የፀረ ሰላም ኃይሎችን አጀንዳ እንመክት!
ደስታ ኃይሉ
የአገራችንን ልማትና ዕድገት ማየት የማይፈልጉና ለባዕዳን በመላላክ አገራችን ውስጥ አለመግባባትና ግጭት እንዲፈጠር ማንኛውንም አጀንዳ ሲጠቀሙ እየተስተዋለ ነው። ታዲያ ይህ የፀረ ሰላም ኃይሎቹ ፍላጎት ህዝቦችን ከህዝቦች ጋር ማጋጨት ስለሆነ ይህን እኩይ ተግባራቸውን መመከት ይገባል።
ዛሬ ላይ እነዚህ ፅንፈኞች ባህር ማዶ ቁጭ ብለው የሚያስደምጡን መሪ መፈክርም ማረጋገጫ የሌላቸውን ቅንጭብጫቢ ሃሳቦችን እየገጣጠሙ ማውራት ነው። አንዳንዶቹ በወንጀል የሚፈለጉ አሸባሪዎች ፣ የቀድሞው ስርዓት ናፋቂዎች፣ የሀገራችን ጠላት የሆነው የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች እንዲሁም ከእንቅልፋቸው ብንን ሲሉ ኢትዮጵያ ተበታንና የምትታያቸው ሃይሎች ናቸው። እነርሱ በሚሰበሰቡባት ሀገረ- አሜሪካ አሊያም ሌላ ሀገር ውስጥ ሆነው የሚሰጥዋቸው መሰረተ- ቢስና ዘረኛ አስተያየቶች፤ ቁም ነገር አልባ ከመሆናቸው ባሻገር የኮሜዲያንነት ባህሪይን እየተላበሱ መጥተዋል።
እነዚህ ፖለቲካን የማያውቁ አሊያም ፖለቲካውን ገና ዳዴ እያሉ የሚገኙ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች፡ በሀገረ- አሜሪካ የሚገኙ አንዳንድ የእምነት ተቋማትንና የንግድ ቦታዎችን በፖለቲካና በዘረኝነት ስም እየፈረጇቸው መሆኑን ብትሰሙ ከቶ ምን ትሉ ይሆን?—አዎ! ወጉን ያጫወተኝ ለሃያ ዓመታት አሜሪካ የኖረ አንድ ወዳጄ ሲሆን፤ የወዳጄን ጨዋታ በብዕሬ እንዲህ እንደወረደ አቀርበዋለሁ።…
…አክራሪ ፖለቲከኞቹ በአንድ የእምነት ተቋም አሊያም የንግድ ቦታ ተቀጣጥረው ለመገናኘት ከፈለጉ፤ በዚሁ ሁናቴ ቀጠሮ መያዛቸው አይቀርም። ታዲያላችሁ እኔም ወዳጄን “በምን መልኩ” ማለቴ አልቀረም። እርሱም ለጠቀና እንዲህ አለኝ።… ይኸውልህ በሀገረ- አሜሪካ አንድ ስቴት ሁለት የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ያለ እንደ ሆነ… ጓድ የት እንገናኝ? የቅንጅቱ ወይስ የኢህአዴግ? በማለት ቀጠሮ ይይዛሉ።
ምን ይህ ብቻ!? ንግድ የሚጧጧፍበት ቦታ ለመገናኘት ከፈለጉም በተመሳሳይ መልኩ ቀጠሮ መያዛቸው አይቀርም። እርግጥም ጉዳዩ ያስገርማል። እነዚህ ወገኖች በሰለጠኑት ዓለም እየኖሩ ኃይማኖትን እና ፖለቲካን ንግድን እና ፖለቲካን ለይተው የማያውቁት አክራሪ ኃይሎች ናቸው። እኔን የደነቀኝ እና ያልገባኝ ጉዳይ ግን የእምነት ተቋማት እና የንግድ ቦታዎች በፖለቲካ ስም መሰየም ያስፈለገበት ምክንያት ነው። ግና እነዚህ ፀንፈኛ ሃይሎች በኃይማኖትን ጨምሮ በእያንዳንዱ ጉዳይ ሽፋን ፖለቲካዊ አጀንዳቸውን ለመፈፀም የማይቀነጥሱት የቅጠል ዓይነት እንደሌለ ስለሚታወቅ ነገረ-ስራቸው እምብዛም እንደማይደንቅ ይኸው ወዳጄ አጫውቶኛል።
ፅንፈኞቹ ለሀገር የሚመኙት ምርጥ እቅድ እና ኘሮግራም፣ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ መንደፍን ሳይሆን ብሔርን እና ኃይማኖትን ከለላ በማድረግ ሁከት እና ብጥብጥ ማስነሳት እንዲሁም በድህነት የምትማቅቅ ሀገርን መፍጠር ነው። እርግጥም እንደ እነርሱ እሮሮ እና እንደ እነርሱ እርግማን ይህቺ ሀገር ድሮ ነበር ያበቃለት ነበር። ግን ወሳኙ ህዝቡ ስለሆነ በወሳኝነት የተፈጠረ ጉልህ ጉዳይ የለም።
ሆኖም ሀገራችን የህዝብን ኑሮ በተጨባጭ በመለወጥ ላይ የሚገኝ መንግስት የታደለች እንዲሁም ተታልሎና በውሸት ተገፋፍቶ ካልሆነ በስተቀር ባህር ማዶ ቁጭ ብሎ ለሚቀነቀን ተራ ወሬ ጆሮውን የሚያውስ ህዝብ የሌለባት በመሆኗ ፍላጎታቸው መክኖ ቀርቷል።
ማንኛውም ሀገራዊ ችግር መፍትሔ የሚያገኘው ሀገሪቱን በመምራት ላይ በሚገኘው መንግስት እንጂ በእነዚህ ፅንፈኛ ሃይሎች አለመሆኑን የሚገነዘበው የሀገራችን ህዝብ፤ የፀረ-ሰላምና የፀረ-ልማት አጀንዳን የሚያራምዱ ፅንፈኞችን አሉባልታ ካለመስማት ባሻገር በመሃሉ የሚገኙ የእነርሱን የዘረኝነት አጀንዳን ለማስፈፀም የሚሹ ወገኖችንም ማንገዋለል ይኖርበታል።
ህዝቡ በተለያዩ ወቅቶች እነዚህ ሃይሎች ሌላው ቢቀር “ኢትዮጵያን አትርዷት” የሚል አጀንዳን ይዘው ሲያወነቅኑ እንደነበር ያውቃቸዋል። ባህር ማዶ የሚገኙና ማንነታቸውን በውል ያልተገነዘቡ ዲያስፖራዎችን የእነርሱ ተከታይ ለማድረግ ብሎም እርጥባን ለመለመን በአምሳያ ሚዲያቸው የማይቀባጥሩት ነገር እንደሌለም ያውቃል።
አዎ! እርግጥም እዛው ባህር ማዶ ተቀምጠው የመንግስትንና የህዝቡን መልካም ስም ለማጉደፍ የማያዥጎደጉዱት የአሉባልታ ጋጋታ የለም። ይህ ብቻ አይደለም። በአሜሪካ ሆሊውድ በተሰኘ የፊልም ኩባንያ ውስጥ የሚፈበረኩ አስፈሪ እና እርስ በርስ የመበላላት ድራማዊ ትዕይንትን ከሚያሳዩ ፊልሞች ጋር በቀጥታ በማዛመድ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ስርዓትም ልክ እንደ ፊልሙ ህዝቡን እርስ በርሱ እንዲበላላ እያደረገ ነው ሲሉ እስከመወትወት ይደርሳሉ።
ከዚህ በተጨማሪም በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ በአንድ ወቅት አንድ የሩቅ ምስራቅ ሀገር ውስጥ የሚገኝ ፖሊስ ያደረገውን ተግባር የኢትዮጵያ ፈፀመው ብለው ይለጥፉታል። ህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ተግባሩን እየከወነ ያለበትን ከተማ የለለ እንቅስቃሴን በፎቶ በማሳየት ‘የእገሌ ከተማ ህዝብ አድማ መታ’ ብለው ያቀርባሉ።
እርግጥም የመወትወታቸው ጉዳይ አስገራሚ እና ሰበካቸውም አስቂኝ ነው። ሆኖም ገና ለገና ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ስለ ሀገሩ በቂ ግንዛቤ የለውም የሚል የእውር ድንብር እሳቤን ይዘው ይቀርባሉ።
ይህን ተግባር የሚፈጽሙት ፅንፈኛና አሸባሪ ፖለቲከኞች ብቻ አይደለም። የግንቦት ሰባት ልሳን እንደሆነው “ኢሳት” እና የአሜሪካ ድምፅ አማርኛው ክፍል ዓይነት በሚዲያ ስም የሚነግዱ የከሰሩ ፖለቲከኞችም “በዲያስፖራ ፋኖነት” የተሰለፉ ናቸው።
እርግጥ እነዚህን “የዲያስፖራ ፋኖዎች” ጋዜጠኞች ናቸው ብሎ ለመጥራት ከሚታወቀው የአሰራር ስርአት እና የስነምግባር ሂደት ውጪ አዲስ የጋዜጠኞች መስክ እና ብያኔ ከሌለ በስተቀር በምን ስም ራሳቸውን ጋዜጠኛ ብለው እንደሾሙ እነሱው ብቻ ናቸው የሚያውቁት።
ህዝቡ ራሱ በትግሉ የፈጠረውን ስርዓት መጠበቅ ያለበት ራሱ ነው። በየማህበራዊ ሚዲያውና በፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች እየተከናወኑ ያሉትን የዘረኝነትና ጥላሸት የሚቀባ አሉባልታዎችን መመከት ይኖርበታል።
እዚህ ሀገር ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ልማታዊ ተግባራት እንዲሁም የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን እየተረጋገጠ የሚገኘውን ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል የሚያውቀው ህዝቡ እንደ መሆኑ መጠን፤ ዘረኝነትንና ከእርሱ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ማናቸውም ጉዳዩች በቂ ምላሽ በመስጠት የውጭና የውስጥ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች የሚያናፍሱትን የአሉባልታ አጀንዳ መዋጋት ይገባል።
አጀንዳቸው እዚህ አገር ውስጥ ያለን እውነታ የማይመለከት በመሆኑ በተጨባጭ ሃቅ ላይ ተመስርቶ ማጋለጥ ያስፈልጋል። እነርሱ የሚፈልጉት ኢትዮጵያ ውስጥ ብጥብጥ ተከስቶ ማየት ስለሆነ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይህን እኩይ ሴራቸውን በማዳፈን የዜግነት ግዴታውን መወጣት አለበት።