ህዝባዊና ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት
ዳዊት ምትኩ
የኢትዮጵያ መንግስት ተግባራቶቹ ሁሉ በህዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ይህ በህዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ፍላጎቱ ከሚመራበት ህዝባዊነት መንፈሰ የመነጨ ነው። ሃላፊነትም የሚሰማው ነው። ይህ ማንነቱ ገና ከመነሻው ጀምሮ በህዝብ የሚመራና ለህዝብ የታገለ ስለሆነ ነው። በመሆኑም መንግስት በየትኛውም ቦታና ጊዜ ህዝብን ያማከለ ተግባራት እየፈፀመ ላለፉት 26 ዓመታት ተጉዞ ዛሬ ላይ ደርሷል። በአገሩ ጉዳይና በህዝብ ፍላጎቶቹ ላይ ተደራድሮ አያውቅም።
መንግስት በተለያዩ ወቅቶች ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ የህዝቡን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከመጠበቅ ባሻገር፤ ባለፉት ጊዜያት ባህር ማዶ ተሻግሮም ባለማወቅ በህገ ወጥ ደላላዎች ተታልለው ለስደት የተዳረጉ ወገኖቻችን ለመርዳት ብዙ ርቀት በመጓዝ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፤ እየተወጣም ይገኛል።
በተለይም የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በህገ ወጥ መንገድ ተጉዘው የሀገሪቱ መንግስት የውጭ ዜጎች እንዲወጡ ያስቀመጠውን የጊዜ ገደብ ያልተቀበሉ ዜጎች ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ያደረገው ጥረት ተጠቃሽ ነው።
በወቅቱ የኢፌዴሪ መንግስት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ የገቡትን ዜጎች ከዚያች ሀገር ለማስወጣት ብርቱ ጥረት አድርጓል። በዚህም በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የገቡ ዜጎችን ለመመለስ በርካታ ገንዘብ መድቦ ዜጎቹን በማጓጓዝ ከጀመረ መንግስታዊ ሃላፊነቱን መወጣን እስታውሳለሁ። ዋነኛ ትኩረቱን በዚህ ጉዳይ ላይ በማድረግና ያለ አንዳች ዕረፍት በመስራቱም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቹን ለሀገራቸው አብቅቷል።
ጥረቱ በዚህ ብቻ ሳይገደብም፤ እነዚህ ወገኖች የሚያገግሙበትን ሁኔታ አመቻችቶ በተዘጋጀላቸው ስፍራም እንዲያርፉ ብሎም ዘላቂ ህይወታቸው የተመቻቸ እንዲሆን የሚያደርጉ አቅጣጫዎችን በመቅረፅ የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥሯል። ይህም ከስደት ተመላሾቹ በሀገር ቤት ሰርተው መለወጥና ማደግ እንዲችሉ ያስቻለ ተግባር ነበር። መንግስትም ምን ያህል ለህዝቡ ተቆርቋሪና አሳቢ መሆኑን ያንፀባረቀ ተግባር እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።
ከሶስት ዓመት በኋላም ዛሬ ላይ ተመሳሳይ ችግር ተፈጥሯል። ይኸውም የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ሀገሩ ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ የገቡ የውጭ ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የምህረት አዋጅ ማውጣቱ ነው። አሁንም ቢሆን ሳዑዲ ውስጥ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ይታወቃል።
ይህን ጉዳይ በሚገባ የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት ካለው ህዝባዊ ወገንተኝነት በመነሳት ዜጎቹ በተሰጠው ምህረት ተጠቅመው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ሰፊ ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም ከሳዑዲ መንግስት ጋር ፊት ለፊት በመነጋገር ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። ዜጎቻችን በሳዑዲ ውስጥ በሚገኙባቸው የተለያዩ ከተማዎች በመገኘት የጉዞ ሰነድ እንዲወስዱ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመክፈት ከምህረቱ ቀነ ገደብ በፊት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ጥረት አድርጓል። እያደረገም ነው።
በሳዑዲ መንግስት በህገ ወጥነት የተፈረጁት ስደተኞች በዚያች ሀገር ቆይታቸው ያፈሩትን ንብረት ይዘው በህጋዊ መንገድ እንዲገቡ እንዲሁም አሻራ መስጠት ሳያስፈልጋቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ጥረት ተጠናክሯል። ስደተኞቹ ወደ አገራቸው ሲገቡም የተለያዩ የመገልገያ ዕቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ፈቅዷል።
ሆኖም መንግስት ዜጎች ሰነዶቻቸውን እንዲያገኙ በሳዑዲ የተለያዩ ጽህፈት ቤቶችን ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ እስካሁን በቂ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች የምህረት አዋጁን እየተጠቀሙበት አለመሆኑ ይታወቃል።
የዚህ ችግር ምክንያቱ ህገ ወጥ ደላላዎች ‘የሳዑዲ መንግስት እንዲህ አያደርግም’ በማለት በሚነዙት አሉባልታ ንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ይመስለኛል። ምክንያቱም ስደተኞቹ ወትሮም ከሀገር የወጡት በህገ ወጥ መንገድ በእነዚሁ ህገ ወጥ ደላላዎችም አማካኝነት የሚካሄድ በመሆኑ ከህግ ያፈነገጠው ስራቸው እንደሚበላሽባቸው በሚገባ ስለሚያውቁ ነው።
እርግጥ የሳዑዲ መንግስት በአዋጁ ላይ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አማካኝነት እንደገለፁት ስደተኞቹ በሌላ ጊዜ በህጋዊ መንገድ እንደሚመለሱ እነዚህ ደላላዎች ስለሚያውቁ በህገ ወጥ ስራቸው ላይ የሚያመጣባቸውን ውድቀት በመገንዘብ አስቀድመው በመላ ምቶች የታገዙ አሉባልታዎችን ማስወራታቸው የሚገርም አይደለም። ምክንያቱም የሳዑዲ መንግስት ፍላጎት የየትኛውም ሀገር ዜጋ በህጋዊ መንገድ በሀገሩ ውስጥ እንዲኖር እንደሚፈልግና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወሰ ውጭ ሀገር እንዲሄዱ የማድረግ ስራ በቅርቡ ይጀመራል ማለታቸው የህገ ወጥነት መንገድ እንደሚገባ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው።
ዳሩ ግን የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ በህገ ወጥ መንገድ በሳዑዲ ይኖሩ በነበሩ ዜጎች ላይ የደረሰው ሞት፣ እንግልትና በባዶ እጅ መመለስ የሚያሳየው ነገር ቢኖር፤ ዛሬም በምህረት አዋጁ ያልተጠቀሙ ስደተኞች የዚያን ጊዜው አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደማይችል ምንም ዓይነት ዋስትና የለም።
እናም ስደተኞቹ ይህንን የለየት የህገ ወጥ ደላላዎችን ቅጥፈት ባለመስማት አንድም የሳዑዲ መንግስት ያስቀመጠውን የጊዜ ገደብ መጠቀም፣ ሁለትም የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት አስቀድሞ ለመጠበቅ ከወዲሁ የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ ይኖርባቸዋል።
በመሆኑም ስደተኞቹ የተሰጣቸውን ዕድል በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል። በመሆኑም ስደተኞቹ ዕውነታውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተገንዝበው ለራሳቸው ዘላቂ ህይወትም ይሁን ለመንግስት ህዝባዊ ወገንተኝነት ጥረት ዋጋ መስጠት ይኖርባቸዋል እላለሁ።
የኢፌዴሪ መንግስት ህዝባዊ በመሆኑ ከሁሉም በላይ ለዜጎቹ ችግር ፈጥኖ ደራሽ መሆኑ ሊታወቅ የሚገባ ይመስለኛል። ይህ ሁኔታም በዜጎች ላይ ችግር በተፈጠረ ቁጥር በሀገር ውሰጥም ይሁን በባህር ማዶ እየተገኘ ፈጣን ምላሽ በመስጠትና ተገቢውን ርምጃ መውሰዱ ለህዝቡ የሚሰጠው ከፍተኛ ክብር ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል።
መንግስት ሁሌም እንዲህ ዓይነቱን ተግባር የሚያከናውነው መነሻውም ይሁን መድረሻው ከሚከተለው ህዝባዊ ወገንተኝነት የመነጨ ነው። ዜጎቹ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በህገ ወጥነት በመገኘታቸው ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ስር ሳይወድቁ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት የዚሁ ለህዝብ የወገነ መርሁ ነፀብራቅ ነው።
መንግስት ለህዝብ የወገነና ኃላፊነት የሚሰማው በመሆኑ በሳዑዲ መንግስት በህገ ወጥነት የተፈረጁ ወገኖችን ለመርዳት አንድ ወር አስጨምሯል። ይህም ወር ቢሆን እያለቀ ነው። ዜጎች የመንግስትን ጥረት በመደገፍ ቀናቶቹን በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል። ከእንግዲህ የሚደርሰው ነገር ከባድ ላለመሆኑ ማንም እርግጠኛ ሊሆን አይችልም። እናም ዜጎቻችን ወደ ሀገራቸው በመመለስ የመንግስትን ጥረት ማገዝ ይኖርባቸዋል።