Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግለሰብን ከባለሃብትነት ወደ ተመፅዋችነት የቀየረው አሳዛኙ የአራጣ ብድር በአዲስ አበባ

0 835

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሚጓጉለት ስራ እንዳይስተጓጎል በማለት የሚወሰድ የአራጣ ብድር የበርካቶችን ህይዎት እያመሰቃቀለ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና እድሜያቸው በ40ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙት አቶ ዳዊት ከበደ ከዓመታት በፊት ከ1 ሺህ 500 በላይ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ፋብሪካና በስማቸው ሶስት ተሽከርካሪዎች እንደነበሯቸው ይናገራሉ።

ከአመታት በፊት አልዳ ፒ ኤል ሲ የተሰኘ የሚስማር ፋብሪካን በስራቸው ያስተዳድሩ ነበር፤ በስራ አጋጣሚ ገንዘብ ይቸግራቸውና በርቀት የሚያውቁት ሰው ገንዘብ ከሚያበድራቸው ሰው ጋር ሊያገናኛቸው ወደዛው ያቀናሉ።

ግለሰቡም የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት ከሆኑት አቶ አብይ አበራ ከተባሉ ገንዘብ አበዳሪ ጋር ያገናኟቸውና በየወሩ 8 በመቶ ወለድ የሚታሰብበት 800 ሺህ ብር ይበደራሉ፤ ለተበደሩት ገንዘብም ያሏቸውን ሶስት ተሽከርካሪዎችና የ180 ሺህ ዶላር የሚስማር ማምረቻ ማሽን በዋስትና ማስያዛቸውንም ተናግረዋል።

ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላም ጅቡቲ ላይ የተቀመጠውን 150 ቶን የሚስማር ሽቦ ለማስገባት በንብ ባንክ በኩል አስፈላጊውን ሰነድ አዘጋጅተው ዕቃውን ለማምጣት ይሞክራሉ፤ ይሁን እንጂ ብረቱ ጅቡቲ ላይ ከመቆየቱ የተነሳ ተበላሽቶ ከአገልግሎት ውጭ ሆኗል፤ አቶ ዳዊትም ለኪሳራ ይዳረጋሉ።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነውም ከአቶ አብይ ለተበደሩት ገንዘብ ወለድ፥ 64 ሺህ ብር ለተከታታይ ስድስት ወራት መክፈላቸውንም ነው የተናገሩት።

አራጣ አበድረዋል የተባሉት አቶ አብይ አበራ በበኩላቸው፥ በጉዳዩ ላይ በስልክ በሰጡን ምላሽ አራጣ እንዳላበደሩና ከአቶ ዳዊት ከበደ ጋር የነበራቸው ግንኙነት የፋብሪካ ሽያጭ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ዳዊት ግን አልዳ ፒ ኤል ሲ በሚል የሚታወቀውን የሚስማር ፋብሪካቸውን አቶ አብይ መጥተው ካዩት በኋላ፥ ፋብሪካውን ለመንጠቅ ጥረት ማድረግ እንደጀመሩና ሼሩን እንዲሸጡላቸው መጠየቃቸውንም ያነሳሉ።

በወቅቱ አቶ አብይ ፋብሪካው ስራ ጀምሮ ከባንክ ብድር እንዲያገኝ በማድረግ አቶ ዳዊት ቀድሞ የተበደሩትን 800 ሺህ ብርና የሁለት ወር ወለዱን ጨምረው መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

አቶ ዳዊትም ፋብሪካውንና የቀረውን ገንዘብ ለመመለስ ተስማምተው የፋብሪካውን ውል በአቶ አብይ ስም አዙረዋል።

የፋብሪካውን ስም ያዞሩት ግን ቅድሚያ በዋስትና ባስያዙት የ800 ሺህ ብር ቼክ ላይ ስለተመታባቸውና አበዳሪው በእርሱ እንደሚከሷቸው ማስፈራሪያ ስላደረሱባቸው መሆኑንም ነው የገለጹት።

አቶ አብይ ደግሞ ፋብሪካውን ከአቶ ዳዊት ላይ በህጋዊ መንገድ ነው የገዛሁት በሚል ሁለቱም የተፈራረሙበትን የሰነድ ማስረጃ አሳይተዋል፤ በውሉ ላይ ከአቶ አብይ ጋር በመሆን አቶ ዮሃንስ ኃይለየሱስ የተባሉ ግለሰብ ግማሹን አክሲዮን በስማቸው መግዛታቸው ተመልክቷል።

እርሳቸው ግን ከፋብሪካው ግዢ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸውና አቶ አብይ ፈርምልኝ ስላላቸው ብቻ መፈረማቸውን በመጥቀስ፥ ለሽያጩ የከፈሉት ምንም አይነት እንደሌለ ተናግረዋል፤ አበዳሪው ግን ለፋብሪካው መግዣ 700 ሺህ ብር ከአቶ ዮሃንስ ተቀብያለሁ ባይ ናቸው።

ከዚያም አቶ አብይ ፋብሪካውን አሜሪካ ሃገር ለሚገኝ ሶስተኛ ሰው ሸጠውታል፥ ለሽያጩም ከገዥው 380 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በአቶ አብይ ስም ወደ ጀርመን ሃገር ገንዘብ ተልኳል፤ ምንም እንኳን አቶ አብይ ገንዘቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የተከፈለኝ ቢሉም።

በዚህ መሃል አቶ ዳዊት ፋብሪካቸውን ያጣሉ፤ የአክሲዮን ባለድርሻ ሆነው ወደፈረሙት አቶ ዮሃንስ በመሄድም ፋብሪካውን በምን መልኩ ለአቶ አብይ አሳልፈው እንደሰጡ አስረድተው እንዲሸመግሏቸው ጥያቄ ማንሳታቸውን አስታውሰዋል።

ጉዳዩን ለማሸማገል የተሰበሰቡ ሰዎችም አቶ አብይ ለአቶ ዳዊት 230 ሺህ ብር እንዲከፍሉና በይደር ሌሎች ክፍያዎች እንዲፈጸሙ ተስማምተው ክፍያውም ተፈጽሟል፤ ምንም እንኳን አቶ አብይ ምንም ክፍያ እንዳልፈጸሙ ቢጠቅሱም።

ከፋብሪካው ባለፈ አቶ አብይ በዋስትና የያዙትንና ንብረትነታቸው የአቶ ዳዊት የሆኑ ተሽከርካሪዎችንም ወስደዋል፤ እርሳቸው የወሰድኩት መኪና የለም ቢሉም ተሽከርካሪዎቹን ለአቶ ዳዊት ያስመጡላቸው አቶ ጀማል ሃሰን የተባሉ ግለሰብ ተሽከርካሪዎቹ የአቶ ዳዊት መሆናቸውን አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ቁጥጥርና ፍቃድ ባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተሽከርካሪዎቹ የተዘዋወሩበት ሰነድ ላይ የአቶ ዳዊት ከበደ ስም ግልጽ ባልሆነ መልኩ እንዲወጣ ተደርጓል፤ አቶ ዳዊት ለአቶ አብይ ሶስቱን ተሽከርካሪዎች በውክልና መስጠታቸውን የሚያሳይ ሰነድ ግን ከውልና ማስረጃ ተገኝቷል።

በዚህ መልኩ በአራጣ ብድር የተነሳ ንብረታቸውን ያጡት አቶ ዳዊት ባለቤታቸው ለህመም በመዳረጋቸው አበዳሪያቸው ባለቤታቸውን የሚያሳክሙበት ገንዘብ እንዲሰጧቸው ጠይቀው መከልከላቸውን ገልጸውልናል።

ማሳከሚያ ገንዘብ ያጡት አቶ ዳዊት በመጨረሻም የሁለት ልጆቻቸውን እናት በሞት ተነጥቀዋል፤ አሁን ላይም እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ከአዲስ አበባ 60 ኪሎ ሜትር ርቀው ሁለት ልጆቻቸውን በችግር እያሳደጉ መሆኑን ይገልጻሉ።

ከአቶ ዳዊት ባለፈ ወደ ጣቢያችን ከአቶ አብይ በአራጣ ተበድሬ ስራየና ኑሮዬ እየተመሰቃቀለ ነው የሚል ቅሬታ ከኢ ኤል ጀኔራል ቢዝነስ ባለቤት ከሆኑት አቶ ዳንኤል ወንደሰን ቀርቧል።

አቶ ዳንኤልም ቢ አይ ካ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር በጋራ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ለማውጣት ላሸነፉት ጨረታ ስራ ቅድመ ክፍያ ሳይከፍሉ ወደ ስራ ለመግባት፥ ከአቶ አብይ አበራ ጋር ከዚህ ቀደም ተበድሮ የመመለስ ግንኙነት ስለነበራቸው በአራጣ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ተበድሬያለሁ ብለዋል።

ከዚያ በኋላም ስራውን ሰርተው ሲጨርሱ በአራት ወር ውስጥ ወለዱን ጨምሮ 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በአቶ አብይ አበራ ስም በተጻፈ ቼክ መክፈላቸውን አቶ ዳንኤል ይገልጻሉ፤ የቼኮቹን ኮፒም አሳይተውናል።

ያበደሩት ገንዘብ የተመለሰላቸው አቶ አብይ ግን የወለዱን መጠን ጨምሩልኝ በሚል ከፍተኛ ግፊት እያደረጉብኝ ነው ብለዋል አቶ ዳንኤል።

በአቶ አብይ አበራ ላይ ከአራጣ ጋር ተያይዞ የተነሳውን ጉዳይ ፖሊስ ያውቅ እንደሆነም ጠይቀናል።

በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፋይናንስ ወንጀል ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር ኃይለሚካኤል ገብረማርያም እንዳሉት፥ ጥቆማው ለፖሊስ ደርሶ አስፈላጊውን ማስረጃ አሰባስበውና አጣርተው ጉዳዩን ወደ ሚመለከተው የፍትህ አካል ለመላክ ዝግጅት ተጠናቋል።

ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy