Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምና የፊንፊኔ ህገ መንግሥታዊነት

0 559

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምና የፊንፊኔ ህገ መንግሥታዊነት

ኢብሳ ነመራ

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2009 በጀት ዓመት የስራ ዘመኑን አብቅቶ ሰኔ 30፣ 2009 ዓ/ም ለእረፍት ተበትኗል። በእለቱ የ2010ን በጀት አጽድቋል። በ2009 ዓ/ም የስራ ዘመኑ ያጸድቀዋል ተብሎ ተገልጾ የነበረውን የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገመንግሥታዊ ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ህዝብ ሊወያይበት ይገባል በሚል በጥድፊያ ከማጽደቅ ተቆጥቧል። ረቂቅ አዋጁን ለህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ቋሚ ጉዳዮች መርቶታል፤ ሞያዊ ትንተና ተካሂዶበት ተሞርዶ እንዲቀርብ። ረቂቅ አዋጁ በቀጣይ ዓመት ህዝብ እና/ወይም ባለድርሻ አካላት ይወያዩበታል ተብሎ የጠበቃል።

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገመንግሥታዊ ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ መነሻ በማድረግ አንድ ቤት የሚሰሩ ሳር አይሻሙም በሚል ርዕስ አቅርቤ በነበረው ጽሁፍ ላይ እንደገለጽኩት፣ ጉዳዩ የተለያየ ጽንፍ ላይ የሚገኙ ቡድኖች (በአንድ ወገን በብሄር ላይ የተመሰረተውን ፌደራሊዝም የሚቃወሙ የአሃዳዊ ስርአት ደጋፊዎች፣ በሌላ ወገን መገንጠልን መድረሻ አድርገው የሚንቀሳቀሱ የኦሮሞን ህዝብ እንወክላለን የሚሉ ቡድኖችና ገለሰቦች) ለየራሳቸው ዓላማ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚጓተቱት ስስ (sensitive) አጀንዳ ነው።

የአሃዳዊ ስርአት ደጋፊ ቡድኖችና ግለሰቦች ሰሞኑን ያሰሙን ተቃውሞ፣ የረቂቅ አዋጁ  ድንጋጌዎች ላይ የሰፈሩ፣ የኦሮሚያ ወይም የኦሮሞ ብሄር አባላት በአዲስ አበባ ላይ ያላቸው ልዩ ጥቅም፣ በአዲስ አበባ ውስጥ በሚኖሩ የሌሎች ብሄሮች አባላት መስዋዕትነት ሊሰጥ የታሰበ ነው የሚል ቃና ያለው አጀንዳ ላይ ያጠነጠነ ነው። መነሻ ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ባላውቅም ህዝቡን እርስ በርስ ለማጋጨት የታለመ ነው የሚል በእኔ አስተያያት በጣም እንጭጭ ሃሳብ ሲሰነዘሩ የነበሩ የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞችም ነበሩ።

በዚህ እንጭጭ ሃሳብ ላይ አስተያየት መስጠት አስፈላጊ አይመስለኝም። በተለይ በሌሎች ብሄሮች አባላት መስዋዕትነት ኦሮሚያን እና/ወይም ኦሮሞዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል የሚለውን አጀንዳ በተመለከተ አንድ ቤት የሚሰሩ ሳር አይሻሙም በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ጽሁፌ ላይ ለዚህ ስጋት ከዳረጓቸው የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌዎች መሃከል አወዛጋቢ ይመስላሉ ብዬ የገመትኳቸውን አንድ ሶስት ጉዳዮች አንስቼ አስተያየት ሰጥቼበታለሁ። አሁን ደገሜ አላቀርበውም።

በዚህ ጽሁፍ በሌላኛው ጽንፍ ያሉት ወገኖች በረቂቅ አዋጁ ላይ ያሰሙት ቅሬታ ወይም የተቃውሞ ማጠንጠኛ አጀንዳ ላይ አተኩራለሁ። ይህም ረቂቅ አዋጁ የኦሮሚያን እና/ወይም የኦሮሞዎችን ‘ልዩ ጥቅም’ ያስጠበቀ አይደለም፤ ድሮምም ሊጠበቅላቸው ይገባ የነበረ ጥቅማቸውን/መብታቸውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የያዘ ነው፣ ረቂቅ አዋጁ ምንም አዲሰ ነገር የለውም፣ . . . የሚል ነው። ረቂቅ አዋጁ ለኦሮሚያ/ኦሮሞዎች ምንም ጥቅም አያስገኝም ወይም ይጎዳል የሚል ተቃውሞ ግን አልቀረበም ወይም እኔ አልሰማሁም። ከዚሁ ጋር አያይዤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስተዳደራዊ ራስ ገዝ ስልጣን ያለውን አዲስ አበባ ርዕስ መዲናው ለማድረግ ያስቻለው ህገመንግስታዊ መሰረት ምንድነው? በሚል በአንዳንድ ወገኖች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ይሆናል ብዬ ያመንኩበትን አስተያየት እሰጣለሁ።

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገመንግሥታዊ ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በርካታ ጉዳዮችን የያዘ ነው። ለማስታወስ ያህል  አዲስ አበባ ውስጥ ስለሚደራጁ በኦሮሚኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች፣ ኦሮሚኛ በአዲስ አበባ ውስጥ ከአማርኛ በተጋዳኝ የስራ ቋንቋ ሆኖ ስለሚያገለግልበት ሁኔታ፣ በአዲሰ አበባ ውስጥ ለሚኖሩ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ሰራተኞች በእጣ ኮታ የኮንዶሚኒየም ቤት እድል ስለሚያሚያገኙበት ሁኔታ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኦሮም ህዝብን ባህልና ታሪክ የሚያንፀባርቁ የባህልና ታሪክ ማዕከላት፣ ቲያትር፣ ኪነ ጥበባትና የመዝናኛ ማዕከላት የሚገነቡበትና የሚተዋወቁበትን ሁኔታ የሚያመቻች ስለመሆኑ፣ “ፊንፊኔ” እና “አዲስ አበባ” የሚሉት የከተማዋ መጠሪያዎች በህግ ፊት እኩል ስለሚያገለግሉበት ሁኔታ፣ ስለ የውሃ አቅርቦት፣ ስለፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች አወጋገድ፣ ስለ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ በከተማዋ ዙሪያ (የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን) ነዋሪዎች የስራ እድል ተጠቃሚ ስለሚሆኑበት ሁኔታ፣  ለፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አርሶ አደሮች በከተማ ውስጥ የገበያ ማዕከላት ስለማቋቋም፣ በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ከመሬታቸው ላይ ለልማት ሲነሱ በቂ ካሳ የማግኘትና በዘላቂነት የማቋቋም አገልግሎት ስለሚያገኙበት ሁኔታ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለተለያዩ መንግስታዊ ስራዎችና ህዝባዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ህንጻዎችን ለመገንባት ሲፈልግ መሬት ከሊዝ ነጻ ማግኘት ስለሚችሉበት ሁኔታ ወዘተ የሚመለከቱ ናቸው።

ረቂቅ አዋጁ የኦሮሚያን እና/ወይም የኦሮሞዎችን ልዩ ጥቅም አላስጠበቀም የሚሉት ወገኖች ከላይ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች ድሮም ሊጠበቁና ሊከበሩ የሚገባቸው ናቸው፤ ልዩ ጥቅም አይደሉም ባዮች ናቸው። እኔ እሰከሚገባኝ ደረስ የህገመንግስቱ አንቀጽ 49 ንኡስ አንቀጽ 5 ላይ የሰፈረው በኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃከል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። የሚለው ድንጋጌ ለኦሮሚያ እና/ወይም ለኦሮሞዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም የሌለውን ልዩ መብት የመስጠት ዓላማ ያለው አይደለም።

ለኦሮሚያና ለኦሮሞዎች የሚሰጡት ጥቅሞችና የሚጠበቁት መብቶች በየትኛውም አካባቢ የሚኖር፣ ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን ሊከበሩለት የሚገቡ ናቸው። በረቂቅ አዋጁ ላይ የሰፈሩ ጥቅሞች በሌሎች አዋጆችና ደንቦችም ላይ የሰፈሩ ናቸው። በተወሰ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉና ሲጓደሉ ጥያቄ ሲነሳባቸው የቆዩም አሉ። የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ የሚሞከርባቸውም አሉ።  የተቀሩት ደግሞ ነባራዊው ሁኔታ እስኪፈቅድና የአፈጻጸም ደንብ እስኪወጣላቸው ጊዜያቸውን በመጠበቅ ላይ ያሉ ናቸው።

ከአዲስ አበባ ጋር በተያየዘ ሊከበሩና ሊጠበቁ ይገባል ተብለው ህገመንግስቱን መነሻ በማደረግ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተጠቀሱትን የኦሮሚያን እና/ወይም የኦሮሞዎችን ጥቅሞች ልዩ የሚያደርጋቸው፣ የትምና መቼም የሌሉና ያልነበሩ መሆናቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከቡድን መብት ጥበቃ አተገባባር ልዩ ባህሪና አዲስ አበባና ኦሮሚያ ካላቸው ልዩ ግንኙነት የመነጩ መሆናቸው ነው። ልዩ የሚለውን ቅጥያ ያሰጣቸው ይህ ነው።

አንዳንድ የቡድን መብቶች አተገባባር፣ ቡድኑ ወይም ማህበረሰቡ በሚኖርበት አካባቢ የተገደቡ ናቸው። ለምሳሌ በቋንቋ የመስራት፣ የመማር መብት የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ ነው። ወይም ማህበረሰቡ በሌላ ማህበረሰብ ውስጥ በብዛት የሚኖር ሊሆን የሚነሳ ጉዳይ ነው። አሁን ባለው የአዲሰ አበባ ተጨባጭ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የአፋር . . . ማህበረሰቦች በአዲስ አበባ የመንግስት መስሪያ  ቤቶች በቋንቋቸው አገልግሎት የማግኘት፣ ልጆቻቸውን በቋንቋቸው የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤቶች በከተማው አስተዳደር ወጪ እንዲደራጅ መጠየቅ አይችሉም። ልብ በሉ ይህን መብት መቼም ሊጠይቁ አይችሉም እያልኩ አይደለም። በራሳቸው ወጪ በቋንቋቸው የሚያስተምር የማህበረሰብ ትምህርት ቤት የማቋቋም መብት የላቸውም እያልኩም አይደለም።

በሌላ በኩል አዲስ አበባ/ፊንፊኔ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ ከተማ በመሆኗ በርካታ የክልሉ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች በከተማዋ ይኖራሉ። ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባ የነባር የኦሮሞ ህዝብ መኖሪያም ነች። እነዚህ ሁኔታዎች ኦሮሞዎች ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሄሮች በተለየ በከተማዋ ውስጥ የቡድን መብታቸው እንዲከበርላቸው የግድ የሚል ሁኔታን ፈጥሯል። እንግዲህ ልዩ ጥቅም የሚለው ሃሳብ የትም የሌለ፣ መቼም ለማንም ተሰጥቶ የማያውቅ ጥቅምን የሚመለከት ሳይሆን ኦሮሞዎች ከሌሎች ብሄሮች በተለየ በአዲሰ አበባ ከተማ ሊኖራቸው የሚገባ ቡድናዊ መብትና ጥቅም የሚመለከት ነው። ከዚህ አኳያ ስናየው በረቂቅ አዋጁ ላይ የሰፈሩት የኦሮሞዎች ቡድናዊ ጥቅሞችና መብቶች ልዩ ለኦሮሞዎችና ለኦሮሚያ ልዩናቸው። ልዩ ተበለው መገለጻቸውም ትክክል ነው።

ሌሎቹ ልዩ ጥቅሞች ደግሞ ኦሮሚያ ከሌሎቹ ክልሎች በተለየ ከአዲስ አበባ ጋር ካለው ግንኙነት ወይም ትስስር የመነጩ ናቸው። የአዲስ አበባ  ከተማ አስተዳደር ከ10 እሰከ 12 ኪሎ ሜትር  ሬዲየስ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተከቦ ያለ ስፍራ ነው። ይህ ሁኔታ የአዲስ አበባ የውሃ አቅርቦት በኦሮሚያ ላይ ጥገኛ እንዲሆን አድርጎታል። ከፍተኛውን የአዲስ አበባ የውሃ ፈላጎት የሚሸፍኑት የገፈርሳና የለገ-ዳዲ ግድቦች ኦሮሚያ ውስጥ ነው የሚገኙት። በቅርቡ የተቋቋሙት የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ መሰረተ ልማቶችም በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልለ ውስጥ ነው የሚገኙት። አዲስ አበባ የዚህ አይነት ግንኙነት ያላት ከኦሮሚያ ጋር ብቻ ነው፤ ከአማራም፣ ከትግራይም፣ ከኢትዮጵያ ሶማሌም . . . ጋር የዚህ አይነት ግንኙነት የላትም።

ለምሳሌ የአዲስ አበባ የውሃ መስመር በሚያልፍባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች በከተማ አስተዳደሩ ወጪ የውሃ አቅርቦት የማግኘትን በረቂቅ አዋጁ ላይ የሰፈረ ጉዳይ ጥቅም ልዩ ያደረገው ይህ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ መሃከል ያለ ከመገኛ ስፍራ የመነጨ ልዩ ግንኙነት ወይም ትስስር ነው። የአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ ለማስወገጃነት የተዘጋጀው ቦታ ኦሮሚያ ውስጥ ነው የሚገኘው፤ ከአዲስ አበባ 43 ኪሎ ሜትር ርቆ በፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ሰንዳፋ አካባቢ። በተለያየ ቆሻሻ የተበከሉት የአዲስ አበባ ወንዞች የሚፈሱት ወደኦሮሚያ ነው። እናም ከአዲስ አበባ ከተማ የሚወገድ የደረቅም ሆነ የፍሳሽ ቆሻሻሻ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ከማንኛውም ክልል በተለየ ኦሮሚያን የሚመለከት ነው። ኦሮሞዎች ነባር አዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው። የአዲስ አበባ ከተማ ሲስፋፋ ለመፈናቀል የሚጋለጡት እነዚህ የከተማዋ ነባር ነዋሪ የሆኑ ኦሮሞዎች ናቸው። ይህ ጉዳይ አማራን፣ አፋርን፣ ትግራይን . . . አይመለከትም፤ ኦሮሚያንና ኦሮሞዎችን እንጂ። በአጠቃላይ ልዩ ጥቅም የሚለው ከእነዚህና መሰል በአዲሰ አበባና በኦሮሚያ መሃከል ካሉ ግንኙነቶች የመነጩ መሆኑን እንጂ ማንም የሌለውን መብትና ጥቅም የሚያመለክት አይደለም።

የኦሮሚያ ከተማ አዲስ አበባን የክልሉ ርዕሰ መዲና አድርጎ መምረጥ ያስቻለው ህገመንግስታዊ መሰረት ምንድነው? ወደሚለው ጥያቄ እንመለስ። በነገራችን ላይ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የምታገኘውን ልዩ ጥቅም የሚመለከት አዋጅ ማውጣት ያስፈለገው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መዲና ፊንፊኔ በመሆኗ አይደለም። የክልሉ ከተማ የትም ቢሆን ኦሮሞዎች በአዲስ አበባ ላይ ያላቸው የባለሃገርነት መብትና በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መሃከል ያለው ትስስር አይቀርም።

በመሰረቱ አሁን አዲስ አበባ የሚባለው አካባቢ ቢያንስ ላለፉ 4 መቶ ዓመታት የኦሮሞዎች መኖሪያ ምድር ነበር። አንድ አካባቢ የአንድ ህዝብ ነባር መኖሪያ ምድር ለመባልና የባለሃገርነት ባለመብት ለመሆን ይህን ያህል የመኖር የታሪክ ዘመን ከበቂ በላይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከዚያ ቀደም ምናልባት የማንም መኖሪያ ያልነበረ መሬት ነው። እናም ፊንፊኔና አካባቢው ወይም የአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሞዎች ሃገር መሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም።

ይሁን እንጂ፣ ይህ ምድር ባለፉት መቶ ዓመታት የኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና መሆኑ ከተለያያ ያሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ብሄሮችና ብሄረሰቦች በከተማዋ እንዲሰፍሩ አድርጓል። ይህን ተከትሎ በተለይ በከተማዋ መሃከለኛ አካባቢ በዘውዳዊው ስርአት ማንነትና የከተሜነት ባህል እንዲሁም ልዩ የከተማ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የተቀረጸ የተለየ ባህሪ ያለው ማህበረሰብ እንዲፈጠር አድርጓል። ይህ በስርአቱ ቋንቋና ባህል የተቀረጸው ማህበረሰብ ኦሮሞዎችንም ያጠቃልላል።  ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ከተማም ነች።

ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብ ገዢዎቹ በመረጡለት ሳይሆን ራሱ በሚፈልገው መንገድ ለመተዳዳር በህገመንግስት በወሰነባቸው ያለፉ ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ልዩ ባህሪ ያላት አዲስ አበባ በቻርተር የምትደዳር ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግስት የሆነ ከተማ እንድትሆን የግድ በሏል። ይህ ሁኔታ ግን ከተማዋ የኦሮሞዎች ነባር መኖሪያና ከመልከዓምድራዊ አኳያ በኦሮሚያ ውስጥ የምትገኝ መሆኑን አልቀየረውም።

በመሆኑም ኦሮሞዎች በኢፌዴሪ ህገመንግስት መሰረት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን ሲያደራጁ ሊገሰስ የማይችል የባለሃገርነት መብት ያላቸውን እንዲሁም ክልሉን ለማስተዳደር አመቺ የሆነ ስፍራ ላይ የምትገኘዋን ፊንፊኔ መረጡ። ይህን በክልላዊ ህገመንግስታቸው አንቀጽ 6 ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ ፊንፊኔ ነው ብለው ደነገጉ። ፊንፊኔ የሚለው ስያሜ ነባር የከተማዋ ማዕከላዊ ቦታ መጠሪያ ነው። የክልሉ መንግስት ፊንፊኔን ርዕሰ ከተማው ለማድረግ ሲወስን ምንም ታሪካዊና ተጨባጭ መሰረት የሌለውን ቦታ በዘፈቀደ እንዳልመረጠ ልብ ሊባል ይገባል።

በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብ የባለሃገርነት መብት የሌለውን የማያገባውን ቦታ በማን አለብኝነት ለርዕስ ከተማነት እንደመረጠ አድርጎ ለመውሰድ የሚያበቃ አንዳችም ምድራዊ ምክንያት የለም። የኢፌዴሪ ህገመንግስት በገዚዎች የተሰጠ ሳይሆን ከህዝብ የመነጨ በመሆኑ ኦሮሞዎች ፊንፊኔን ርዕሰ ከተማቸው አድርገው እንዳይመርጡ ሊከለክላቸው እንደማይችልም መታወቅ አለበት። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ ከተማ ፊንፊኔ/አዲስ አበባ እንዲሆን መወሰኑን አስመልክቶ የኢፌዴሪ ህገመንግስት ላይ ምንም የሚከለክል ድንጋጌ ያልሰፈረው ለዚህ ይመስለኛል።

የኢፌዴሪ ህገመንግስት አዲስ አበባ ከፌደራል መንግስት እና/ወይም ከከተማዋ አስተዳደርና ዓለም አቀፍ ተቋማት ውጪ ሌላ አካል ወይም የከተማዋ ነባር ህዝብ የመሰረተው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ ከተማ ሆና ማገልገል አትችልም የሚል፣ ይህን በጨረፍታ እንኳን የሚያመለክት ድንጋጌ የለውም። በመሆኑም በህገመንግስቱ ተለይቶ ያልተከለከለን ነገር የህገመንግስት መሰረት እንደሌለው መወሰድ አይቻልም። ተለይቶ ያልተከለከለ ነገር ሁሉ እንደተፈቀደ ይቆጠራልና።

ከዚህ በተጨማሪ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ ፊንፊኔን ወይም አዲስ አበባን ርዕሰ ከተማው ማደረጉ፣ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ከተማ ማግኘት እንደሚገባው ህገመንግስታዊ ልዩ ጥቅም አዋጅ ውስጥ ሊካተት የሚችልበት እድል መኖሩም መዘንጋት የለበትም። አዋጁ ገና ለህዝብ ውይይት እንደሚቀርብ ልብ በሉ። እናም ፊንፊኔ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መዲና እንድትሆን መወሰኑ ህገመንግስታዊ ነው። ቢያንስ በህገመንግስቱ አለመከልከሉ ሊታወስ ይገባል።

በአጠቃላይ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገመንግሥታዊ ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ በትክክል የኦሮሚያ ክልልና የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች በተለየ ሊኖረው የሚገባውን ልዩ ተጠቃሚነት የሚገልጽ ነው። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፊንፊኔን ርዕሰ ከተማው እንዲሁን በክልላዊ ህገመንግስቱ መወሰኑም የኢፌዴሪን ህገመንግስት መርሆች መሰረት ያደረገ ነው።  

   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy