Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እኛም በጠብታ ድጋፋችን

0 312

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እኛም በጠብታ ድጋፋችን ታላቁ ግድባችንን…

አባ መላኩ

“ጋን በጠጠር ይደገፋል” እንደሚባለው አገራችን እየገነባች ያለችው ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት  እያንዳንዳችን  ባደረግናት  ጠብታ ድጋፍ ወደ ስኬት ተቃርቧል። ትብብር ወደ ስኬት እንደሚያደርስ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጥሩ ማሳያ ነው። የኢፌዴሪ መንግስት የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዕቅድ ይፋ ሲያደርግ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች “የኢትዮጵያ መንግስት ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር እውነትም በራሱ ወጪ ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት   ሊተገብረው አይችልም”  የሚሉ አስተያየቶች ሲሰነዝሩ  ነበር።

 

እነዚህ አስተያየቶች በእርግጥም  እውነታነት ነበራቸው። ምክንያቱም እንዲህ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት መተግበር ኢኮኖሚያዊ አቅምን የሚጠይቅ ብቻ  ሳይሆን ልምድንም ጭምር  የሚሻ ፕሮጀክት ነው። እንደኢትዮጵያ ላለ ታዳጊ አገር  እንዲህ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት መተግበር ከባድ ነው የሚል አስተያየቶች  ቢሰነዘሩ  የሚያስገርም አይደለም። ይሁንና አሁን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ይህን ታላቅ ፕሮጀክት ዕውን ለማደረግ በመቃረብ ላይ ናቸው።  

 

ከአፍሪካ አንድነት ምስረታ እስካሁን ድረስ  የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለአፍሪካ ነጻነት፣ አንድነትና ህብረት እስትንፋስ ነች። ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን መጠጊያ መሸሸጊያ ነች። ምዕራባዊያን  በተለይ አውሮፓዊያን ለስደተኞች በራቸውን በዘጉበት በአሁኑ ወቅት እንኳን  ኢትዮጵያ ከ850 ሺህ በላይ አፍሪካዊያን ስደተኞችን መጠጊያ ሆናለች። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ በመጀመሯ ለአፍሪካ አገራት በፖለቲካው ረገድ የነበራትን አጋርተኝነት በኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር በመስራት ላይ ነች። በኢኮኖሚው ትስስር ረገድ እያከናወነው ከሚገኘው በርካታ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ተጠቃሽ ነው።

መንግስት ይህ ግድብ መገንባት የጀመረው በዋነኝነት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰጠውን  ጥቅም ታሳቢ ቢደረግም የጎረቤት አገሮችም በተለይ የሃብቱ ቀጥታ ተጋሪ የሆኑት ሱዳንና ግብፅ የሚያገኙትን ጠቀሜታም ከግምት እንዲገባ በማድረግ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የሚገነባቸው ፕሮጀክቶች በጎረቤት አገራት ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ በተቻለ መጠን ተገቢው ጥናት አካሂዷል።

 

እስካሁን ባለው ሁኔታ የትኛውም የተፋሰስ አገራት እስካሁን አድርገውት በማያውቁት ሁኔታ የዓለም ዓቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ፕሮጀክቱን እንዲገመግሙ አድርጓል። ይህ በራሱ የሚያሳየው የኢትዮጵያ መንግስት በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ያለውን መተማመን ነው።  እውነት እንነጋገር ከተባለ  ግብጽም ሆነች ሱዳን በአባይ ላይ በርካታ ፕሮጀክቶችን ሲያከናውኑ ለላይኞቹ የተፋሰስ አገራት  ፕሮጀክቶቻቸውን ማስገምገም ይቅርና  አሳውቀው አያውቁም። ኢትዮጵያ ግን በሶስተኛ አካል ፕሮጀክቷን  አስገምግማለች።  ይህ የሚያመላክተው መንግስት የሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የአካባቢ አገራትን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ  መሆኑን  ነው።  

 

ግብፃዊያን በአባይ ወንዝ ላይ ሙሉ ለሙሉ ጥገኛ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት  ከግምት በማስገባት የተፋሰሱ አገራት የጋረ  ሃብት  የሆነው  የአባይን  ውሃ   “እኩል ተጠቃሚነት”  የሚል መርህ  ሳይሆን   “ፍትሃዊ ተጠቃሚነት” የሚል መርህን በመከተል ህዝባዊነቱን አሳይቷል።ኢትዮጵያ የጀመረችውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠል የሚቻለውና ኢኮኖሚው የመዋቅር ሽግግር ሊያደርግ የሚችለው የሃይል አቅርቦቷን ከ25-30 በመቶ ማሳደግ ስትችል ብቻ መሆኑን አሳይቷል።       

 

የኢትዮጰያ  መንግስት እያለ ያለው  ግብጻዊያን ወንድሞቻችን እናንተ ሳተጎዱ በድህነት የኖረው ኢትጵያዊ ወንድሞቻችሁም  የኤሌክትሪክ  ሃይል  እናግኝ የሚል  ነው። ይሁንና የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለግብፃዊያን ወንድሞቹ እንዳሰበላቸው ከእነሱ በኩል ቅን ምላሽ አልተሰጠም።  ከአንዳንድ  የግብጽ ፖለቲከኞችና ምሁራኖች የተቸረው ምላሽ እጅግ ኋላ ቀርና በየትኛውም መስፈርት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተቀባይነት የሌለው “ጠብታ ውሃ በጠብታ ደማችን ይተካል’’ የሚል  ነበር። ዘግይተውም ቢሆን ግብጻዊያን ፖለቲከኞች ይህ ፉከራ እንደማያዋጣ  ተረድተውት ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጋር ተቀራርበው መስራትን መርጠዋል። ይህ የመንግስታችን የዲፕሎማሲ ስኬት ነው።

 

እንደእኔ አስተያየት  ያን የመሰለው ቅጥ ያጣ የግብጻዊያን አስተያየት  የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ  ደም ውስጥ እንዲሰርጽ  አድርጎታል። ታላቁ ግድባችን የእንችላለን ስሜት በዜጋው ውስጥ እንዲጎለብት እንዲሁም ህዝብና መንግስትን የበለጠ እንዲተሳሰሩ  አድርጓቸዋል። አሁን ላይ  ኢትዮጵያዊያን በጠብታ ድጋፋችን ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ  እውን ወደማድረግ እየተቃረብን ነው። በእርግጠኝነት ታላቁ ግድባችን በእያንዳንዳችን ልቦና ውስጥ ትልቅ ስፍራ አለው። ምክንያቱም በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር  ኢትዮጵያዊያን ይህን ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ተግባራዊ አያደርጉትም ሲሉ በአደባባይ ሲናገሩ ነበር። ይሁንና አሁን ላይ በተግባር ለዓለም አሳይተናል። እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት በመቻላችን ይህን የባለብዙ ቢሊዪን ዶላር ፕሮጀክት በራሳችን አቅም እውን ለማድረግ በመቃረብ ላይ ነን።  

 

የኢትዮጵያ መንግስት በሚከተለው  ግልጽ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሳቢያ በቀንዱ ብቻ ሳይሆን በመላ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የተቸቻለውን ነገር ሁሉ አድርጓል፤ በማድረግም ላይ ይገኛል። በተባበሩት መንግስታት  ጥላ ስር ከሚንቀሳቀሱ የሰላም ማስከበር ሰራዊት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በቀዳሚነት እንዲሁም  ከዓለም ደግሞ በአራተኝነት ደረጃ ላይ  ትገኛለች።  የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ከትላንት እስከዛሬ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት የፈጸሟቸው ገድሎች እውቅና ተችሯቸው የቀድሞ መሪዎቹ ሃውልት በህብረቱ ጊቢ እንዲቆሙ ወስኗል። ይህ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት  ትልቅ ስኬት ነው።

  

ከዓባይ 85 በመቶ በላይ የሆነውን ውሃ መገኛ የሆነችው አገራችን  ከወንዙ አንድም ጥቅም ሳታገኝ ለዘመናት ቆይታለች። ኢትዮጵያ አባይ የተፋሰሱ አገራት የጋራ ሃብት ነው። ይሁንና ግብጻዊያን ፖለቲከኞች አባይ የግብጻዊያን ንብረት ብቻ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲያውጁ በመኖራቸው ሳቢያ በግብጻዊያን  መካከል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲፈጣር ምክንያት ሆኗል። ኢትዮጵያ ለዘመናት ከወንዙ ጠቀሜታ ባለማግኘቷ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በተፋሰሱ አካባቢ አከናውና አታውቅም። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ላይ እየተከሰተ ያለው የአየር ንብረት ቀውስ ሳቢያ በላይኞቹ የተፋሰስ አገራት ጠንካራና ዘለቄታዊነት ያለው የአካባቢ ጥበቃ ካልተከናወነ በስተቀር የወንዙ ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አመልክተዋል። ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ተጠናክሮ በመሰራት ላይ ነው። ይህ ደግሞ ለዓባይ ዘላቂ ህይወት ትልቅ ዋስትና ነው።

 

ግብፃውያን ፖለቲከኞች ዛሬም አገራችንን በድሮው ሚዛናቸው  በመመዘን ኢትዮጵያን የመሰለ ድሃና ኋላ ቀር አገር እንዲህ ያለ ግዙፍ ግድብ ምን ያደርግላታል በማለት የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት አሳንሰው ሲናገሩ ተደምጠው ነበር። እውነታው ግን ይህ አይደለም። የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ትክክለኛ ገጽታ ግብፃዊያን መሪዎችና ሊሂቃን ሊቀበሉት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በተግባር አሳይተወዋቸዋል።  

 

ኢትዮጵያ ድሮ እንደሚያስቧት ደካማ፣ ይህን አድርጊ ይበጅሻል፣ ይህ ደግሞ አይጠቅምሽም ይቅርብሽ እየተባለች እንደ አሻንጉሊት የምትበጃጅ አገር አይደለችም። አዲሲቷ ኢትዮጵያ ጠንካራ አቋም ያላት በህዝቦቿና ለህዝቦቿ ውሳኔ ብቻ የምትገዛ አገር ናት። እኛ ኢትዮጵያዊያን  የሚያዋጣንንና የማያዋጣንን በራሳችን መለየት የምንችልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። የጀመርነውን የህዳሴ ግድብ በራሳችን የውስጥ አቅም ልንጨርሰው እንደምንችል ለዓለም አረጋግጠናል።

 

በአገራችን ታሪክ እስካሁን ከታዩ የልማት ፕሮጀክቶች እንደ ህዳሴው ግድብ ያለ  የህዝብን ቀልብ የገዛና የሁሉም ህዝቦች አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት አልታየም። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ  የአገራችንን ገጽታ የሚቀይር በህዝቦች መካከል “የይቻላል” ስሜት የፈጠረ  ፕሮጀክት በመሆኑ የልማት ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች የትብብርና አንድነት ማሳያ ነው። ይህን የአገራችን መለያ የሆነ ፕሮጀክት እስካሁን እንዳደረግነው ሁሉ  ነገም ድጋገፋችንን አጠናክረን በመቀጠል ከዳር ማድረስ ይገባናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy