Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዴሞክራሲና ፈጣን ልማት የስርዓቱ እስትንፋሾች ናቸው

0 282

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዴሞክራሲና ፈጣን ልማት የስርዓቱ እስትንፋሾች ናቸው

ወንድይራድ ኃብተየስ

ባለፈው ተሃድሶ ተካሂዶ  በነበረበት ወቅት መረዳት እንደተቻለው ህብረተሰቡ እንዲረጋገጥለት የሚፈልገው “ልማት” ብቻ ሳይሆን “ፈጣን ልማትን” ነው። በቀድሞ ስርዓት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያልነበራቸው አካባቢዎች ዩኒቨርሲቲ፣ የጠጠር መንገድ ያልነበራቸው አካባቢዎች የአስፋልት መንገድ፣ ወዘተ በመጠየቅ  ላይ ናቸው። ይህ የህብረተሰቡ የልማት ጥያቄ ጊዜው የፈጠረው የመለወጥ ፍላጎት ነው። ይህን ለማሳካት መንግስትና ህዝብ እጅግ ተቀራርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል።  አንድ አገር እንደአገር ልትቀጥል የምትችለው የህዝቦቿን ጥያቄዎች መመለስ እንዲሁም ፍላጎታቸውን  ማሳካት ስትችል ብቻ ነው። ይህ ሁኔታ በእኛ አገር ጎልቶ የሚታይ  ነው። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ  ስርዓትን ለማስፈን ለዘመናት መሰዋዕትነት ከፍለዋል። በርካቶች ውድ ህይወታቸውንና አካላቸውን ገብረዋል። የዛሬ 26 ዓመት አምባገነኑ የደርግ መንግስንት በማስወገድ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዕኩልነት የተረጋገጠባት አዲሲቷን ኢትዮጵያ ዕውን አድርገዋል።

የህዝቦች ነጻነትንና ዕኩልነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ ባለፉት 26 ዓመታት  ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ማስመዝገብ ችላለች። በተለይ ባለፉት 14 ዓመታት  ዓለምን ያስደመመ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ በዜጎች ህይወት ተጨባጭ ለውጦች ታይቷል።  የድህነት መጠኑ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከነበረበት ከ44 በመቶ  በግማሽ ዝቅ  ማድረግ ተችሏል። በርካታ ማህበራዊ መገልገያዎች ተገንብተዋል። መንግስት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተመጣኝ  ልማት እንዲኖርና  በህዝቦች መካከል ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲሰፍን  የሚያደርጋቸው ጥረቶች በተጨባጭ ለውጥ አሳይተዋል። አገራችን መሰረታዊ  የመንግስታቱን ዘላቂ ግቦች በተለይ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ  ማሳካት ችላለች።  

ነባራዊውን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ መንግስት የተከተለው ግብርና መር የኢኮኖሚ ቀመር ፈጣን ልማት ከማረጋገጡ ባሻገር በአገራችን ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል  እንዲኖር አግዟል የሚል ዕምነት አለኝ።  ምክንያቱም  የግብርናው ዘርፍ  በአገራችን በርካታውን የሰው ሃይል ያቀፈ  ዘርፍ ነው።  በዚህ ዘርፍ የተመዘገበው  ለውጥ በእያንዳንዱ አርሶና አርብቶ አደር ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ችሏል። የአገራችን ለውጥ በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን   በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታም ጭምር የታየ ነው።

በአንዳንዶች ኢትዮጵያ   በኢኮኖሚው ዘርፍ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ የቻለችውን  ያህል በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ረገድ ዕምርታ አላመጣችም የሚል ክርክር ሲያነሱ ይደመጣሉ። እንደእኔ እንደኔ ግን ለኢትዮጵያ ፈጣን ልማት መመዝገብ ትልቁን ሚና የተጫወተው የዴሞክራሲያዊው ስርዓት መጎለበት መጀመሩ እንደሆነ ይሰማኛል። ኢትዮጵያ ፍጹም አምባገነን ከሆነ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በአንዴ የተሸጋገረች አገር ናት። የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ልምድን የሚጠይቅና በሂደት የሚጎለብት ነው።  

ለቀድሞው የአገራችን  ድህነትና  ኋላቀርነት በምክንያትነት ከሚነጠቀሱ ነገሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚነሳው በአገሪቱ ለረጅም ጊዜ የተካሄደው የዕርስ በርስ ጦርነት ነው። ህዝቦች ዕኩልነትን፣ ነጻነትንና ፍትህን ከተነፈጉ ወደ ግጭት ማምራታቸው የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ ጥሩ ማሳያ አገራችን ነች። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ትግል ሲያደርጉ የነበሩት ዕኩልነትንና ነጻነትን በመሻት ነበር። አገራችን ለረጅም ጊዜ በግጭት ውስጥ መሆኗ በርካታ ነገሮችን አሳጥቷታል።  ግጭት ካለ  ሰላም የደፈርሳል። ሰላም የለም ማለት ሁሉም መልካም ነገሮች ሁሉ የሉም ማለት ነው።

ለአገራችን ሰላም መሰረት የሆነው  ህገመንግስታችን ነው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት እጅግ ዘመናዊና ተራማጅ ከሚባሉ  በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከሚጠቀሱ  ህገመንግስቶች መካከል የሚመደብ ነው። ህገመንግስቱ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መበቶች ማስከበር የሚችሉ አንቀጾችን አካቷል። የህዝቦችን አብሮነትና መተማመን እንዲጎለብት  የሚያስችሉ ሃሳቦችን አካቷል። በመሆኑም  ህገመንግስታችን የአገራችንን አንድነት በጠንካራ አለት ላይ እንዲመሰረት እና ዳግም አምባገነንነት  እንዳያቆጠቁጥ አድርጓል።

የኢፌዴሪ ህገመንግስት ከጸደቀ ባለፉት 22 ዓመታት ህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በተግባር አረጋግጧልል።  አምስት አገራዊ ምርጫዎችን በማካሄድ ይሆኑኛል ይበጁኛል ላላቸው ተወካዮች ድምጹን በነቂስ ወጥቶ በነጻነት ሰጥቷል።  ህዝቦች በተወካያቸው መተዳደር፣  ቋንቋቸውንና ባህላቸውን በነጻነት መጠቀምና ማሳደግ እንዲሁም በአገራዊ ጉዳይ እኩል የመወሰን መብታቸውን አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀድሞ በአገሪቱ ይታይ  የነበረውን የተዛባ ግንኙነት በማረም መተማመንና መከባበር የሚያስችል ስርዓት  በመኖሩ  ዜጎች ወደልማት እንዲሰማሩ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።       

ኢትዮጵያ በርካታ ልዩነቶች የሚንጸባረቁባት አገር ናት። ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚያስችል የፖለቲካ፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስርዓት መከተል ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። አዲሲቷ ኢትዮጵያ  በህዝቦች መካከል የሚስተዋሉ የሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ የፖለቲካ ፍላጎቶች፣ ወዘተ አጣጥማ መጓዝ ካልቻለች መጪውን ነገር መገመት የሚያዳግት አይመስለኝም። አሁን እንደቀድሞው ጊዜ ነገሮች አለባብሶ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ረግጦ በማስፈራራት ወይም በመሸንገል  ማስተዳደር አይቻልም። ጊዜው ተለውጧል። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ልማትና ዴሞክራሲ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። ባለፈው ሁከት መረዳት እንደተቻለው ህብረተሰቡ እየፈለገ ያለው ልማትን ብቻ ሳይሆን ፈጣን ልማትን ነው።

ልማትን ያለ ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ ማሳካት ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን ዘላቂነት ሊኖረው አይችልም። አንዳንዶች ዴሞክራሲንና ልማትን ተነጣጥለው ሊተገበሩ እንደሚችሉ ነገሮች ናቸው በማለት ሲከራከሩ ይታያሉ። እንደምሳሌም የቻይናን ተሞክሮ ያቀርባሉ። በእርግጥ ቻይና    ይህን መንገድ ተከትላ ስኬታማ ሆና ሊሆን ይችላል። ይሁንና የቻይናና የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እጅግ የተለያየ ነው። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ፈጣን ልማት የአገሪቱ ስርዓታ ዋልታና ማገር ናቸው።

በኢትዮጵያ ጭቆና ለዘመናት  የተንሰራፋባት አገር በመሆኗ ህዝቦች በጋራ ሆነው ለመብታቸው ሲታገሉ የቆዩበት ሁኔታ ነበር። አሁን መንግስትን የሚመራው ኢህአዴግ በራሱ ጭቆና የወለደው የትግል ግንባር ነው። ኢህአዴግ ደርግን ለመጣል ከ17 ዓመታት በላይ  እልህ አስጨራሽ የትጥቅ ትግል አካሂዷል። በዚህ የመብት ጥያቄ ትግል በርካቶች የህይወትና የአካዕ መስዋዕትነት ከፍለዋል። እንግዲህ ልማትን ለማፋጠን ተብሎ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማፈን አይቻልም። የኢትዮጵያ እና የቻይና ነባራዊ ሁኔታ እጅግ የተለያየ ነው። የኢፌዴሪ መንግስት የህዝቦችን የመልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ሊመልስ የሚችል ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ  መንግስት  መተግበር ብቸኛው አማራጭ አድርጎ ወስዶታል። በመሆኑም መንግስት እየተከተለው ያለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ አገሪቱን በተጨባጭ የለውጥ ምህዋር ውስጥ እንድትገባ አስችሏታል።

ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ስርዓት ለኢትዮጵያ  ብቸኛ አማራጭ ነው።  በኢትዮጵያ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች   ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት  ግንባታ ህይወታቸውንና አካላቸውን ገብረዋል።  በመሆኑም ለልማት ተብሎ ዴሞክራሲን መጨፍለቅ አይቻልም።  ለዚህም ነው የኢፌዴሪ መንግስት  የዴሞክራሲ ስርዓትና ፈጣን ልማትን ማረጋገጥ   የስርዓቱ እስትንፋሾች  ናቸው  የሚለው።  

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy