Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህዝብን ከህዝብ ጋር የማስተሳሰር ጥረት

0 947

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህዝብን ከህዝብ ጋር የማስተሳሰር ጥረት

                                                        ታዬ ከበደ

የኢፌዴሪ ህዝብና መንግስት ስደተኞችን በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እያስተናገዱ ነው። መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ስደተኞችን እንደሚቀበልና በዚህም በተለይ የኤርትራ ስደተኞች እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ እንዲማሩ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህም ህዝብን ከህዝብ ጋር የማስተሳሰር ጥረት አካል ነው። በዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና እና ምስጋና ተችሮታል።

እንደሚታወቀው የምስራቅ አፍሪካ አገራት በእርስ በርስ ጦርነት ችግር አለባቸው። እንደ ኤርትራ ያሉ ህዝቦች ደግሞ በውስጣቸው ካለው የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ እጦት ሳቢያ አገራቸውን በመተው በየብስና በባህር ይነጉዳሉ።

ይሁንና የቀጣናው አገራት ህዝቦች ዛሬ ላይ ሩቅ ከማለም ይልቅ አስተማማኝ ሰላም ያላትን አገር እየመረጡ ነው። መንግስት ይህን ሁኔታ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እየተጠቀመበት ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተላቸው ማናቸውም ፖሊሲዎች ህዝብን መሰረት ያደረጉ ናቸው። ቅድሚያም ለህዝብ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት የሚሰጡና የሚጨነቁ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት በህዝብ ውስጥ አድጎ በህዝብ የሰላ ትችት እየተመራና ራሱን በራሱ እያረመ ዛሬ ላይ የደረሰ በመሆኑ ህዝባዊ ወገንተኛ ነው።

ይህ ህዝባዊ ባህሪውም የየትኛውንም ሀገር ህዝብ እንደ ህዝብ የሚያከብርና በእኩል ዓይን የሚመለከት ነው። በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ የአብዛኛዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች እንደ ሁለተኛ ሀገር የምትቆጠር ሆናለች። የህዝቦችን ችግር የሚገነዘብ መንግስትና እንግዳ ተቀባይና አክባሪ ህዝብ ያለባት ሀገር በመሆኗ የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች መጠለያ ሆናለች።

ህዝባዊ ባህሪን የተላበሰ ማንኛውም መንግስት ከህዝብ ሰላምና ደህንነት ውጭ የሚያስበው ነገር የለውም። ይህ በመሆኑም የሌሎች ሀገራትን ህዝቦች የራሱ ህዝቦች የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅሞች ሳይቀር እንዲያገኙ እያደረገ ነው።

የኤርትራ ስደተኞችን በምሳሌነት ማንሳት እውነታውን የሚያጎላው ይሆናል። የኤርትራ ህዝብ አምባገነኑ የኤርትራ መንግስት በሚያደርስበት ከፍተኛ ጫና እንዲሁም በገዛ ሀገሩ ውስጥ የመኖር ዋስትና በማጣቱ በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ ይጎርፋል። ከእነዚህ ውስጥ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች፣ አሮጊቶች፣ ህፃናትና ወታደሮች ተጠቃሽ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ እነዚህን ህዝቦች እየተቀበሉ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ እያስተማሩ ነው።

ምዕራባውያን የሌሎች አገራት ዜጎች ወደ አገራችን እንዳይገቡ በማለት በሚከለክሉበት ወቅት፤ ኢትዮጵያዊያን ምንም እንኳን እጅግ የዳበረ ኢኮኖሚ ባይኖራቸውም ባላቸው አቅም የህዝቦችን ችግር እየተጋሩ መሆኑ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካላት አድናቆት ቢቸራቸው የሚገርም አይደለም።

ህዝብና መንግስት ‘ስደተኞቹ ባይቸገሩ አገራቸውን ጥለው አይመጡም’ በሚል ሚዛናዊና ህዝብን ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ያለውን ከማካፈል ባሻገር፤ ስደተኞቹ በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች እንዲሳተፉ እያደረጉ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ህዝባዊነት ከውስጣዊ ባህሪ የሚመነጭ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝቦች ለስደተኞች እያደረጉ ያሉት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ከመደነቅ ባሻገር፣ ተገቢው ትብብርም ሊደረግላቸው የሚገባ ይመስለኛል።

ያም ሆኖ እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የጎረቤት ሀገራት ህዝቦችን ችግር የሚካፈሉት ድጋፍ እንዲደረግላቸው አይደለም—ለህዝቦች ካላቸው ፅኑ ፍቅርና የአገራቱ ዜጎች በየአገራቸው የተፈጠረው ችግር እስኪረጋጋ ድረስ ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ሀገራቸው በመቁጠር ቢኖሩ ቀጣናውን የማረጋጋት አካል ሊሆን ይችላል ብለው ስለሚያስቡ እንጂ። በመሆኑም ሀገራችን ለውስጧ ችግሮች ቅድሚያ በመስጠት የቀጣናውን ሀገራት ህዝቦች የሰላም እጦትን ለማገዝ የምታደርገው ጥረት ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ በቀጣናው ሀገራት መካከል ሰላም ሰፍኖ ልማታዊ ትስስር እንዲጎለብት ፈርጀ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ውጤትም እያገኘበት ነው። ህዝብ ለህዝብ ከተሳሰረ ደግሞ የበለጠ ውጤት ይመጣል ብሎ ያምናል።

መንግስት ሀገራዊ ህልውናን የማስጠበቁ ጉዳይ ሊሳካ የሚችለው ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች ላይ መሰረት በማድረግ ብቻ እንደሆነ በማመን ለተግባራዊነቱ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወቃል።  

በከፍተኛ ኋላ ቀርነትና የድህነት አዘቅት ተዘፍቃ ለቆየችው ሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ግንባታና ሰላምን የማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ወደ ተግባር ተሸጋግሮ ላለፉት 26 ዓመታት ተጉዟል።

በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም የማስገን፣ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን እውን የማድረግ እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ስር እንዲሰድ ምቹ ምህዳርን የመፍጠር ተግባሮችን ከውኗል።

አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው የኢፌዴሪ መንግስት ለአገራችን ሰላምና ልማት እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ፅኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ነው ብሎ ያምናል። ምክንያቱ ደግሞ የአገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ስለሚገነዘብ ነው።

በተለይም ህዝብን ከህዝብ ጋር በማስተሳሰር የሚገኘው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ያውቃል። አንድ ህዝብ ሌላኛውን እንደ አገሩ በመቁጠር በስደት የሚገኝበትን አገር ማመን ከቻለ ለህዝቦች የጋራ እሴት መጎልበት ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።

ታዲያ ይህን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለበጎ ነገር መጠቀም ይቻላል። ስደተኞች በተጠለሉበት አገር ውስጥ ችግራቸው እስከሚቀረፍ ድረስ በመልካም ህዝባዊ መንፈስ ከተያዙ ወደፊት በሰላምና መረጋጋት ጊዜ ለሚኖራቸው ግንኙነት ወሳኝ ነው። ስደተኞችን አቅፎና ደግፎ መያዝ የሁለትዮሽ ህዝባዊ ግንኙነትን በማስፋት ባህላዊ እሴት ከፍ እንዲል ያደርጋል።

በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ የምትከተለው የስደተኞች ፖሊሲ ዓለም አቀፍ መርህን የተከተለና ህዝቦችን በመደገፍ ላይ የተመሰረተ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ምንም እንኳን ያላቸው አቅም ውሱን ቢሆንም፤ ለህዝቦች ካላቸው ፍቅር በመነጨ ስደተኞችን በተገቢው መንገድ እየተንከባከቡ ነው።

ይህ መልካም ተግባራቸው ስማቸው በዓለም ዙሪያ እንዲሰማ ያደረገ ነው። በእርስ በርስ ጦርነትም ይሁን በአምባገነናዊ አገዛዞች ግፍ ሳቢያ የሚሰደዱ ከ850 ሺህ ስደተኞችን በመያዛቸው ዓለም አቀፍ አድናቆትን አትርፈዋል። ይህ ተግባራቸው መንግስት ከሚከተለው ህዝብን የሚደግፍ የስደተኞች ፖሊሲ ህዝቡም ካለው እንግዳ ተቀባይነት የመነጨ በመሆኑ ወደፊትም ይህ ተግባራቸው ተጠናክሮ መቀጠሉ አይቀርም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy