Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ድርድሩ የሚያካሄደው ዴሞክራሲን ለማጎልበት ነው!

0 233

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ድርድሩ የሚያካሄደው ዴሞክራሲን ለማጎልበት ነው!

                                                       ደስታ ኃይሉ

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርተዎች ጋር እያካሄደ ያለው ድርድር በሀገራችን ውስጥ እየተከናወነ ያለው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲጎለብት ካለው ፍላጎት የመነጨ ነው። በድርድሩ ላይ የሚነሱት አጀንዳዎች የሰለጠኑ፣ የህገ መንግስቱን የበላይነት የሚያከብሩና ለሀገር ያለቸው ፋይዳ እየታዩ እውን እንዲሆኑ ፓርቲዎቹ መትጋት ያለባቸው ይመስለኛል።

ለዴሞክራሲው መጎልበት ወሳኝ ሚና ያላቸው በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ተመስርተው ህጋዊ በሆነ መንገድ ተግባራቸውን ሲያከናውኑ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። የመደራጀት መብቱን ተከትሎ የየራሳቸው ደጋፊዎች ያሏቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተውና በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የባህር መዝገብ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመስርተው ተግባራቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።

በተለይም የሽግግር መንግስቱን ተከትሎ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ዕውን ከሆነ በኋላ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ እስከተካሄደው ምርጫ 2007 ድረስ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብረው ለአምስት ጊዜያት በተካሄዱት ምርጫዎች ተወዳድረዋል።

ሆኖም የምርጫ ጉዳይ በመራጩ ህዝብ ፍላጎት በሚሰጥ ድምፅ ላይ የተመሰረተ እንጂ፣ በገዥው ፓርቲ አሊያም መንግስት በሚያደርጉት ችሮታ ላይ የሚከናወን ባለመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በአብላጫ ድምፅ ተመራጭ ሊሆኑ አልቻሉም።

በመሆኑም እነዚህ  ሶስት ምክንያቶች ተቃዋሚዎቹ የህዝቡን አብላጫ ድምፅ እንዳያገኙ ምክንያት የሆኑ ይመስለኛል። አንደኛው፤ ተቃዋሚዎቹ በህገ መንግስቱና በህዝባቸው ከመተማመን ይልቅ በውጭ ኃይሎች የሚዘወር ዴሞክራሲን የሚሹ ሆነው መቅረባቸው ነው።  

ሁለተኛው፤ በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሳቢያ በህዝቡ ውስጥ የተፈጠሩ ብሶቶችን ከማራገብና ቅንጭብጫቢ የኒየ-ሊበራሊዝን አስተሳሰብ ከማስተጋባት በስተቀር የህዝብን ቀልብና ልብ ሊገዙ የሚችሉ የነጠሩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ማቅረብ አለመቻላቸው ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ፤ ተቃዋሚዎቹ ራሳቸውን እንደ ፓርቲ ሲመሰርቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን እናጎለብታለን በሚል እሳቤ ይሁን እንጂ፣ ከአወቃቀራቸው ጀምሮ እርስ በርሳቸው የማይተማመኑና በስሜታዊ ቁርኝት የተቧደኑ እንዲሁም በጥቅም ሽኩቻ ሳቢያ በምርጫ ሰሞን በአደባባይ ሲፈረካከሱና እርስ በርሳቸውም ሲወነጃጀሉ በመራጩ ህዝብ ዓይን ትዝብት ላይ ስለወደቁ ነው ብዬ አምናለሁ።

ገዥው ፓርቲ ‘ቁጥሩ ይነስ እንጂ ተቃዋሚዎችን የመረጠ የሀገራችን ህዝብ በመኖሩና የዚህ ህዝብ ድምፅ መሰማት ስላለበትም በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር አካሂዳለሁ’ ብሎ ድርድር እያካሄደ ነው። በዚህም የመደራደር ፍላጎት ካላቸው 16 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተደራደረ ነው።

ለዚህም የምርጫ ህጉን ከማሻሻል ጀምሮ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ህገ መንግስቱን እስከማሻሻል ጭምር ድረስ በመሄድ የተዳቀለ የምርጫ ስርዓትን በመከተል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፅ የሚሰማበትን ሁኔታ በመፍጠር የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ቃል ገብቷል።

እርግጥ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከሚከተል እንዲሁም ዴሞክራሲን እንደ ሞትና ሽረት ጉዳይ አድርጎ ከሚመለከት ፓርቲና መንግስት የሚጠበቅ በመሆኑ የሚያስመሰግን ተግባር ነው።

ገዥው ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸው አበረታች ድርድሮች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ የተያዘው ቁርጠኝነት በሚፈለገው ፍጥነት መጎልበት ያለበት ይመስለኛል። ዴሞክራሲውን ለማስፋት በመንግስት በኩል የተያዘው ቁርጠኝነት ተጨባጭ መገለጫዎች ሊኖሩት ይገባል። ተቃዋሚዎችም ይህን ተስፋ በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ወዳልተፈለገ እሰጥ አገባ ውስጥ እንዳይከታቸው ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ይመስለኛል።

እናም ከተቃዋሚዎቹ ጋር የሚካሄዱ ውይይቶችና ድርድሮች መነሻቸውና መድረሻቸው በግልፅ ተለይተው ሊገለፁና የጋራ ድምዳሜ ሊያዝባቸው ይገባል። ይህ ሲሆንም መንግስትና ገዥው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጎልበት ያላቸውን ቁርጠኝነት ይበልጥ በመግለፅ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ የሚችሉ ይመስለኛል።

በእኔ እምነት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ውይይትና ድርድር፤ ፓርቲዎቹ ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታው ጋር ተያይዞ መንግስት ያለበትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ህፀፆቹን በግልፅ እንዲያይ ያደርጉታል። መንግስትም አግባብና ትክክለኛነት ያላቸውን አስተያየቶች በመቀበል ለስራው እንደ አንድ ድጋፍ እንዲጠቀምባቸው የመነሻ ሃሳቦች ሊሆኑት ይችላሉ።

ይህ ሁኔታም በአንድ በኩል ዴሞክራሲውን ለማስፋትና የህዝቦችን ተደማጭነት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሰሚነት ድምፅ እንዲጨምር ዕድል ይሰጣል። በፓርላማ ደረጃ የሚኖረው የአሳታፊነት ዴሞክራሲም ይጎለብታል።

ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ ውይይት ከላይ እንደጠቀስኩት ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ እንጂ፣ ስልጣንን ከመጋራት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። ሊኖረውም አይገባም እላለሁ።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ልክ እንዳለፉት ጊዜያት መንግስታዊ ስልጣንን ህገ መንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ በውጭ ኃይሎች ግፊት ለመያዝ ከመሻት ከመነጨ በሚመስል ሁኔታ፣ ዛሬም መንግስት ‘ዴሞክራሲውን ለማስፋት ቆርጨ ተነስቻለሁ’ ሲል ጉዳዩን የመድብለ ፓርቲውን ስርዓት ከማጎልበት አኳያ ከማየት ይልቅ፣ ከስልጣን መጋራት ጋር ሊያያይዙት ይሞክራሉ።  

እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ አስተሳሰባቸው የተሳሳተ ብቻ አይደለም—ህገ መንግስቱን ካለመገንዘብ ጭምር የመጣ እንጂ። የኢፌዴሪ ህገ መንግስቱ አንቀፅ 8፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸውንና ሉዓላዊነታቸው የሚገለፀውም በህገ-መንግስቱ መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካኝነት እንደሚሆን ደንግጓል።

ይህ ድንጋጌ በግልፅ እንደሚያሳየው ማንኛውም የፖለቲካ ስልጣን የሚያዘው የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት በሆነው ህዝብ ይሁንታ ብቻ መሆኑን ነው። ህዝቡ ሲፈልግ ይሾማል፤ ሳይፈልግ ደግሞ ይሽራል። ይህ በየትኛውም ሀገር የሚሰራበት ነው። በመሆኑም ይህን የዴሞክራሲ እሴት ማጉላት ያስፈልጋል። በየድርድሮቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዴሞክራሲን በማጎልበት ረገድ ጉልህ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy