ከስደት ተመላሾቹ
ደስታ ኃይሉ
ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ ስደተኞች እዚህ አገር ውስጥ በርትተው ከሰሩ ራሳቸውን ጠቅመው አገራቸውንም መጥቀም ይችላሉ። ሆኖም በተለያዩ ወቅቶች “እንዲህ ይደረግላችኋል፣ እዚህ ቦታ ትቀጠራላችሁ…ወዘተ” የሚል ቃል ተገብቶልናል የሚሉ ጉዳዩችን ሲያሰሙ ይደመጣሉ። ሆኖም እዚህ ላይ ከስደት ተመላሽ ዜጎቻችን መንግስት ለሌላው ዜጋ የሚያደርገውን ነገር ለእነርሱም ከማድረግ ውጪ የተለየ ነገርን የሚያደርግ አይመስለኝም።
እንደሚታወቀው መንግስት ዜጎች ሰነዶቻቸውን እንዲያገኙ በሳዑዲ የተለያዩ ጽህፈት ቤቶችን ከፍቶ በመንቀሳቀሱና ሌሎች ህዝባዊ ተግባራትን በመፈፀሙ፣ እስካሁን ድረስ ከ50 ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች የምህረት አዋጁን ተጠቅመው ወደ ሀገራቸው ገብተዋል።
ምንም እንኳን ህገ ወጥ ደላላዎች ‘የሳዑዲ መንግስት ምንም አያደርጋችሁም’ በማለት የተሳሳተ ወሬ በስደተኞቹ መካከል እየነዙ ቢሆንም፤ ሃቁ ግን ጊዜው ሲደርስ በህገ ወጥ ዜጎች ላይ ስለሚወሰደው ርምጃ የሪያድ የፀጥታ ክፍሎች እየተወያዩበት ነው።
ይህም ልክ ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት የሪያድ መንግስት እንዳደረገው ህገ ወጦች ብሎ የፈረጃቸው ዜጎችን ንብረት በመውረስና በማንገላታት ጭምር ከሀገሩ እንደማያባርር ማንም ዋስትና ሊሰጥ የሚችል አይመስለኝም—የየትኛውም ሀገር መንግስት በህገ ወጥ ስደተኞች ላይ ስለሚወስዳቸው ማናቸውም ርምጃዎች ወሳኙ እርሱ ብቻ ስለሆነ ነውና።
ታዲያ ህገ ወጥ ደላላዎቹ ይህን የተሳሳተ ወሬ እየነዙ የሚገኙት ባለማወቅ ለእነርሱ አሁንም ገንዘብ ከፍለው የሚሄዱት ወገኖች እንዳይቀሩባቸው በመስጋት መሆኑን ሰነዱን ያልወሰዱት ዜጎች ሊያውቁ የሚገባ ይመስለኛል። ህገ ወጥ ደላለዎቹ የሳዑዲ መንግስት ከሚወስዳቸው ርምጃዎች ሊያስጥሏቸው አይችሉም።
በአሁኑ ወቅት በህገ ወጥነት በሳዑዲ ውስጥ የሚገኙት ዜጎች ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ፍላጎት ካላቸው በህጋዊ መንገድ ወደዚያው ማቅናት ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ በአዋጅ የተደገፈ ህጋዊ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየሆነ ነው። ዜጎች በህጋዊ መንገድ ተገቢውን ስልጠና ወስደው ወደ ሳዑዲ እንዲሄዱ የሚያስችል ስምምነትም በመንግስት ጥረት ከዚያች ሀገር ጋር ተፈርሟል።
እናም ይህን መፃዒ ዕድል ለመጠቀም በዚያች ሀገር የሚገኙት ዜጎች በቅድሚያ ወደ ሀገር ቤት መምጣት ይኖርባቸዋል። ይህ ወርቃማ ዕድል ሊያመልጣቸው የሚገባ አይመስለኝም። በውድሚያ ግን ወደ ሀገራቸው መምጣት ይኖርባቸዋል። ለሁለተኛ ጊዜ የሳዑዲ መንግስት ለአንድ ወር የሰጠውን የምህረት ጊዜ በተገቢው ሁኔታ መጠቀም አለባቸው።
ይህ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት ወደ ሀገራቸው ለሙመለሱ ስደተኞች ድጋፍ ያደርጋል። ድጋፉ ግን እዚህ ሀገር ውስጥ ለሌሎች ዜጎች ከሚደረገው የተለየ የሚሆን አይመስለኝም። መንግስት ሁሌም ቢሆን አቅም በፈቀደ መጠን ለዜጎቹ ድጋፍ ያደርጋል። ስደተኞቹ ወደ ሀገር ቤት ከመጡ በኋላም እንደ ማንኛውም ዜጋ በሀገሪቱ ውስጥ እየተሳለጠ በሚገኘው የልማት ስራዎች ውስጥ በአቅማቸው ሊሳተፉ ይችላሉ። በቂ ጥሪት ያላቸውም ሀገራቸው ውስጥ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት መስክ በግልም ይሁን በጥምረት ተሳትፎ ሊያደርጉ ይችላሉ።
ይህ ሀገር በዕድገት ላይ የሚገኝ በመሆኑም ሁሉም ዜጋ በየደረጃው በልማቱ ላይ እንደሚያደርገው አስተዋፅኦ ተጠቃሚ እንደሚሆነው ሁሉ፤ እነርሱም በልማቱ ላይ በሚጫወቱት ሚና ልክ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
እናም መንግስት ለማንኛውም ዜጋ እንደሚያደርገው ሁሉ ይህን መሰሉን ሁኔታ ለሁሉም ዜጎቹ ያመቻቻል። እናም ለተመላሽ ስደተኞቹ ለሀገሬው ዜጎች እንደሚያደርገው ድጋፍ ያደርጋል።
እናም በእነዚህ ሀገራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ይሳተፋሉ ማለት ይመስለኛል። የተለየ ፍላጎት ሊኖርበትም ይሁን የተለየ ትርጓሜ ሊሰጠው ይገባል ብዬ አላምንም—መንግስት ማድረግ ያለበት ድጋፍ ለሌላው ዜጋው የሚከውነውን ተግባር ነውና።
በአሁኑ ወቅት መንግስትና ህዝቡ በሀገራችን ውስጥ እየፈጠሩት ያለው ሁኔታ ለሚሰራ ማንኛውም ዜጋ የተመቻቸ ነው። በእኔ እምነት በሳዑዲ ይኖሩ የነበሩት ዜጎቻችን ማናቸውንም የስራ ዓይነቶች በሚገባ ይገነዘባሉ። በሀገራችን ምቹ የልማት ስራ ውስጥ ሊሳተፉ ይገባል። እዚህ ሀገር ሲመጡም የሚጠብቃቸው ይኸው መንግስታዊ ድጋፍ ነው።
ዋናው ነገር አሁንም ወደ ሀገር ቤት መመለስ የሚገባቸው ዜጎች የመመለሳቸው ሁኔታ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ በሳዑዲ መንግስት የተሰጠው የምህረት ጊዜ ድፍን አንድ ወር ያለው ነው።
አሁንም መንግስት ዜጎቹን የማውጣት ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ይህን እያደረገ ያለውም በዜጎቹ ላይ አንዳች ዓይነት ችግር እንዳይፈጠር ከማሰብ ነው። ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት በሳዑዲ በዜጎቻችን ላይ የደረሰውን አደጋን ስለሚገነዘብም ነው።
በዚያን ወቅት በሳዑዲ ውስጥ የሚኖሩ ህገ ወጥ ዜጎቻችን ለደረሰባቸው ሞት፣ እንግልትና ስቃይና በባዶእጅ ንብረትን ጥሎ የመመለስ እውነታን መንግስት ዝም ብሎ አልተቀበለም። ለዜጎቹ እጅግ ተከራክሯል። ተገቢውንም ድጋፍ አድርጓል። ዛሬም እያከናወነ ያለው ጥረቱ እንደዚያ ዓይነቱ ተግባር ዳግም እንዳይከሰት ካለው ህዝባዊ አስተሳሰብ ነው።
በወቅቱ በህገ ወጥ መንገድ በሳዑዲ ይኖሩ በነበሩ ዜጎች ላይ የደረሰው ሞት፣ እንግልትና በባዶ እጅ መመለስ የሚያሳየው ነገር ቢኖር፤ ዛሬም ለሁለተኛ ጊዜ በምህረት አዋጁ ያልተጠቀሙ ስደተኞች የዚያን ጊዜው አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደማይችል ምንም ዓይነት ዋስትና የለም።
ያም ሆኖ በእርግጥ በህገ ወጥ መንገድ ባህር ተሻግረው በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎቻችን ቁጥር በርካታ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም ህገ ወጥንም በህግ መጠየቅ እንጂ ህይወት ማጥፋት ወንጀል እንደሆነ የሚያስገነዝብ አቋሙን የኢትዮጵያ መንግስት ገልፆ እንደነበር እናስታውሳለን።
በወቅቱ በዚህ የመንግስት አቋም የአያሌ ዜጎቻችንን ህይወት ከአደጋ መታደግ መቻሉን የተገነዘበ ኢትዮጵያዊ ምን ያህል እንደተደሰተና በኢትዮጵያዊነቱም ምን ያህል እንደኮራ መገመቱ አዳጋች አይመስለኝም። ዛሬም ቢሆን ከስደት ተመላሾቹ በመንግስታቸው መኩራት አለባቸው።
የትናንቱ መንግስታቸው የዛሬው ነው። ህዝባዊነቱ አልተለወጠም። ሊለወጥም አይችልም። የተመሰረተበት ባህሪው ስለሆነም የሚለወጥበት ምክንያት የለም። በመሆኑም ከስደት ተመላሾቹ ይህን እውነታ ተገንዝበው ወደ አገራቸው በመመለስ ይኖርባቸዋል። ለሁለተኛ ጊዜ እንደተሰጠው የምህረት አዋጅ ነገሮች ከእንግዲህ ቀላል ላይሆኑ ይችላሉ። እናም መንግስ በፍትሐዊ መንገድ ለዜጎቹ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ተገንዝበው ወደ ሀገራቸው ዛሬ ነገ ሳይሉ ሊመለሱ ይገባል።