Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ መድረሻና ሁሉን አቀፍ ጠቀሜታው

0 390

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ መድረሻና ሁሉን አቀፍ ጠቀሜታው

                                                           ይነበብ ይግለጡ

ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በአለም አቀፍ መድረክ ጉልህ ተሰሚነትና ተደማጭነትን  ለማግኘት የበቃች ሀገር ነች፡፡ ተሰሚነትና ተደማጭነትዋ እያደር እየጎለበተ፣ እያደገ የመጣበት ተጨባጭ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ውድቀው በነበረበት ዘመን ብቸኛ ድምጽ ሁና ለአፍሪካ ነጻነት ስትከራከርና ድምጽዋን  ስታሰማ የኖረች፣ አቅምዋ በፈቀደውም መጠን የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትን ነጻ አውጪዎች በሀገር ውስጥ ሰብስባ ያስተማረች፣ ያሰለጠነች፣ ለነጻነታቸውም ጸንተው እንዲቆሙ ያደረገች ሀገር ነች፡፡

ከዚህም በላይ በአፍሪካ ውስጥ በሚፈጠሩ የእርስ በእርስ ጦርነቶችና አለመግባባቶች ቀደም ካለው የኮንጎ ብራዘቢል ጦርነት ጀምሮ በሰላም አስከባሪነትና በማረጋጋት ስራ ተሰልፋ የድርሻዋን የተወጣች፤ በዘመነ ኢህአዴግም በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን – በዳርፉር የሰላም አስከባሪነት ግዳጅዋን በከፍተኛ ሀላፊነት የተወጣችና በመወጣትም ላይ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕዝቦች ያላትን ቅርብ አጋርነትና ወዳጅነት፣ ወንድማማችነት በብዙ መልኩ ስትገልጽ፣ በተግባርም ስታሳይ የኖረች ሀገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ፋና ወጊና ቀንዲል በመሆን በታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የኢጣሊያን ፋሽስት ወራሪ ጦር አድዋ ላይ ድል በመምታት በጥቁር አፈርና መሬት ላይ የነጭ ወራሪዎችን ድል ያደረገች፣ የማረከች፣ ያንበረከከች ሀገር ናት፡፡ ይሄን እውነት መላው አለም ያውቀዋል፡፡

ሀገረ ኢትዮጵያ በአለም ላይ የመጀመሪያው የሰው ልጅ መገኛ፣ በአለም ታላላቅ ጥንታዊ ቅርሶች በዩኔስኮ ተመዝግበው የሚገኙባት፣ ጥንታዊ የመንግስትነት ታሪክ ያላት ቀደመት የስልጣኔ ምድር የነበረች፣ አሁን ወደቀድሞው የኃያልነት ታሪክዋ እየተመለሰች ያለች ሀገር ነች፡፡

ጥንት የነበረው ቀዳሚ ስልጣኔዋ ወድሞና ጠፍቶ የቁልቁለት ጉዞ ጀምራ፣ ስምዋም በድሕነት፣ በረሀብና በተመጽዋችነት የሚነሳ ሁኖ ለዘመናት ለመኖር ተገዳ የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬ ከዚያ አስከፊ ጨለማ በመውጣት፣ ድህነትን በመዋጋት፣ አዲስና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ፤ በብዙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ሀገርን ሙሉ በሙሉ እየለወጠ ባለ የእድገት እርምጃ እየገሰገሰች ያለች ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡

በአፍሪካ ብቻም ሳይሆን በአለም በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ከተዘረዘሩ ቀደምት ሀገራት ውስጥ አንደኛዋና በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ናት፡፡ ዛሬ ለአፍሪካ ሀገራት በኢኮኖሚ እድገት ተጠቃሽና ምሳሌ በመሆን፤ ብዙዎችም ከተሞክሮዋ ሊማሩና ልምድ ለመውሰድ የሚመላሉሰባት ለመሆን በቅታለች፡፡

ኢትዮጵያ ግዙፍና ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ላይ ያለች ሀገር ነች፡፡ በዚህም ሂደት የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማእከል (ሀብ) የምትሆንበት ግዜ ብዙም ሩቅ አይደለም፡፡ ዛሬ የአፍሪካ ሀገራት በኢኮኖሚ ጥቅም እንዲተሳሰሩ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ የምትገኘውም እሷው ነች፡፡

የአፍሪካ ሀገራትን በመንገድ የማገናኘት፤ በንግድ የማስተሳሰር፣ በኃይል ግንባታም ተጠቃሚ የማድረግ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ቅርብ የኢኮኖሚና የንግድ ትስስር ከማድረግም ባለፍ የጋራ በሆኑ የጸጥታና የደሕንነት ጉዳዮች ዙሪያ ኢትዮጵያ የበኩልዋን የላቀ ድርሻ በመወጣት ላይ ትገኛለች፡፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለቀንዱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር የሚያበረክተው፣ በሀይል አቅርቦት ረገድ የሚያስገኘው ጥቅም እጅግ የጎላ ሲሆን ለሀገራችን ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በበቂ ደረጃ ለመጠቀም ያስችላል፡፡ የአፍሪካ የውሀ ማማ ተብላ የምትወደሰው ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የብዙ ታላላቅ ፕሮጀክቶች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ ፋብሪካዎች ማማ ወደ መሆኑም ተቃርባለች፡፡ ይሄም እኛ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን መላ አፍሪካውያንን ሁሉ በእጅጉ ሊያኮራን ይገባል፡፡

እኛ ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የልብ ወዳጆች፣ በክፉም ሆነ በደጉ ቀን ከጎናቸው ያልተለየን፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት መስራችና የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያ እንዲሆን የወቅቱ መስራች አባቶች በአንድ ድምጽ ተስማምተው ቢሮው በአዲስ አበባ እንዲሆን የወሰኑባት የታሪካዊ ምድር ባለቤቶች ነን፡፡ ለመላው የአለም ጥቁር ሕዝብ የክብሩና የኩራቱ ምንጭ ተደርገን የምንወሰድ ሕዝቦችም ነን፡፡

በሌላ መልኩ ስናየው ዛሬ ዘመን ከሸበተ በኋላ ራሳቸውን ወደ አፍሪካ ለመመለስ ደፋ ቀና ቢሉም ግብጻውያን ከአፍሪካዊነት ይልቅ አረባዊነትን መርጠው የሕይወታቸውን እጣ ፈንታ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር አጣምረውና አቆራኝተው፣ አፍሪካና አፍሪካውያንን ሙሉ በሙሉ የረሱበት፣ አፍሪካውያን አይደለንም ለማለትም የዳዱበት ሁኔታ በሰፊው ታይቶአል፡፡

አፍሪካ መሬት ላይ ቢፈጠሩም ስለአፍሪካ ደንታ ቢስ ሆነው ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡ አብዛኛው አፍሪካዊ ግብጾችንና መንግስታቸውን የሚያውቀው በመካከለኛው ምስራቅ ቀዳሚ ተዋናይነታቸው እንጂ በአፍሪካዊነታቸው አይደለም፡፡ ለአፍሪካ ያበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦና ድርሻ የላቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት አፍሪካውያን ለግብጽ ብዙም ቦታ ሳይሰጥዋት ኖረዋል፡፡ የተረሳች ተብላ የምትጠቀሰውን አፍሪካ ግብጾችም በበኩላቸው ረስተዋት ኖረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ ሁልግዜም በአፍሪካ ጉዳይ ቀዳሚ ሚና ያላት፣ ድምጽዋን ከፍ አድርጋ የምታሰማ፣ ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረገች፤ የዋናው  ጽህፈት ቤት መቀመጫ በሀገርዋ እንዲሆን የፈቀደች፣ ዛሬም በአፍሪካዊ እምነትና ማሕተብዋ ጸንታ የቆመች ሀገር ነች፡፡ በምንም መልኩ ለአፍሪካ መቆርቆርና መቆምን በተመለከተ ኢትዮጵያና ግብጽ በአንድ ሚዛን ሊቀመጡ፣ ሊሰፈሩም አይችሉም፡፡ የመላው አፍሪካ ሀገራት ሁልግዜም ከኢትዮጵያ ጎን የሚቆሙበት ምስጢርም ይሄው ነው፡፡

ኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካውን የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላንና የኤኤንሲን አመራር በሀገርዋ ያስጠለለች፣ ወታደራዊ ትምህርት አስተምራ ለነጻነታቸው እንዲዋጉ ያደረገች፣ የከለላ ቪዛ የሰጠች፣ የሞዛምቢክን ነጻ አውጪዎችና እነሙጋቤን ያስጠለለች፣ ከ40ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ሰራዊትን ያሰለጠነች፣ ለእነዶ/ ኮሎኔል ጆን ጋራንግ መጠለያና የክፉ ቀን ወዳጃቸው የነበረች ሀገር ናት፡፡ ለዛሬዎቹም የደቡብ ሱዳን መሪዎችም ጭምር፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በመላው አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ የመሪነት ሚናን  በቀደሚነት ስትጫወት ኖራለች፤ በአፍሪካ ቀንድ ተጽእኖ ፈጣሪ ሀገር ለመሆንም በቅታለች፡፡ የአፍረካ ሀገራት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብራቸው እንዲጎለብት ኢትዮጵያ  የምታደርገው ሰፊ ጥረት ዛሬም ጎልብቶ ቀጥሎአል፡፡  

ኢትዮጵያ ሰላምን አፍቃሪና ለሰላም ጸንታ የቆመች ሀገር መሆንዋን በተለያዩ ታሪካዊ ወቅቶች ለአፍሪካም አልፋ ለአለምም ለማሳየት የበቃች፤ ሰላም አክባሪ ለሰላምም ዘብ የምትቆም ሀገር ነች፡፡ የአባይ ውሀ ተፈጥሮ በጋራ እንድንጠቀምበት ያደለችን በመሆኑ የጋራ ሀብት ስለሆነ በጋራና በሰላም ልንጠቀምበት እንችላለን የሚለው ቋሚ እምነትዋ ዛሬም ዝንፍ አላለም፡፡

 

ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ ውሀ በመጠቀም የማልማት መሰረታዊ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ መብት ያላት ሀገር ነች፡፡ የውሀው ተጠቃሚዎች ከውሀው ሊያገኙት የሚገባውን ጥቅም አልከለከለችም፤ ሀሳቡም የላት፡፡ የግድቡ መሰራት በውሀው መጠን ላይ የሚያደርሰው አንዳችም ችግር ካለመኖሩም በላይ ተጋሪ ሀገራትን የበለጠ በኢኮኖሚው መስክ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ሳትታክት ስትገልጽ ቆይታለች፡፡ በቅርቡም ይህንን እውነት በተግባር ለማየት ግዜው የደረሰ ይመስላል፡፡ የአባይ ግድብ መጠናቀቅና ስራ ላይ መዋል በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ ያደርጋልና፡፡

 

ግብጾች ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ውሀ አንድ ቀን ግድብ ትሰራለች በሚለው ዘመናትን ባስቆጠረው ስጋታቸው በራሳችን ውሀ ተመልሰው ጠላት ሁነው ከጀርባና በፊት ለፊትም ሲወጉን የኖሩበትንና ያሉበትን ሁኔታ ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ እናውቃለን፡፡ ይህ ስጋትና ፍርሀታቸውም ጸረኢትዮጵያ ሀይሎችን ከነሱ ጀርባ በማደራጀት በኢትዮጵያ ላይ እስከማዝመት አድርሶአቸዋል፡፡ ዛሬም በፊት ለፊት እየሳቁ ከጀርባ ሆነው እየወጉን እንዳሉ  እናውቃለን፡፡ እነሱም ያውቃሉ፡፡ ደግነቱ አለመሳካቱ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy