Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከህገወጥ ነጋዴው አስቀድሞ ህገወጥ ባለስልጣናቱን ማጥመድ ያስፈልጋል

0 472

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከህገወጥ ነጋዴው አስቀድሞ ህገወጥ ባለስልጣናቱን

ማጥመድ ያስፈልጋል

 

ስሜነህ

 

መንግስት የትናንት፣ የዛሬን እና የነገን ትውልድ ሀላፊነት ተሸክሞ እየሰራ መሆኑ እሙን ነው። መንግስት ትናንት የነበረውን ያልተወራረደ የህዝቦች የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እርብርብ እያደረገ መሆኑም በተመሳሳይ። በእስካሁኑ ሂደት ተጨባጭ ለውጦች የመጡ ቢሆንም  እድገታችን ያስከተላቸውን የህዝቦችን ተጨማሪ ፍላጎቶች ከመመለስ  አኳያ ግን ግና ብዙ ርቀት መሄድ የሚገባው እንደሆነም አያከራክርም። መከራከር ከተገባ የጉዞው መሰረት ምንድነው? በሚለው ጉዳይ ላይ ይሆናል። በረዥሙ ጉዞ  ስኬታማ ለመሆን ትልቅ የፋይናንስ አቅም ያስፈልጋል ።  

 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 30፣ 2009 ዓ/ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለ2010 በጀት 320 ቢሊየን ብር እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል። ለ2010 በጀት ዓመት የጸደቀው 320 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በጀት ከ2009 ጋር ሲነጻጸር የ9 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ አለው። ይህም ሊሆን የቻለው የህዝቡ ፍላጎት እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ መሆኑ አያከራክርም። ለ2010 ከተያዘው 320.8 ቢሊየን ብር በጀት ውስጥ 196 ቢሊየን ብሩን  ለመሸፈን የታቀደው ደግሞ ከግብር በሚሰበሰብ ገቢ ነው። ይሁን እንጂ በባለፈው በጀት ዓመት ከታየው የግብር ገቢ አሰባሰብ ክፍተት አንጻር፣ 196 ቢሊየን ብር የመሰብሰቡም ነገር አጠራጣሪ ነው። ከወር በፊት በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት ከግብር ገቢ 171 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ቢታቀድም፣ 120 ቢሊየን ብር ብቻ መሰብሰቡ ለዚህ በአስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል።

 

የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በዚያው ሰሞን ከነዋሪዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ በበጀትና በግብር አሰባሰብ ጉዳዮች ዙሪያ ባካሄደው ስብሰባ፣ እስካሁን ያለው የግብር አሰባሰብ ካልተስተካከለ ለ2010 የተመደበውን ባጀት ማሟላት አዳጋች እንደሚሆን ማሳወቁም ስለዚህ ነው። ባጠቃላይ የሃገሪቱ ግብር የመሰብሰብ አቅም አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ከነዚሁ የስጋት ጠቋሚ አስረጂዎች መገንዘብ ይቻላል።  

 

ስለሆነም እየሰፋ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት ለመመለስ  የታክስ መሰረቱን ማስፋት፣ ሁሉም ገቢ አመንጪዎች በግብር መረብ ውስጥ እንዲታቀፉ ማድረግ፣ ግብር የመክፈል አመለካካት እንዲጎለብት ማድረግ . . . ያሰፈልጋል።  

 

ያም ሆኖ ግን ዛሬም የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ የሚያስችል አላማ ያለውን የቀን ገቢ ግምት ጽንፈኛው ሃይል አጣሞ ለአመጽ እንቅስቃሴው እያመቻመቸው ነው። ለዚህ ደግሞ የአገራችን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ሁኔታ ምቹ ሁኔታን የፈጠረለት ይመስላል። የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት አሁንም የበላይነቱን ባስጠበቀበት ተጨባጭ ሁኔታ ኪራይ ሰብሳቢው ነጋዴ ግብርን በመቃወም ሥም ዕቃዎችን ያለአግባብ በመጋዘኖች በማከማቸት አሊያም ህዝባዊ አገልግሎትን በማቋረጥ ሆን ብሎ የገበያ እጥረትን የመፍጠር አዝማሚያዎች እያሳየ ነው።  ዋጋ በማስወደድ የራሱን ህገወጥ ትርፍ ለማጋበስ ሲሞክር በሌላ በኩል የጸረ ሰላም ሃይሉ መጠቀሚያ በመሆን ልማታዊው ነጋዴውም ጭምር የግብር ትመናን እንዲቃወም በማስተባበር፣ ቀጥሎም በምርትና አገልግሎት እጥረት ሳቢያ ህዝቡን በማስመረር ለአመጽ ለማነሳሳት፣ ካልተሳካለትም ህዝብን አግቶ ከመንግስት ጋር ለመደራደር የመሞከር ያህል እየተፍጨረጨረ ነው፡፡

 

በእርግጥ የገቢ ግብር ትመና የሚሰላው በግምት ላይ ተመስርቶ እንደመሆኑ ስህተት ሊኖር እንደሚችል አያጠያይቅም። ሆኖም ለዚሁ ሲባል የተዘረጋ የቅሬታ አፈታት ስርዓት ተዘርግቷል።  ቅሬታን መፍታት የሚቻለው ደግሞ በሕግ አግባብ ብቻ ነው።  

 

አዲሱ የቀን ገቢ ግምት ዓላማ ነጋዴው በሚያገኘው ገቢ ልክ የመንግስትን ግብር እንዲከፍል ማስቻልና ህገወጡን ወደህግ መመለስ ብቻ ነው። በዚሁ መሰረት በርካታ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ መስመር ማስገባት የተቻለ መሆኑን የተመለከቱ መረጃዎች እየወጡ ነው። ለአብነትም በሦስት ክልሎች ብቻ ከ100ሺህ በላይ ግብር የማይከፍሉ የነበሩ ነጋዴዎችን ለመለየት ማስቻሉ፤ ሕጋዊ ነጋዴዎች ለዓመታት ሲያቀርቡት የነበረውን ሮሮ የመለሰ እና ሮሮውም ትክክል የነበረ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

 

ከዚህ አኳያ ፀረ-ሰላም ኃይሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምን፣ የግብር ትመናንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች መሰረት አድርጎ እያካሄደው ያለውን እንቅስቃሴ ስናሰላ ዋነኛ ዓላማው ህዝብን ለአመጽ ተግባር መቀስቀስ ነው። ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያ ረድፍ ተሰላፊ ሊሆን ይችላል በሚል በወጣቱ ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል፡፡ የሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች የቱን ያህል የህዝብን ጉዳዮች የሚመለከቱ ቢሆንም ቅስቀሳው ሕዝብን ለአመጽ በሚጋብዝ መልኩ በተለይም ወጣቱን ግንባር ቀደም የጥፋት ሃይል አድርጎ ለማሰማራት አቅዶበት እየሰራ ነው።

 

የመንግስት ፍላጎት ደግሞ ከላይ ለተመለከተው የህዝቦች ፍላጎት ሲል የግብር አድማሱን ማስፋት ሲሆን ይህንን ለማከናወንም ነጋዴውን ማማረር ሳይሆን ሁሉንም ነጋዴ ወደ አሰራሩ በማስገባት በህግ የሚሄደውን ግብር ከፋይ ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማትን ማፋጠን ነው።

 

በየቀኑ ብዙ ገንዘብ እያንቀሳቀሱ ግብርን አለመክፈል የሞራል ውድቀት ነው። በጥቃቅን ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ እና ገቢያቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑ ነጋዴዎች ራሳቸው ባመኑት የቀን ገቢ ግምት ልክ ግብር እንዲከፍሉ ቢደረግም በግብር ስርዓቱ ውስጥ መታቀፋቸው በራሱ ትልቅ ፋይዳ ነው ያለው። የመንግስት ትኩረት ከነጋዴው ጋር የተፈጠረውን ቅሬታ በውይይትና በመግባባት መፍታት ላይ ነው። ከመግባባት ላይ ካልተደረሰም የቅሬታ አፈታት ስርዓት ተዘርግቷል። ያም ሆኖ ግን ከመንግስት በኩል የሚቀር መሰረታዊ ጉዳይ አሁንም አለ። ይኸውም ከግብር የተገኘ ሃብትን ስለምን ባክኖ እንደቀረ ዛሬም ለግብር ከፋዩ ህዝብ ምላሽ ያልተሰጠ ሞሆኑን የተመለከተው ነው።

 

ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትን እንደገና ለማቋቋም በወጣው የአዋጅ ቁጥር 982/2008 መሰርት በመንግስት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ መስሪያ ቤቶች ላይ ኦዲት ያደርጋል። የኦዲት ግኝት ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል፤ የዚህ ዋነኛ አላማም በመንግስት ፋይናንስ አሰራር ላይ ተጠያቂነት፣ ግልፅነትንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሲሆን፤ የኦዲት ሪፖርት መቅረብ በመንግስት ፋይናንስ አሰራር የገንዘብ አጠቃቀምና ንብረት አያያዝ ምን አንደሚመስል ከማስገንዘብ ባሻገር ክፍተቶች ካሉ በቀጣይ ሊወሰዱ ስለሚችሉ እርምቶች መፍትሄ ለማበጀት አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡

 

በህገ መንግስቱ ድንጋጌ መሰረት የመንግስት ተቋማት የኦዲት ግኝት ለሕዝብ ግልፅ እንዲሆን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን  እንዲዘግቡት ተደርጎ ለህዝብ ተደራሽ ይሆናል፡፡ ቀጣይ ተግባር የሚሆነው ጥፋተኞችን ተጠያቂ ማድረግ ነው፡፡ ተጠያቂነትን ለማምጣት የተቀመጡ የህግ ማዕቀፎች አሉ፡፡ አንዱ የፌዴራል ዋና ኦዲተርን ስልጣንና ተግባር የሚደነግገው የአዋጁ አንቀፅ 5 ንዑስ አንቀፅ 6 ነው፡፡ የዋና ኦዲተሩ የምርመራ ውጤት ወንጀል መፈፀሙን የሚያሳይ ሆኖ ሲገኝ ለሚመለከተው አካል ወዲያውኑ እንዲያሳውቅ ድንጋጌው ያስገድዳል፡፡ የሚመለከተው አካል የሚባሉትም በአዋጁ አንቀፅ 20 ንዑስ አንቀፅ 2 መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የጠቅላይ አቃቤ ህግና የኦዲት ተደራጊው መስሪያ ቤት ወይም ድርጅት የበላይ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ ሌላኛው የህግ ማዕቀፍ አንቀፅ 17 ንዑስ አንቀፅ 3 ነው፡፡ ይህ ንዑስ አንቀፅ ተመርማሪ መስሪያ ቤቶች በፌዴራል ዋና ኦዲተር በተላኩ ሪፖርቶች በተገለፁ ግኝቶች ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ በተሰጡ የማሻሻያ ሃሳቦችና አስተያየቶች መሰረት ከ15 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እርምጃ እንዲወስዱ ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡

 

ባሳለፍነው በጀት አመት ከሂሳብ ጉድለት እስካልተወራረደ ሂሳብ ፤ ካልተገባ ግዥ እስከ ተበላሸ ጨረታ ወዘተ የተመለከቱ የዋናው ኦዲተር በቢሊዮኖች የሚቆጠር የብክነት ግኝቶች ተጠያቂ መሆን ያለባቸው አካላት በሙሉ ሲጠየቁ ሳናይ 15 ቀን አይደለም ወራት መቆጠሩ በግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ቀላል እንዳልሆነ መንግስት ሊገነዘብ ይገባል። የማንንም ኪስ ለማደለብ እና የማንንም ኑሮ ለማሞቅ ስል ስለምን ግብር እከፍላለሁ? የሚለው አስተሳሰብ የበላይ እንዳይሆን መጠንቀቅም ያስፈልጋል። ዛሬ የመንግስት ባለስልጣናትን ኑሮ ለመመልከት የትም መሄድ ሳያስፈልግ ውድ የተባሉ መሸታ ቤቶችን የሚያጣብቡ ልጆቻቸውን መመልከት በቂ ነው። ማስረጃና መረጃ አጣሁኝ የሚል አካል ሌላ ቦታ ሳይሄድ የ7ሺህ ብር ደሞዝተኛው ባለስልጣን ጎረምሳ 10 ሺህ ብር በደቂቃዎች ውስጥ ቀርጥፎ ሲበላ መመልከት ይችላል። ስለሆነም አለኝ ከሚለው ላይ ግብር ከፋይ የሆነው ህዝብ ይህን ሲመለከት ተስፋ ያጣል፤ ተነሳሽነቱ ይከስማል። ስለሆነም ህገወጥ ነጋዴውን ወደህጋዊው መረብ ለማስገባት ሲታሰብ ህገወጥ ባለስልጣናትን አስቀድሞ ወደህጋዊው መረብ በማስገባት ይሆናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy