Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሕግ የበላይነትን የማስከበሩ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል – የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ

0 640

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 የሙስና ተግባርን በማጋለጥ የሕግ የበላይነትን የማስከበርና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን የማስጠበቁ ጉዳይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ገለፁ።

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ባለሃብቶችና ደላሎች ቁጥር 42 ደርሷል።

በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር ያልዋሉ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ አካላት ራሳቸውን እንዳይሰውሩና መረጃ እንዳያሸሹ ተገቢው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግና የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ጥናት ሲያካሂዱ  ቆይተዋል።

በዚህ መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በፌዴራል ደረጃ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ መጀመር የሚያስችሉ ማስረጃዎች በበቂ ሁኔታ የተገኘባቸውን ተቋማትና ግለሰቦችን በመለየት በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉትን ግለሰቦች በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቀደም ብሎ መንግስት በሙስና ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን እየለየ ለህግ እንደሚያቀርብ በገባው ቃል መሰረት ተከታታይ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አመልክተዋል።

የህግ የበላይነትን በማስከበር ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የማስጠበቁ ጉዳይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው አቶ ጌታቸው ያመለከቱት።

ከፌደራልና ከአዲስ አበባ ከተማ ዋና ኦዲት መስሪያ ቤቶች የተገኙ ሪፖርቶችን፣ ከመንግስት ሰራተኞችና ከህብረተሰቡ የደረሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ በተከናወኑ ክትትሎችና ጥናቶች እርምጃውን ለመውሰድ የሚያስችሉ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ማስቻላቸውንም ነው ያብራሩት።

ከፌደራል መንገዶች ባለስልጣን ከ1 ቢሊዮን 358 ሚሊዮን ብር በላይ፤ ከስኳር ኮርፖሬሽን፣  ከመተሃራ፣  ተንዳሆ እና ኦሞ ኩራዝ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ከ1 ቢሊዮን 21 ሚሊዮን ብር በላይ፤ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ፤ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከ198 ሚሊዮን ብር በላይ እና ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ የግዥ መመሪያው ከሚያዘው ውጪ ክፍያና ግዢ የፈፀሙ የሥራ ኃላፊዎች፣ ደላሎችና ባለሀብቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤት በሺዎች የሚቆጠር የእንግሊዝ ፓውንድ፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ዩሮ፣ በመቶ ሺዎች የሚቀጠር የአሜሪካን ዶላር፣ በአስር ሺ የሚቆጠር የተባበሩት አረም ኤምሬትስ ድርሃም እንዲሁም የቻይናና የዩጋንዳ ገንዘቦች ጭምር መያዛቸውንም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

የቤትና የመሬት ይዞታ ባለቤትነትን የሚያረጋግጡ ካርታዎች፣ የቤትና የጭነት ተሽከርካሪ ሊብሬዎች እንዲሁም የተለያዩ ኩባንያዎች ላይ የአክሲዮን ክፍያ የፈፀሙባቸው ሰነዶች  እንዲሁም የተለያዩ የገንዘብ መጠን ያላቸው የባንክ ደብተሮች በብርበራ ወቅት ተገኝተዋል።

የጠፉ ንብረቶችን ለማስመለስ በብርበራ የተገኙ ንብረቶችን ጨምሮ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚታገዱ ንብረቶች እንደሚኖሩም  ነው አቶ ጌታቸው የተናገሩት።

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ሌሎች ግለሰቦች ራሳቸውን ሰውረው መረጃ እንዳያሸሹ ተገቢው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።

ቀጣይ ምርመራው ሊስባቸው የሚችሉ አካላት ንብረት እንዳያሸሹና ራሳቸውንም የመሰወር ሁኔታዎች እንዳይኖሩ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገለጸዋል።

ማንኛውም ወንጀለኛ ከህግ የማያመልጥ ቢሆንም፤ አጥፊዎችን በመጠቆም የህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ህብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy