Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህል ይዳብር

0 2,078

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህል ይዳብር

ብ. ነጋሽ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባሉ ዓመታት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየተለመደ መጥቷል። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት በተካሄደው 14ኛው የወጣቶች የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመላ ሃገሪቱ 10 ሚሊየን ገደማ ወጣቶች የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ተሰማረተው እንደነበር ይታወሳል። በያዝነው ዓመት ደግሞ ወደ 11 ሚሊየን የሚጠጉ ወጣቶች ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሰማርተዋል። በአዲስ አበባ ብቻ 9 መቶ ሺህ ወጣቶች ናቸው ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተሰማሩት። በኦሮሚያ 4 ሚሊየን ወጣቶች ተሰማርተዋል።

ወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሚሰጡባቸው ዘርፎች መሃከል ለ1ኛና ለ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ የጎልማሶች ትምህርት፣ የደካሞችንና የአረጋውያንን የመኖሪያ ቤት መጠገን፣ የአካባቢ ጽዳት፣ ችግኝ ተገላ፣ የትራፊክ ደንብ ማስከበር፣ የደም ልገሳና የመሳሰሉ ናቸው። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ ደንብ ማስከበር ላይ ጉልህ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ እየታየ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ነባረ ባህል ነው። ለችግር የተጋለጡና ችግር የደረሰባቸውን ሰዎች ቀስቃሽ ሳያስፈልግ መርዳት የተለመደ ባህላዊ ተግባር ነው። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ መንገድና የተሟላ የትራንስፖርት አገልግሎት ባልነበረበት ወቅት የታመሙ ሰዎችን በርካታ ኪሎ ሜትሮች በወሳንሳ ተሸክሞ የሚወስዱት የታማሚው ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ሃገሬው ነው።  ሙታንን መቅበር በተቀጣሪ ሰራተኞች የሚከናወን ተግባር አይደለም። የሃገሬው እንጂ። ሃገሬው የቀብር ጉድጓድ ቆፍሮ፣ አስከሬን ተሸክሞ የቀብር ስነስርአቱን ይፈጽማል። በኢትዮጵያ ሙታንን መቅበር የቤተሰብ እዳ ሆኖ አያውቅም፤ አሁንም ድረስ።

የኢትዮጵያ ህዝብ ሃላፊንት በጋራ የመውሰድ ባህል አለው። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህል እንዲኖረው ያደረገው ከዚህ ሃላፊነትን በጋራ የመውሰድ ዝንባሌ የመነጨ ነው። በአንድ ቤተሰብ ወይም ግለሰብ ላይ የሚፈጠር ችግር የቤተሰቡና የግለሰቡ ብቻ ሳይሆን የህብረተሰብ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ህሙማንን ማስታመም የጋራ ሃላፊነት የሚሆንበት ሁኔታ አለ። በተለይ ቋሚ የአካል ወይም የአእምሮ ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች መንከባከብ በጋራ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ። ይህን በተመለከተ ከቀድሞ የኢህአዴግ ታጋዮች የሰማሁት አንድ ጥሩ ምሳሌ አለ። የኢህአዴግ ታጋዮች አንድ መንደር ውስጥ መናገርና መስማት፣ መንቀሳቀስ የማይችል አንድ የአካል ጉዳተኛ የአካባቢው ሰዎች ተራ ገብተው ሲክባከቡ እንዳጋጠማቸው ነበር ያጫወቱኝ። ሃላፊነትን በጋራ የመውሰዱ ነገር ያስገረማቸው ታጋዮች ይህን የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ ሲጠይቋቸው፤ እግዚአብሄር ይህን ልጅ እንዲህ አድርጎ በመሃከላችን የፈጠረው ሊፈትነን ይሆናል። ስለዚህ ይህን አካል ጉዳተኛ መንከባከብ የሁላችንም ሃላፊነት ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል። ይህ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን በጋራ ሃላፊነት የመውሰድ ነባር ባህል ያሳያል።

ኢትዮጵያውያን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡት በችግር ወቅት ብቻ አይደለም። በምርት ስራ ላይም በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተጋገዛሉ። የደቦ ወይም ጂጊ ባህልን ለዚህ ማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። ከቤተሰብ አቅም በላይ የሆነ የምርት ስራ – እርሻ፣ አጨዳ፣ ጎጆ ማዋቀር . . . ሲኖር መንደረተኛው በሙሉ የራሱን መሳሪያ ይዞ በስራ ይተባበራል።

ይህ የኢትዮጵያውያን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአካባቢ፣ በክልልና በሃገር አቀፍ ደረጃ በተደራጀ ሁኔታ በማከናወን ረገድ ግን ያን ያህል የተጠናከረ ተጠቃሽ ነገር አይታይም። በወታደራዊው ደርግ የስልጣን ዘመን በ1967 ዓ/ም የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ያሳተፈው የእድገት በህብረት ዘመቻ በተወሰነ ደረጃ እንደበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሊታይ ይችላል።

በዚሁ በወታደራዊው ደርግ የስልጣን ዘመን የተካሄደውን የመሰረተ ትምህርት ዘመቻም እንዲሁ የበጎ ፍቃድ ባህሪዎች አሉት። እነዚህን ዘመቻዎች ሙሉ በሙሉ እንደበጎ ፍቃድ አገልግሎት መውሰድ ግን አይቻልም። ምክንያቱም በዘመቻዎቹ ላይ የተሳተፉትን ወጣቶች የሚያስገድድ ህግ ነበር፤ ሙሉ በሙሉ የተሳታፊዎቹን ፍቃደኝነት ያለበት አልነበረም።

ያም ሆነ ይህ፤ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት፣ በተለይ በክረምት ወቅት የተደራጀ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አሰጣጥ እየጎለበተ መጥቷል። ዘንድሮ 15ኛው የከረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ነው በመካሄድ ላይ የሚገኘው።

በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተመለከተው አሁን በያዝነው ክረምት በመላ ሃገሪቱ 15ኛው ዙር የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተካሄደ ነው። ለምሳሌ በአዲስ አበባ 9 መቶ ሺህ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ተሰማረተዋል። በጎ ፍቃደኛ ወጣቶቹ ወጣቶቹ የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት በሚሰጥባቸዉ ማዕከላት ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ ላሉ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ ይገኛሉ። በዚህ የማጠናከሪያ ትምህርት አገልግሎት ከ85 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ። የማጠናከሪያ ትምህርቱ የሚሰጠው በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሆን፣ ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ መምህርነት አገልግሎት ላይ ተሰማርተዋል። ከዚህ ቀደም በተለያየ ደረጃ የማጠናከሪያ ትምህርት የተከታተሉ ተማሪዎች በመደበኛ ትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።

ከፍተኛ የተኝከርካሪ ትራፊክ ፍሰትና መጨናነቅ ባለበት አዲስ አበባ በመንገድ ትራፊክ ደህንነት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት ከ6 ሺህ በላይ ወጣቶች ስልጠና ወስደው ተሰማረተዋል። የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶቹ አገልግሎት ተሳትፎ በተለይ በእግረኞች መንገድ አጠቃቀም ላይ ለውጥ መፍጠር መፍጠሩ በተጨባጭ የሚታይ እውነት ነው። የበጎ ፍቃደኞቹ አገልግሎት ከ50 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ለማዳን የሚያስችል እንደሆነም ይገመታል።

በተመሳሳይ፣ በኦሮሚያ የወጣቶች የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በ20 የክልሉ ዞኖችና በሁሉም የከተማ መስተዳድሮች እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ የወጣቶች ፌዴሬሽን አስታውቋል። በኦሮሚያ በተያዘው ዓመት ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች 4 ሚሊየነ ናቸው። ይህ የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ቁጥር ከባለፈው ዓመት በ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ይበልጣል።

ባለፈው ዓመት ክረምት  2 ነጥብ 6 ሚሊየን ገደማ ወጣቶች ነበሩ ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተሰማሩት። ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ በተካሄደ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፣ ወጣቶቹ 73 ሚሊዮን ብር የሚገመት አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ከክልሉ የወጣቶች ፌዴሬሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል ። ዘንድሮ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት 84 ሚሊዮን ብር የሚገመት አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሰሞኑን በአዳማ በተካሄደ ሃገር አቀፍ የወጣት አደረጃጀቶችና ባለድርሻ አካላት መድረክ  ላይ፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመላ ሃገሪቱ ቀጣይነት ባለው መንገድ እንዲካሄድ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የወጣቶችና ሰፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል። የወጣቶችን ዕውቀት፣ ጉልበትና ክህሎት በማቀናጀት በሃገሪቱ ልማት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲያበረክቱ ሚኒስቴሩ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በተለይ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በወጣቶች ዘንድ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል  በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የወጣቱን ክህሎትና ግንዛቤ ለማዳበር እየተሰራ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትግበራ ዘመን ወጣቶች በተሰማሩበት የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስታውጽኦ ማበርከታቸውንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በአጠቃላይ፣ ከግዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣው የተደራጀ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በአገልግሎቱ ላይ የሚሳተፉ ወጣቶች ለህብረተሰቡ ከሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በተጨማሪ ወጣቶቹን በህዝብ አገልጋይነት አመለካካት ለማነጽ ያግዛል። በህዝብ አገልጋይነት የታነጸ ወጣት ሃገርን የመምራት ፍላጐትና ብቃት ይኖረዋል። እናም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህል እንዲሆን መሰራት አለበት።

 

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy