Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፌደራላዊ ስርአቱ ትርጉም የተገለጠበት ፕሮጀክት

0 646

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌደራላዊ ስርአቱ ትርጉም የተገለጠበት ፕሮጀክት

 

ስሜነህ

 

ተገንብተው የተጠናቀቁትን ጨምሮ በመገንባት ላይ የሚገኙ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቻችን ለህዳሴ ጉዞአችን ስኬታማነት  ሚናቸው የጎላ መሆኑ ይታወቃል። በተለይ  ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሃገራችንን ከድህነት የሚያወጣ፣ የአፍሪካ ቀንድ አገራትንም የሚጠቅም መሆኑም በብዙ አግባቦች ተረጋግጦ ተመስክሮለታል። የሀገራችን ህብረ-ዜማ፣ የህዳሴያችን ማማ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዛሬም ለሠከንድ ሳይቆም በመፋጠን ላይ ይገኛል። ይህ ፕሮጀክት የኢፌዴሪ መንግሥት የአካባቢው ሃገራት  ህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ያለ ህዝባዊ መንግስት ስለመሆኑም የማረጋገጫ ሰርተፍኬት ነው። ምክንያቱም የህዳሴው ግድብ  የተፋሰሱ አገራት ህዝቦችን የጋራ ተጠቀቃሚነት ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት መሆኑ ስለተረጋገጠ።

 

ምንም እንኳን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ የግብጽ ሚዲያዎች ብዙ እየጮኹ ቢሆንም ፕሮጀክቱ የእነርሱም የሆነና ሊዘምሩለት የሚገባ እንደሆነ የውሃ ሊሂቃኑ እየተናገሩ፤ መላው ኢትዮጵያውያንም ለስኬቱ ከጫፍ ጫፍ ሌት ተቀን እየተጉለት ይገኛሉ። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንደተበሰረ የሃገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ከጫፍ ጫፍ በመነሳት በመላው ሃገሪቱ የድጋፍ ሰልፎችን ማካሄዳቸው ፕሮጀክቱ ከሃይል ማመንጨትም ባሻገር ብሄራዊ ትርጉሞች ስላሉት ነው፡፡ በድጋፍ ሰልፎቹ ላይ ታዲያ የመንግስትም አቋም ብዙ ባልተብራራበት ሁኔታ በውሃ ሀብታችን በፍትሃዊነት መጠቀም መብታችን ነው የሚል መልእክት እንጂ እኛ ከሞትን ሰርዶ አይብቀል የሚሉ መልእክቶችን ህዝቡ አላሰማም። ይህ ባለበት ሁኔታ የግብጾቹ ጩኸት ምክንያታዊነቱ የቱ ጋር እንደሆነ ግራ ገብ ይሆናል። ተወደደም ተጠላ በውሃ ሀብታችን በፍትሃዊነት የመጠቀምን መርህ ያነገበው የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም ልክ እንደትናንቱ ድጋፉን አጋግሎ እንደቀጠለ መሆኑ የፕሮጀክቱ ትርጉም ከሃይልም በላይ ስለሆነ ይልቁንም የቀጠናውን ሃገራት ጨምሮ ለተፋሰስ ሃገራቱ  የተስተካከለ የሃይል ሚዛን ማስጠበቂያ ስለሆነም ጭምር ነው። ድጋፎቹ ደግሞ ሲጀመርም ከነበረው በላይ እየጋሉ መሄዳቸውን ግብጻዊያን ጯሂዎቹ ቢያጤኑ ወደቀናው መንገድ በመጡ በነበር።  

ግና ከጅምሩ ኢትዮጵያውያኑ በየአደረጃጀቱ እና በየመስሪያ ቤቱ በመሰባሰብ ለግድቡ ይህን ያህል እንሰጣለን እያሉ ቃል የገቡ ሲሆን የመንግስት እና የግል ሰራተኛው የወር እና የሁለት ወር ደሞዙን በዓመት ቆርጦ ለመስጠት ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ድጋፉን አሃዱ ሲል ጀምሮ የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ታዲያ ህዝባዊ ውግንናው በሁሉም መልክ እየተገለጸ ባለው የመንግስት ውሳኔ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት የህብረተሰቡ ስጦታ በቦንድ እንዲቀየር እና ቆጥቦ መልሶ ገንዘቡን ከነወለዱ እንዲያገኘው ከማድረግ አልፎም ግድቡን እየገነባ በሌላም በኩል የቁጠባ ባህሉን እንዲያዳብር በማሰብ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ በኢትዮጵያ መንግስት አቅራቢነት  በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል በባለቤትነት ለሽያጭ እንዲቀርብ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በአነስተኛ እና ጥቃቅን የቁጠባ እና ብድር ተቋማት ሽያጩ በውክልና እንዲከናወን ማድረጉም የሚታወስና የነገሩን በጥንቃቄና በጥልቀት የመያዝ ሚስጥርና ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው፡፡

ቦንድ ግዢውና ልገሳ እንዲሆም ሌሎችንም ድጋፎች ጨምሮ ባሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ የተቻለ ሲሆን፤ ቃል ከተገባው 70 በመቶ ያህሉ ገቢ እንደሆነም ከብሄራዊ ምክር ቤቱ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እዚህ ላይ ሰራተኛው ቃል ከገባው ከ90 በመቶ በላይ የተሰበሰበ ሲሆን የፌዴራል ፖሊስ እና ሜቴክ 6 ዙር ቦንድ ግዢ ከገቡ ተቋማት ተጠቃሾች መሆናቸውን ጨምሮም በወረዳ ደረጃም የየም ልዩ ዞን ለ6 ዙር ቦንድ ግዢ ማካሄዱን መረጃው ጨምሮ አመልክቷል፡፡

የዚህ ፕሮጀክት ግዙፍነት የሚለካው በሚያመነጨው የሃይል መጠን ሳይሆን በፈጠረው ብሄራዊ መነቃቃትና መግባባት ነው የሚባለው ያለምክንያት ሳይሆን በህዝቡ የተጠናከረ ተሳትፎ የሚረጋገጡ መነሳሳቶችን መነሻ በማድረግ ነው። ይህ ተረክም ይህንኑ የሚያወሳና ከዚህ መነሳሳት ጀርባ ያለውን ቋጠሮ መፍታት ነው።

ከፍተኛ የቦንድ ግዢ የፈጸሙ ተቋማትን ለማመስገን በ2004 መጨረሻ በተከናወነ ስነስርዓት ላይ  ታላቁ መሪ ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ የሃገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ላደረጉት የላቀ ድጋፍ ያሸናፊነት ምልክት ዋንጫ ሸልመው የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህ ዋንጫ ታዲያ ባሳለፍናቸው 5 አመታት ከገንዘብ ባሻገር የአንድነት ልካችንን እና የብሄራዊ ማንነታችንን በጉልህ ለዓለም ህዝብ በማሳየት ከሃይል ምንጭነት ባሻገር ያለውን የፕሮጀክቱን ሚስጥራት እየገላለጠ ይገኛል።   

ዋንጫው መጀመሪያ ግድቡ በሚገኝበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለ6 ወራት የቆየ ሲሆን በኋላም በዕጣ በተለያዩ አምስት ክልሎች በመዘዋወር ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ እና መነሳሳትን ይልቁንም ብሄራዊ መግባባትን የፈጠረ እና እግረ መንገዱንም የገንዘብ ድጋፍ ለግድቡ ግንባታ ማሰባሰብ አስችሏል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ በአፋር፣ በትግራይ ፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የተዘዋወረው ዋንጫ  በድምሩ ከዞረባቸው 5 ክልሎች ብቻ 1.224 ቢሊዮን ብር በላይ  ለግድቡ ግንባታ  ድጋፍ ማሰባሰብ ከማስቻሉም በላይ ብሄራዊ መግባባትን ፈጥሮ የፌደራላዊ ስርአቱን ፋይዳ በሚገባ አጠይቀል፡፡  እስከ ህዳር 29 /2009 ዓ/ም በኦሮሚያ 607 ሚሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ባሁኑ ወቅት ዋንጫው በደቡብ  ህዝቦች ክልል ታቅዶ ከነበረው ግማሽ ቢሊዮን የማይደርስ የገንዘብ ድጋፍ ከእጥፍ በላይ ማሰባሰብ ያስቻለ የመሆኑ ነገር ሲታሰብ በእርግጥም ታላቁ ፕሮጀክት ከሃይል ምንጭነት የላቀ ትርጉም ያለው እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው። ይኸውም ዋንጫው በተዘዋወረባቸው ክልሎች ሁሉ የተደረገለት ከፍተኛ አቀባበል፤ ይልቁንም ከክልል ክልል እና ከዞን ዞን ዋንጫውን በሚረካካቡበት ጊዜ በህዝቦች መካከል የመተሳሰብ እና የመረዳዳት መንፈስ እያሰረጸ ሸኚው ለቀጣዩ ተረካቢ ዞን እና ወረዳ ዋንጫውን ሲያስረክብ ስጦታዎች (የቁም ከብቶችን) ጨምሮ በመስጠት ብሄራዊ አንድነቱን የበለጠ ሲያጠናክር እና በልዩነቱ ውስጥ ያለውን አንድነት በማጉላት የትምክህት ሃይሎችን ቅስም መስበሩ የመጀመሪያው ነው፡፡

ከህዳሴው ግድብ ዋንጫ በተጨማሪ በሌሎችም የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮጀክቶች ማስተዋል የተቻለው ለግድቡ ሃብት ከማግኘት ባሻገር የጠለቁ እና የፌደራላዊነታችንን ስር መስደድ ያጠየቁ ጉዳዮችን ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሁለት ዙር በተግባር ላይ የዋለው የ8100 A አጭር የሞባይል አጭር መልዕክት ሎተሪ ጨዋታ ታሳቢ የተደረገው ቦንድ መግዛት ለማይችሉ በቀን ስራ እና አነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን በማሰብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በግድቡ ላይ አሻራቸውን እንዲያኖሩ መሆኑ በእርግጥም የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞቹ ገንዘብ ከማሰባሰብም በላይ በታላቁ ፕሮጀክታችን ጥላ ስር ብሄራዊ አንድነታችንን ለማጠየቅ እንደሆነ ለመገመት አይከብድም። በዚህም አብዛኛዎቹ ቦንድ ለመግዛት ያልቻሉ እና ለግድባችን መቼ ነው ድጋፍ የምናደርገው እያሉ ሲያስቡ የነበሩ ሁሉ በሶስት ብር ድጋፍ በማድረግ በታላቁ ፕሮጀክት አሻራቸውን እንዲያኖሩና የህዝባዊው ንቅናቄ እና ተሳትፎው አካል እንዲሆኑ በማስቻል የባለቤትነት ስሜታቸውን ማጎልበት ማስቻሉም ሌላኛው እና ቋጠሮውን የፈታው የፕሮጀክታችን ትሩፋት ነው፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የወረቀት ሎተሪም ባለፈው ዓመት በተግባር ላይ የዋለ ሲሆን  10 ሚሊዮን ብር በማሸለም እና ብዙ ተሸላሚዎችን የያዘ ዕጣ በማካተት በአይነቱ  የመጀመሪያው እና ታሪካዊ  ሎተሪ በመሆን ደማቅ ታሪክ ማስመዝገብ የቻለ፤ የ64.7 ሚሊዮን ብር ሎተሪ በመሸጥ የብሄራዊ መግባባትን እና የፌደራላዊነትን ክብረወሰን የሰበረ ፕሮጀክት በመሆን ከሃይል ምንጭነትም በላይ የሆነውን ትርጉም ለዓለም እየተረከ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ በሌሎች እና ከገንዘብ ባሻገር በሆኑ ፕሮግራሞች ብዙ ቋጠሮዎችንም ለመፍታት ያስቻለ ነው። መላው ኢትዮጵያውያን ይልቁንም በአባይ ተፋሰስ መንደርተኛ የሆኑ ዜጎች ከቦንድ ግዢ በተጨማሪ በአካባቢ ጥበቃ ስራ በተለይም በችግኝ ተከላና አፈር ጥበቃ ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተረባረቡ መሆናቸው አንደኛው መገለጫ እና ከገንዘብ ባሻገር የሚገኘው ማሳያ ነው፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ በሚል እሳቤ በመላው ሃገሪቱ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በእርከን ስራ ላይ ባመት ከ30  የስራ ቀናት በላይ ሰፊ ጉልበት በማፍሰስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ባለፈው ዓመት ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለው ከነዚህ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ መጽደቁን፤ እንዲሁም የሰው ኃይል ጉልበት በገንዘብ ሲሰላ ወደ 47 ቢሊዮን ብር ሊተመን የሚችል ጉልበት በእርከን እና አፈር ጥበቃ ስራ ላይ በማዋል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን የተመለከተው የብሄራዊ ምክር ቤቱ መረጃ የሚያጠይቀው ታላቁ ግድባችን ከሃይል ምንጭነትም የዘለለ የብሄራዊ ኩራታችን እና ተሞክሮ ላልተሳካው የትርምስ አጀንዳ መልስ የሰጠ፤ የፌደራላዊነታችንን ትክክለኛነት እና በማይናወጥ አለት ላይ እየተገነባ የሚገኝ ስርአት መሆኑን ነው፡፡

በሁሉም የአለም ክፍሎች ማለትም በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በኤዥያና ኦሽኒያ እንዲሁም በአውስትራሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዚሁ አገራዊ ፕሮጀክት ላይ የበኩላቸውን አሻራ ለማኖር በየአገሩ ባሉ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም የፋይናንስ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ድጋፍ በማሰባሰብ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ለአገሪቱ ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይህንን በመረዳት በአገራቸው እድገትና ብልጽግና ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዲችሉ እድል በመፍጠር በተለያዩ መስኮች ተሳትፎ እንዲያደርጉ አነሳስቷል፡፡ በግድቡ ግንባታ የዳያስፖራ አባላት የፖለቲካ፣ የብሄርና የሃይማኖት ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በማሰባሰብና በማስተሳሰር የጋራ መግባባት እንዲፈጥሩ ያስቻለ ልዩና ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ እንደተበሰረ የህዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ መነሳሳት ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ሁሉም በአንድነት ለግድቡ ድጋፍ መስጠታቸው ግድቡን ያለምንም ልዩነት የሚገነባ የህዝብ ግድብ አድርጎታል፡፡ በዚህም የተነሳ የግድቡ ባለቤት መላው  የኢትዮጵያ ህዝቦች መሆናቸው በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ አልፎ አልፎ በሚታዩ በጣት የሚቆጠሩና ግንባታውን በማይደግፉ ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር የፌደራላዊ ስርአቱ ባለቤትም ሆነ ጠባቂው መንግስት ሳይሆን ህዝቡ መሆኑንም ያስመሰከረ ታላቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለምንም የውጭ ብድር እና ዕርዳታ በራሱ አቅም ታግሎ የሚሰራው ግድብ በመሆኑ ግድቡን መቃወም  ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መላተም መሆኑን ያስገነዘቡት ከላይ የተመለከቱት የተሳትፎ አይነቶች በእርግጥም ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከሃይል ምንጭነት ባሻገር በርከት ያሉ ፌደራላዊና ዴሞክራሲያዊ ትሩፋቶች ስላሉት ነው።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy