎችን በማከናወን የዘርፉን ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል። እናም ጥራትን፣ ምርታማነትን እንዲሁም ተወዳዳሪነትን ለማጐልበት ሀገራችን የመረጠችው የካይዘን የአመራር ፍልስፍና በሁሉም ዓይነት ኢንዱስትሪዎችናየኤክስፖርት ዘርፎች በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን ገቢራዊ ይሆናል።

በአጠቃላይ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ቀጣይነት እንዲረጋገጥ ኢንቨስትመንት መኖር ይኖርበታል። ኢንቨስትመንቱም ኤክስፖርትን ሊደግፍ ይገባል። ኢንዱስትሪው ኤክስፖርት ተኮር መሆን ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy