Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አብዮት የተፋፋመባት ሃገር

0 729

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አብዮት

የተፋፋመባት ሃገር

ስሜነህ

የመጀመሪያ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አራት ግቦችና ሰባት አፈፃፀም አቅጣጫዎችን በማካተት የተነደፈ ነው። በዚህም መሠረት ኢኮኖሚውን በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ 11 በመቶ በማሳደግ የሚሊኒየም የልማት ግቦችን ማሳካት፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎት ሽፋንን በመጨመርና ጥራቱን ማረጋገጥ፤ የተረጋጋ፣ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግስትን በመፍጠርና በማጠናከር ለቀጣይ የሀገር ግንባታ ስራዎች ምቹ መደላደል መፍጠርና የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን በማስፈን የልማቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ የሚል የነበረ መሆኑ ይታወሳል።

የእቅዱ መሰረታዊ አቅጣጫዎችም ፈጣን፣ ቀጣይና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ፣ የግብርና ዘርፍ ዋና የእድገት ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት ማስቻል፣ መሰረተ ልማትን ማስፋፋትና ጥራትን ማረጋገጥ፣ የማህበራዊ ልማትን ማፋጠንና ቅልጥፍናውን ማረጋገጥ፣ አቅም ግንባታና መልካም አስተዳደርን ማሳደግ እና የሴቶችንና የወጣቶችን ብቃት፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚሉት የነበሩ መሆኑና ጥሩ ሊባል በሚችል አፈጻጸም የተጠናቀቀ መሆኑ ይታወቃል። ከዚሁና አንደኛ ከነበረው ዙር በርካታ ተሞክሮዎችን ቀምሮ የቀጠለው የሁለተኛው ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ደግሞ ትኩረቱን በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ላይ አድርጎ ጉዞውን ከጀመረ 2 ዓመታትን አስቆጥሯል። ጉዞውም ከተቀሩት የ3 ዓመታት እድሜ አኳያ ሲሰላ የተሳካ ስለመሆኑ በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ መረጃዎች እያመለከቱ ነው።

ለስኬቱ የላቀውን አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኘው ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ስለመሆኑም እየተነገረ ነው። ዥንዋ የኢትዮጵያ መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ እና ኤክስፖርቱ ዘርፉን ለማሳደግ በመጪው ዓመት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ቁጥር ወደ 15 የማሳደግ ዕቅድ መያዙን የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ኮርፖሬሽን የቦርድ ሊቀመንበር አርከበ ዕቁባይ ከዜና አውታሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ መናገራቸውን በዘገባው አስታውቋል። ኢትዮጵያ በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ላይ የምትገኘው እ.ኤ.አ በ2025 የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የጠቅላላ ሀገራዊ ምርቱን (GDP) 20 በመቶ ድርሻን እንዲይዝ፣ የኤክስፖርት ዘርፉ ደግሞ 50 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው ለማድረግ ነው ሲሉ ዶ/ አርከበ ገልጸዋል ያለው ዘገባው በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ሰባት አገልግሎት መስጠት የጀመሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዳሏት መጠቆሙም የመጀመሪያው ማረጋገጫ ነው። ሌሎችም የእቅዱን ስኬት አመላካች የሆኑ መረጃዎች እየወጡ ነው። የግል ንጽህና እና የውበት መጠበቂያ ምርቶችን በማምረት እና በመላው ዓለም በማከፋፈል የሚታወቀው ኦንቴክስ ኩባንያ  ማምረቻ ፋብሪካውን በኢትዮጵያ አቋቁሞ ወደ ምርት መግባቱን ቢዝነስ ዋየር ድረገጽ አስታውቋል። ኦንቴክስ በኢትዮጵያ ገበያ ቀደም ብሎ ያሠራጫቸው የነበሩትን (Can bebe Comfort & Dry diapers) እንዲሁም ሞዴሶችን እና ሌሎች የእጅ እና የፊት ንጽሕና መጠበቂያ እርጥበት ያላቸው ሶፍቶችን በሰፊው እንደሚያመርት ድረ-ገጹ አመላክቷል። ኦንቴክስ አዲሱን የማምረቻ ኢንዱስትሪውን ያቋቋመው በሀዋሳ ኢንዱስትሪል ፓርክ ውስጥ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው ምርቶቹን ወደ ወጪ ከመላክ በተጨማሪ በተለየ መልኩ ለአገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ስልት ነድፎ እንደሚተገብር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቻርለስ ቦአዚዝ መግለጻቸውን የተመለከተው የድረገጹ ዘገባም ሌላኛው እና ስለአፈጻጸሙ አመርቂነት ሊጠቀስ የሚገባው አስረጅ ነው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በዋናነት በጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ተነግሯል። ስለሆነም ይመስላል በርካታ የቻይና፣ የደቡብ ኮሪያ እና ሕንድ የልብስ አምራቾች የማምረቻ ኢንዱስትሪዎቻቸውን በኢትዮጵያ ውስጥ በመክፈት ላይ የሚገኙት። ኒካይ ኤዢያን ሪቪው ድረገጽ እንዳስታወቀው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የሦስቱም ሀገራት ልብስ አምራቾች ምርታቸውን በአብዛኛው ለአሜሪካ እና ለአውሮፓ ገበያዎች ያቀርባሉ። ዘገባው አያይዞም ኩባንያዎቹ በዓለም ላይ ስመ-ጥር እና ዝነኛ ልብስ አምራች ሆኑትን የአሜሪካው Calvin Klein እና ጃፓኑ Uniqlo brand ልብሶች ምርት እንደሚያመርቱ አስታውቋል።

የቻይና ኩባንያዎች ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የነበረውን የውጭ ኢንቨስትመንት ሲመሩ እንደነበር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ዋቢ ያደረጉ መረጃዎች እየገለጹ ነው። በኢትዮጵያ ተመዝገበው ከሚገኙ 379 የቻይና ኩባንያዎች መካከል 279 ያህሉ ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ 13 ነጥብ 16 ቢሊዮን ብር በሚያወጡ ፕሮጀክቶች ላይ መሳተፋቸውን፣ ቀሪዎቹ 100 ኩባንያዎች በትግበራ ላይ እንደሚገኙ የኮሚሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኃይሉን ዋቢ አድርገው የወጡ መረጃዎች  አመልክተዋል። በርካታ የቻይና ኩባንያዎችን ቀልብ የሳበው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ መሆኑም ተጠቁማል።

ከቻይና ኩባንያዎች ጋር ተያይዞ ሌሎችም መረጃዎች እየወጡ ሲሆን፤ Tiesiju Civil Engineering (CTCE) group የተባለ የቻይና ኩባንያ አዲስ አበባ ውስጥ በቂሊንጦ አካባቢ እየገነባው የሚገኘው የመድኃኒት ማምረቻ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በስምንት ወራት ውስጥ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር መገለጹን africanreview.com ድረገጽ አስታውቋል። መድኃኒት ማምረቻ ኢንዱስትሪያል ፓርክ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የሀገሪቱን የጤና አስተዳደር ሥርዓት በማዘመን እና ደህንነታቸው የተጠበቁ መድኃኒቶችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው በዘገባው የተመለከተው። በተጨማሪም የፓርኩ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መግባት በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ በከፍተኛ የወጪ ምንዛሬ የምታስገባውን መድኃኒት በማስቀረት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አመላክቷል።  

በጥቅሉ እስካሁንና በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተገነቡት መሰረተ ልማቶች፣ ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማነት ትልቅ አቅም መሆናቸው ሌላው ተፈፃሚነቱን ከወዲሁ ያመላከተና ለውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰቱም ትልቅ አቅም የፈጠረ እንደሆነ ለመገመት ይቻላል፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የአገሪቱን የኢኮኖሚ አውታር በማስፋት፣ ኢንዱስትሪ በተለይም ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ወሳኝ ሚና እንዲጫወት በማድረግና የወጪ ንግድን በማሳደግ፣ የአገሪቱን የህዳሴ ጉዞ  የሚያሳልጥ ነው፡፡

ወጣቱ ትውልድ በገጠርና በከተማ ልማት በማሰማራት የስራ ዕድል ከመፍጠር ጎን ለጎን የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሃይል ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ ከላይ በተመለከቱት አስረጂዎች እና መሰል ተቋማቶች የገጠሩን አጠቃላይ ገፅታ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚለውጠው ይታመናል፡፡ የመስኖ ግብርና፣ የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንደዚሁም የእንሰሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ስራ በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋትን ትኩረት ያደረገው ዕቅድ፣ ግብርናው በዕቅድ ዘመኑ ለልማቱና ለፈጣን ዕድገቱ የማይተካ አስተዋፅኦ ከማድረግ ባሻገር የዘመናዊ አምራች ዘርፍ ዕድገት ዋና ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚያስችለው ይታመናል፡፡

የገጠር ኢንዱስትሪ ማዕከላት እና በሂደት እየተፈጠሩ ከተሞቻችንም በዛው መጠን እያደጉ ሲሄዱ የህብረተሰቡ የኑሮ ደረጃ እየተቀየረ፣ የከተማና የገጠር ትስስር እየጠበቀ፣ ያደገ ህብረተሰብ ለመገንባት የሚያስችለን አቅም እየተፈጠረ መሄዱ አይቀሬ  እንደሚሆን ከላይ የተመለከቱት አስረጂዎችና ያለአንዳች መንገራገጭ እየሄደ የሚገኘው አፈጻጸም አመላካች ነው፡፡  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy