የአማራና የትግራይ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ያዘጋጁት የህዝብ ለህዝብ መድረክ ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተጀምሯል።
የሁለቱም ክልል ህዝቦችን አንድነት ና አብሮነት ለማጠናከር በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የፌደራል መንግስት የስራ ሃላፊዎች፣የብአዴን እና ህውሀት አመራሮች፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና የሁለቱም ክልሎች የሀገር ሽማግሌዎች ተሳታፊ ናቸው።
በህዝብ ለህዝብ ውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራና ትግራይ ህዝቦች አብረው ለዘመናት የኖሩ በደም እና በአጥንት የተሳሰሩ ህዝቦች ናቸው፤ የሀገችራንን ልዕልና እና ክብርን ለማስጠበቅ አብረው ተጋድለው ለድል የበቁ ህዝቦች ናቸው ብለዋል።ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው ሁለቱ ድርጅቶች ችግሮችን እየፈቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙቱ ላይ ሳንካ የሚሆኑ ችግሮችን ለመፍታት በፍቅር እና በመተጋገዝ አብረው መስራት አለባቸው ብለዋል።
የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አባይ ወልዱ በበኩላቸው ሁለቱም ህዝቦች የተሳሰሩ እና የተዋኻዱ ናቸው ፤ ህዝቦቹ እና ድርጅቶቹ አብረው ታግለው አብረው ለድል የበቁ ናቸው ብለዋል።የሀገር ሸማግሌዎች የህዝብ ለህዝብ ትስሩን ለማጠናከር የጀመራችሁት ስራ መልካም በመሆኑ የትግራይ ክልል መንግስት በተቻለው አቅም ይደግፋችኋል ብለዋል።
ለ4ኛጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የህዝብ ለህዝብ መድረክ እስከ ሀምሌ 16 /2009 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ የሚቀጥል ሲሆን በቀጣይ ጎንደር ከተማ ላይ ለማዘጋጀት እንዳስቡ የሀገር ሽማግሌዎቹ አስረድተዋል።