Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኤርትራ መንግስት “ማነህ ባለ ሳምንት?…” ፖሊሲ

0 325

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኤርትራ መንግስት “ማነህ ባለ ሳምንት?…” ፖሊሲ

                                                ዘአማን በላይ

ሁሌም የምስራቅ አፍሪካን ቀጣና በቀውስ ማዕበል ውስጥ ማስገባት የሚሻውና በአንድ ሰው ፍፁም አምባገነናዊ አገዛዝ የሚመራው የኤርትራ መንግስት፤ ከመሰንበቻው የዓለም መነጋገሪያ ርዕስ የሆነውን የባሀረ-ሰላጤውን ሀገራት የፖለቲካ ጡዘት ወደ ራሱ ፍላጎት እየወሰደው ነው። በተለይም ከጂቡቲ ጋር በራስ ዱሜራ ኮረብታዎችና ሐይቆች ሳቢያ በሚያነሳው የድንበር ውዝግብ ኮረብታዎቹንና ደሴቶቹን ላለፉት ስምንት ዓመታት ይዘውት ከነበሩት የኳታር ወታደሮች በኃይል ተረክቦ እዛው ቁጭ ብሏል።

ይህ የሻዕቢያ የራስ ዱሜራን ኮረብታዎችና ሃይቆች የመቆጣጠር ተግባር ለጂቡቲ በሁለተኛ ዙርነት መድረሱ ነው። ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት የጂቡቲ መንግስት “የኤርትራ ወታደሮች ግዛቴን ጥሰው በመግባት ተቆጣጠሩ” ብሎ ክስ ማሰማቱን አስታውሳለሁ። ታዲያ በወቅቱ የአቶ ኢሳያስ አስተዳደር “ወደ ራስ ዱሜራ ኮረብታዎችና ሐይቆች የገባነው ለመንገድ መስሪያ የሚሆን አሸዋና ጠጠር ለማምጣት ነው” ማለቱ ይታወሳል። ጂቡቲም “የኤርትራ ወታደሮች ከራስ ዱሜራ አሸዋና ጠጠር እንውሰድ ብለው በዚያው ወርረውኝ ቀሩ” ማለቷ፤ በቅድሚያ ሻዕቢያ ወደ ጂቡቲ ግዛት የሄደበትን እውነተኛ ምክንያት ያሳየ መስሎ ነበር። ይሁንና የኤርትራ መንግስት ወዲያውኑ “ከጂቡቲ ጋር አለ ስለሚባለው የድንበር ችግር ጉዳይ አናውቅም” ማለቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት አሻክሮታል።

እንደሚታወቀው የጂብቲና የኤርትራ የጋራ የባህር ዳርቻ አዋሳኝ በሆነችው ራስ ዱሜራ ላይ በሁለቱ ሀገሮች መካከል እ.ኤ.አ ሰኔ 2008 ዓ.ም ጦርነት ፈንድቷል። በወቅቱ ጂቡቲ በጦርነቱ 30 ወታደሮች ሲገደሉባት፣ 19 እንደቆሰሉባትና ሌሎች በርካቶች እንደጠፉባት ገልፃ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ጂቡቲ ሁለት ኤር ክራፍቶችን ጨምሮ በርካታ ተሽከርካሪዎችና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ጥይቶች፣ የጦር መሣሪያዎችና ወታደራዊ ቁሳቁሶች እንደወደሙባትም አስታውቃለች። ሻዕቢያ ግን በወቅቱ ስለ ግጭቱ ትንፍሽ ያለው ነገር አልነበረም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፤ የኋላ ኋላ ላይ “ስለ ግጭቱ የምናውቀው ነገር የለም” ቢልም። ያም ሆኖ ሁለቱ ሀገሮች በኳታር መንግስት አደራዳሪነት እ.ኤ.አ ሰኔ 9 ቀን 2010 በይፋ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመዋል። የኤርትራ መነገስት ግን ከ“ውህደት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ግንባር” (ፍሩድ) ተገንጥሎ የተመሰረተውን ተቃዋሚ ድርጅት መርዳቱን ከመቀጠል እንዳልቦዘነ መረጃዎች ያስረዳሉ።

ሻዕቢያ በጂቡቲ ላይ ያደረገውን ወረራ አስመልክቶ ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ)፣ የአፍሪካ ህብረትና የአረብ ሊግ የኤርትራውን መንግስት ቢለምኑና ጥሩ ቀረቤታ አላቸው በሚባሉ ሀገራት ጭምር ቢያስመክሩ ሰሚ ጆሮ አላገኘም። ጉዳዩ የዚያች ትንሽ ሀገር መንግስት ከሚከተለው የጠብ አጫሪነት ፖሊሲ የመነጨ በመሆኑና ጦርነትን እንደ አንድ የገቢ ማስገኚያ ዘዴ ስለሚጠቀምበት “ማነህ ባለ ሳምንት?…” በሚል ዘይቤ የተደረገ በመሆኑ በኤርትራ በኩል እንደ ትክክለኛ አሰራር የሚቆጠር ነበር፤ ነውም። ሻዕቢያ ከጂቡቲ ቀደም ሲል የመንን፣ ሱዳንንና ኢትዮጵያን በቀጥተኛና በእጅ አዙር ፀረ-ሰላም ሃይሎች በመመልመል፣ በማደራጀትና በማሰልጠን እንዲሁም ወደ ሀገራቱ አስርጎ ለማስገባት በመሞከር አዳርሷቸዋል። “ባለ ሳምንት” ወረፈኛው ጂቡቲ ስለነበረችም በወቅቱ የማንንም ምልጃ ሊሰማ አይችልም።

በእኔ እምነት አስገራሚው ጉዳይ በአሁኑ ወቅት በኤርትራ መንግስት ወታደሮች ጂቡቲ ለሁለተኛ ጊዜ ወረፋ የደረሳት መሆኑ ነው። ምናልባትም የኤርትራ መንግስት ያለፉት ወረራዎቹን ለሁለተኛ ጊዜ እየደገማቸው ከሆነ፤ ምንም እንኳን የመን ዛሬ ላይ እጅግ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ላይ ብትገኝም፤ የመንን ተዘዋዋሪ መንገድ ቀደም ሲል በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተወሰነላትን “የሃኒሽ ደሴቶችን” ወስዷቸው ሊሆን አለመቻሉን በርግጠኝነት መናገር አይቻልም። በሱዳን ውስጥ “የቤጃ እንቅስቃሴ” እየተባለ የሚጠራውን አማፂ ቡድን ዳግም ለሚፈልገው ዓላማ በማስፈራሪያነት እንደማይጠቀም፣ በኢትዮጵያም ላይ አስመራ ውስጥ የሰበሰባቸውን ፀረ-ሰላም ሃይሎችንና አሸባሪዎችን እያጠናከረ በማሰማራት (መዘዙ የከፋ ስለሚሆንበት ጦርነት ያካሂዳል ብዬ አላስብም) በድንበር አካባቢ የሚገኙ ዜጎቻችንን ከማወክ ወደ ኋላ ይላል ብሎ መገመት አይቻልም። ጂቡቲም ላይ የመንግስታቱ ድርጅት አጣሪ ቡድን በአንድ ወቅት እንደገለፀው “ፍሩድ” ከተሰኘው ቡድን የተገነጠለውን አማፂ ማሰማራቱን ያቆ አይመስልም። ይህም የሀገሪቱን ኃይል በመከፋፈል ራስ ዱሜራ ላይ ተቆናጥጦ እንዲቀመጥ እድል የሚሰጠው ይመስለኛል።      

በኤርትራ መንግስት ለሁለተኛ ዙር ጂቡቲ ላይ የተካሄደው የድንበር ጥሰት “ማነህ ባለ ሳምንት?…” በሚል የሻዕቢያ በወረፋ ሀገራትን የማጥቃት ፖሊሲ በመሆኑ ብዙም የሚደንቅ አይደለም። ሻዕቢያ በባህሪው ቀጣናውን እስካተራመሰለት ድረስ ከማንኛውም ሃይል ጋር ተቆራኝቶ ሁከት ሊፈጥር እንደሚችል የትናንት ማንነቱ አፍ አውጥቶ ይናገራል። እንደሚታወቀው የኤርትራ መንግስት በሶማሊያ ውስጥ የነበረውን ጣልቃ ገብነት እንዲያጣራ የተመደበው ቡድን የኤርትራ መንግስት የአል ቃዒዳ የምስራቅ አፍሪካ ክንፍ ከሆነው አሸባሪው አልሸባብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ማስታወቁ አይዘነጋም። እንዲያውም ይኸው የሽብር ቡድን ኬንያ በሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ አማካኝነት በየወሩ 80 ሺህ ዶላር ቀለብ እየተቆረጠለት ሽብርን ሲያስፋፋ እንደነበር የሻዕቢያ ድርሳነ-ታሪክ ይናገራል።

ምን ይህ ብቻ። የኤርትራ መንግስት ይህን የሽብር ቡድን ከአንዴም ሁለቴ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ሲቀብል እንደነበር የአጣሪ ቡድኑ መረጃዎች ያስረዳሉ። ከዚህ በተጨማሪ አጣሪ ቡድኑ በወቅቱ የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵንና የጅቡቲን ታጣቂ ቡድኖች እንደሚረዳ ለቀረበለት ጥያቄ ምንም ዓይነት መረጃ ለመስጠት አለመፍቀዱን ገልጿል።

ርግጥ የኤርትራ መንግስት ለዓለም አቀፉ ህግ የሚገዛ አይደለም። አሁንም የመንግስታቱን ድርጅት አጣሪ ቡድን ዋቢ አደርጋለሁ። ኤርትራ ለእነዚህ ኃይሎች የሚታደርገው ድጋፍ በግርድፉ በአራት ሊከፈሉ ይችላሉ። አንደኛው የተመድ ውሳኔን 1844 (2008) እና 1907 (2009) በመጣስ ለሶማሊያ ታጣቂ ተቃዋሚዎች የሚደረግ ድጋፍ፣ ሁለተኛው ውሳኔ 1844 (2009) እና 1907 (2009) በመተላለፍ በሶማሊያ አማካኝነት የኢትዮጵያ ታጣቂ ተቃዋሚ ቡድኖችን ለመርዳት የሚደረግ ዕርዳታ፣ ሶስተኛው ውሣኔ 1907 (2009) በመተላለፍ ሶማሊያዊ ባልሆኑ ሰዎች የተቋቋሙ ተቃዋሚ ታጣቂ ቡድኖችን በመርዳት የሚደረጉ ጥሰቶች ሲሆኑ፤ አራተኛው ደግሞ በኤርትራ አገዛዝና ቁጥጥር ስር የዋሉ ሃይሎችን እንደ የውስጥ ተቃዋሚ ቡድኖች አድርጎ በሃሰት በማደራጀትና ውሳኔ 1907 (2009) መጣስ ናቸው።

እነዚህ ጥሰቶች የሚያሳዩት ነገር ቢኖር የኤርትራ መንግስት ለየትኛውም ቀጣናዊም ይሁን አህጉራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ህግ የማይገዛ መሆኑን ነው። ሰሞኑን በጂቡቲ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የቃጣውን ወረራ ለመሸምገል የአፍሪካ ህብረት የመደበው የእውነት አፈላላጊ ቡድንን የኤርትራ መንግስት በለመደው የማን አለብኝነት ባህሪው እንዳልተቀበለው መረጃዎች ይጠቁማሉ። ምንም እንኳን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ህብረቱ ቀጣይ ጥረቶችን የሚያደርግ ቢሆንም፤ ጉዳዩ ከሻዕቢያ ባህሪ አኳያ መታየት እንደሚኖርበት እዚህ ላይ መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል።

ያም ሆኖ አሁንም ቢሆን የአስመራው መንግስት ለቀጣናው ፀረ-ሰላም ሃይሎችና አሸባሪዎች የሚያደርገው ድጋፍ፤ ከብሔራዊ የደህንነት ፅህፈት ቤት፣ ከኤርትራ ወታደራዊና ከህግደፍ (ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ) አመራሮች በተውጣጡ አነስተኛና ከፍተኛ መኮንኖች በተመሰረተ ቡድን እንዲሁም በቀጥታ በፕሬዚዳንቱ ፅሕፈት ቤት አዛዥነት የሚመራ መሆኑን አጣሪ ቡድኑ ማስታወቁ አይዘነጋም። ይህም ሻዕቢያ ምስራቅ አፍሪካን ለማተራመስ ፀረ-ሰላም ሃይሎችንና አሸባሪዎችን በሁሉም መስኮች በመደገፍ የቀጣናውን ሀገራት ለማተራመስ በመንግስትና በፓርቲ ደረጃ ምን ያህል ተደራጅቶ እንደሚሰራ የሚያሳይ ነው።

በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር የዛሬ 19 ዓመት ባደረገው ጦርነት በግንባር ላይ የፊት ለፊት ውጊያ የተጎነጨው የሽንፈት ፅዋ ሁሌም እያንገበገበው በሀገራችን ላይ ለባዕዳን ያደሩ ፀረ ሰላም ሃይሎችንና አሸባሪዎችን እያደራጀ፣ እያሰለጠነና አስርጎ ለማስገባት እየሞከረ ሰላማችንን ለማወክ ያልጣረው ነገር የለም—ከንቱ ጥረቱ በሀገራችን ሰላም ወዳድ ህዝብና በመንግስት የተቀናጀ ጥረት ሊሳካ አልቻለም እንጂ። ከዚህ አኳያ ሻዕቢያ ራሳቸውን “ግንቦት ሰባት”፣ “ኦነግ” እና “ኦብነግ” የተሰኙ አሸባሪዎችን እንዲሁም አንድም ሆነ ሁለት አባላት ያሏቸው ፀረ-ሰላም ሃይሎችን በራሱ ወጪ አደራጅቶ የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ሰላም ለማወክ ያደረገውንና እያደረገ ያለውን ጥረት ማስታወስ የሚቻል ይመስለኛል።

ታዲያ ይህን መሰሉ የኤርትራ መንግስት የጠብ አጫሪነት ተግባር የሚሰምርለት አይመስልም። በሻዕቢያ የተደራጁ ፀረ ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች በተለያዩ ወቅቶች የኤርትራን መንግስት ተልዕኮ በመተው በሰላም ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ነው። በአቶ ሞገስ አስገዶም ይመራ የነበረው “ደምሕት” እንዲሁም ሰሞኑን ራሱን “የቤኒሻንጉል ነፃነት ንቅናቄ” (ቤነን) እያለ የሚጠራው ቡድን በኤርትራ ቆይታው የሻዕቢያን ማንነት በመገንዘቡ 95 አባላቱን ይዞ በሰላም ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ከብዙ በጥቂቱ በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። እንዲህ ዓይነቱ የፀረ-ሰላም ኃይሎችና የአሸባሪዎች በሰላም ወደ ሀገራቸው መጥተው ከህዝባቸው ጋር በመቀላቀል የልማቱ ተቋዳሽ መሆን መቻላቸው ለኤርትራ መንግስት ጥሩ ምልክት ነው ማለት ይቻላል። ይህ ማለት ግን አሁንም ቢሆን የኤርትራ መንግስት ችግር ሊፈጥር አይችልም እያልኩ አይደለም። በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ሀገራችን ተዳክማ ማየት የረጅም ጊዜ ህልሙ በመሆኑ የትርምስ ሴራውን አይተውም። ይህ ሁኔታ ደግሞ በተለይ ከሻዕቢያ ጋር ተጎራባች ለሆኑ የሰሜን ሀገራችን ህዝቦች “ከቁልቋል ጋር የተጠጋ አጋም” እንዲሉ ፈተና መሆኑ አይቀርም። እናም የኤርትራ መንግስት “ማነህ ባለ ሳምንት?..” ፖሊሲ ሰለባ ላለመሆን ከዚህ በፊት ከነበረው ጥንቃቄ በላይ ጥንቁቅ መሆን እንደሚገባ እዚህ ላይ ሳልጠቅስ አላልፍም።   

 

  

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy