Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የግብር ግዴታን መወጣት የሞራልና የህግ አቅም ይፈጥራል

0 829

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የግብር ግዴታን መወጣት የሞራልና የህግ አቅም ይፈጥራል

ብ. ነጋሽ

የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፈው ዓመት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ወደተቃውሞነት ያደገ ቅሬታ ሲገልጽ እንደነበረ ይታወሳል። በዚህ ወደተቃውሞነት አድጎ በነበረ ቅሬታ ከተነሱ ጥያቄዎች መሃከል የልማት ጥያቄ ቀዳሚው እንደነበረ ይታወሳል። ተቃውሞውን ተከትሎ መንግስት ከህዝብ ጋር ባካሄደው ውይይት የውሃ፣ የኤሌትሪክ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመስኖ መሰረተ ልማት ወዘተ ይሟላላን የሚሉ ጥያቄዎች በብዛት ተሰምተዋል። መንግስት በተለይ ተጀምረው የተጓተቱትንና የተቋረጡትን የመሰረተ ልማቶች ለማስጨረስ፣ አቅም በፈቀደ መጠን አዳዲስ ግንባታዎችን በማስጀመር ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ቃል ገብቶ ነበር።

መንግስት የህዝብን ፍላጎት የሚያሟሉና የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ቃል የገባቸውን በተለይ የተጓተቱና የተቋረጡ የልማት ፕሮጀከቶችን ለማሰቀጠልና ለማስጨረስ ተንቀሳቀሷል። በዚህ ረገድ በ2009 በጀት ዓመት አርኪ ባይባልም ጥሩ ወጤት ተገኝቷል። አሁንም የኤሌትሪክ መቆራረጥ፣ የውሃ አቅርቦት ችግር፣ የስራ አጥነት ችግር አለ።

ከዚህ በተጨማሪ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝብ በቦንድ ግዢ ያቀረበው ብድር ቢኖርም፣ ግንበታው በአብዛኛው መንግስት በየዓመቱ በሚመድበው ባጀት ነው የሚከናወነው። ከዚህ ባሻገር ግድቡ እንደተጀመረ ህዝብ በቦንድ ግዢ ያበደረው ገንዘብ የአምስት ዓመት የመመለሻው ወቅት ስለደረሰ መንግስት ከነወለዱ እየከፈለ ይገኛል። ሌሎች በከፊል በመንግስት ባጀት የሚከናወኑ ሜጋ ፕሮጀከቶችም አሉ። ኢኮኖሚው እያደገ በሄደ መጠን ህዝቡ የበለጠ የልማት ጥያቄ እያነሳ ይገኛል። የስራ አጥነት ችግርም መንግስትን አስጨንቆ የያዘ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

መንግስት እነዚህንና ሌሎች የኢኮኖሚው እድገትና ልማት የግድ የሚላቸውንና በተለይ ህዝብ “አሟላልኝ” በሚል ከምሬትና ቁጣ ጋር የሚያቀርባቸውን የልማት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ለመመለስ በቂ የልማት ባጀት መመደብ ይጠበቅበታል።

ይህ የልማት ባጀት በግብር የሚሰበሰብ ነው። መንግስት በግብር መልክ ከሚሰበሰብ ገንዘብ ውጭ ሌላ የራሱ የገንዘብ ምንጭ የለውም። በግብር መልክ ከህዝብ የሚሰበሰበው ገንዘብ ሲያጥረው የልማት እቅዶቹን ለማሳካት ከሃገር ውስጥና ከውጭ የገንዘብ ምንጮች ይበደራል። በብድር የሚገኘው የልማት ገንዘብም ቢሆን ግን ዞሮ ዞሮ ያሀገር እዳ ነው። እርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ የሚያገኘውን ብድር በቀጥታ ኢኮኖሚውን ማሳደግ ለሚያስችሉ የልማት ፕሮጀከቶች ኢንቨስትመንት ስለሚያውለው፣ የልማት ፕሮጀክቶቹ የሚያመነጩት ሃብት ብድሩን ይከፍላል። በመሆኑም የህዝብ እዳ አይሆንም።

ያም ሆነ ይህ፤ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በሚፈልገው ልክ በማሳደግ የህዝቡን ተጠቃሚነትና የተሻለ ህይወት ለማረጋገጥ መንግስት በተለይ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ማከናወን ይኖርበታል። ማህበራዊ ልማትን በብዛትና ጥራት ማስፋፋት ይኖርበታል። ለዚህ የሚሆነውን በጀት እንዲያገኝ በተለያየ ስራ ላይ ተሰማረተው ሃብት የሚያመነጩና ገቢ የሚያገኙ ዜጎችና የንግድ ተቋማት በተገቢው መጠን ግብር መክፈል ይኖርባቸዋል።

እንግዲህ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉ ሁለት አስርት ዓመታት መንግስት መጠነ ሰፊ የልማት ስራ ማከናወኑ ይፋ እውነት ቢሆንም፣ የሃገሪቱ የግብር አሰባሰብ ግን እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የ2009 በጀት በጸደቀበት እለት ለለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ይህን ጉዳይ አንስተው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ሃገሪቱ የምትሰበስበው ዓመታዊ ግብር ሃገሪቱ ከምታመነጨው ዓመታዊ አጠቃላይ ሃብት 12 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል። ከኢትዮጵያ ጋር ተመጣጣኝ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ አጎራባች ሃጋራት የአጠቃላይ ዓመታዊ ሃብታቸውን እስከ 17 በመቶ ግብር እንደሚሰበስቡም በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል። መረጃዎች እንደሚመለክቱት የአውወሮፓ ሃገራትና አሜሪካ  ከሚያመነጩት አጠቃላይ ዓመታዊ ሃብት እስከ 45 በመቶ የሚደርስ ግብር ይሰበስባሉ።

በዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት ደረጃ ላይ የሚገኙት ከሳህራ በታች ያሉ ሃገራት ከሚያመነጩት አጠቃላይ ዓመታዊ ሃብት እስከ 20 በመቶ ግብር እንደሚሰበስቡ መረጃዎች ያሳያሉ።  ከሳህራ በታች ከሚገኙ ሃገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ከላይ እንደተጠቀሰው የምትሰበስበው ግብር የምታመነጨውን ዓመታዊ አጠቃላይ ሃብት 12 ነጥብ 5 በመቶ ገደማ ብቻ ነው።

ይህ በኢትዮጵያ፣ ከግብር የሚሰበሰበው የመንግስት ገቢ፣ ከሃገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ሃብት ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል በዝቅተሻ መጠን ላይ እንደሚገኝ ይመሰክራል። ይህ በሃገሪቱ  ግብር የማይሰበሰብበት ትልቅ ሃብት መኖሩን ያመለክታል።

መንግስት በግብር መልክ እሰበሰበዋለሁ ብሎ ያቀደውን ማሟላት እያቃተው መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ለ2010 በጀት ዓመት ከተያዘው 320 ነብ 8 ቢሊየን ብር በጀት ውስጥ 196 ቢሊየኑ ከግብር በሚሰበሰብ ገቢ ለመሸፈን እቅድ ተይዟል። ይሁን እንጂ በ2009 በጀት ዓመት ከታየው የግብር ገቢ አሰባሰብ አፈጻጻም ጉድለት አኳያ፣ በ2010 በጀት ዓመት 196 ቢሊየን ብር መሰብሰብ የመቻሉ ጉዳይ አዳጋች ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል። ከአስር ቀን በፊት በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት ከግብር ገቢ 171 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ነበር የታቀደው። መሰብሰብ የተቻለው ግን 120 ቢሊየን ብር ብቻ ነው።

እንግዲህ፣ የኢፌዴሪ መንግስት በቀጣይነት አጠቃላይ በሃገሪቱ የሚመነጨውን ዓመታዊ ሃብት 17 በመቶ ግብር ለመሰብሰብ አቅዷል። ይህን እቅድ ለማሳካት በያዝነው ዓመት በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰራ የውጭ አማካሪ ኩባንያ ተቀጥሮ እየሰራ ይገኛል። አማካሪ ኩባንያው በኢትዮጵያ አቻ የኢኮኖሚ አቅም ካላቸው አጎራባች የአፍሪካ ሃገራት ጋር የሚመጣጠን የአጠቃላይ ሃገራዊ ዓመታዊ ሃብት 17 በመቶ ግብር መሰብሰብ የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩን አመልክቷል።

በሃገሪቱ የሚሰበሰበውን ግብር ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት 17 በመቶ ለማደረስ የግብር መሰረቱን ማስፋት፣ ሁሉም ገቢ አመንጪዎች በግብር መረብ ውስጥ እንዲታቀፉ ማድረግ፣ ግብር የመክፈል አመለካካት እንዲጎለብት ማድረግ ያስፈልጋል።

እስከአሁን እንደሚስተዋለው፣ በኢትዮጵያ ግብር የመክፈል ፍቃደኝነት (በተለይ የነጋዴው ፍቃደኝነት) መንግስት የልማት ስራዎችን እንዲያከናውን የመጠየቅንና ጉድለት ሲገኝ አፋጦ የመያዝን ያህል ጠንካራ አይደለም። በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ የልማት ጥያቄዎችን በማንሳት ቀዳሚ ነው፣ የግብር ነገር ሲነሳ ግን ወገቤን በማለት የሚያህለው የለም። ይህ ተጨባጭ እውነት ነው። በያዝነው ዓመት የተካሄደው የእለታዊ ገቢ ትመና ወጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ይህን በገሃድ ተመልክተናል።

በርካታ ነጋዴዎች የዕለት ገቢ ትመናው መረጃ እንደደረሳቸው ገና የሚከፍሉት ግብር ሳይገለጽ ነበር ተቃውሞ ወደማሰማት የገቡት። የአንድ በሬ ስጋ ጨርሶ የሚውል ሉካንዳ ነጋዴ፣ የቀን ገቢ ግምቱ 10 ሺህ ብር መሆኑን ሲሰማ “ምን ሲደረግ?” ብሎ ዱታ ነኝ ያለበት ሁኔታ አጋጥሟል።

የቀን ሽያጩ 5 መቶ ብር ተብሎ እንዲገመት ነው የሚፈልገው። የአንድ በሬ ዋጋ ምን ያህል እነደሆነ የሚታወቅ መሆኑ እንኳን ትዝ አይለውም። በቀን አስር የወንድ ሱሪ ሸጦ የሚውል የልብስ መደብር ባለቤት፣ የቀን ገቢ ግምቱ 3 ሺህ ብር መሆኑን ሲሰማ “ታይቶ የማይታወቅ ግምት ነው” ብሎ መንግስት ላይ ተቃውሞ እንዲነሳ ሲቀሰቅስ የታየበት ሁኔታ አለ። ሰሞኑን ያጋጠሙ ሌሎችም ብዙ አስገራሚ ነገሮች አሉ። ይህን በቀጥታ ከጉዳዩ ጋር አያይዤ በሌላ ጽሁፍ እመለስበታለሁ።

ያም ሆነ ይህ፣ እነዚህ ሁኔታዎች በሃገሪቱ በተለይ በነጋዴው ህብረተሰብ ዘንድ ግብር የመክፈል ፍላጎት ምን ያህል ዝቅተኛ እንደሆነ ያመለክታሉ። ነጋዴውና ሌላውም ህብረተሰብ በኢትዮጵያ ከሚመነጨው ሃብት ጋር ሲነጻጻር በሃገሪቱ የሚሰበሰበው ግብር እጅግ አነስተኛ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ኢትዮጵያ ከምታመነጨው አጠቃላይ ዓመታዊ ሃብት አንጻር ሲታይ ግብር የማይሰበሰብባት ሃገር ብትባል ብዙም የተጋነነ አይደለም። በተቃራኒው  የመሰረተ ልማት የሟላለኝ ጥያቄው፣ ኩርፊያውና ተቃውሞው ከፍተኛ ነው።

በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ ከገቢ ጋር የሚመጣጠን ግብር መከፈል፣ የሃገሪቱን የህግ የበላይነት በማስከበር ሰላምና መረጋጋት ለማረጋጋጥ፣ እድገትና ልማትን ለማቀላጠፍ፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ለማስቻል የሚከናወን፣ ማንም እምቢ ሊለው የማይችለው የውዴታ ግዴታ መሆኑን ማወቅ አለበት። በትክክል ከገቢው ጋር የማይመጣጣን የገቢ ግብር ሲጣልበት በወረዳ ከሚገኝ የገቢ ባለስልጣን እስከ ፌደራል የገቢዎችና ጉብሩክ ባለስልጣን፣ በዚህም መፍትሄ ካላገኘ እስከጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የማለት መብት እንዳለው በህግ መደንገጉንም ማስታወስ አለበት።  የህግ የበላይነት መረጋገጥንና የመሰረተ ልማት መሟላትን አፍ ሞልቶ መጠየቅ የሚቻለው፣ የግብር ግዴታን ከተወጡ በኋላ ብቻ ነው። የግብር ግዴታውን የተወጣ መብቶቹን የመጠየቅ የሞራልም የህግም አቅም ይኖረዋልና።

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy