Artcles

ህገ መንግስቱ የድንበር ውዝግብ መፍቻ ነው!

By Admin

July 20, 2017

ህገ መንግስቱ የድንበር ውዝግብ መፍቻ ነው!

                                                    ደስታ ኃይሉ

በአገራችን ውስጥ በተፈጥሮ ሃብት እጥረት ሳቢያ የሚከሰቱ ውዝግቦች በህገ መንግስቱ መሰረት እልባት እየተሰጣቸው ነው፡፡ በአገራችን የድንበር ውዝግቦች መነሻቸው ምንም ይሁን ምን ከህገ መንግስቱ የአሰራር ማዕቀፍ ውጪ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ማናቸውም ተግዳቶች በህገ መንግስቱ መሰረት ምላሽ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡

ዛሬ በህገ መንግስቱ ዜጎች ለአዲስ ህይወት ማበብ ተስፋ ሰንቀው፣ በፀና ህብረት ላይ ቆመው፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው ኑሮን ማጣጣም ይዘዋል፡፡ ንፁህ አየር መማግ፣ በሰላም ገብቶ መውጣት፣ በነፃነት መንቀሳቀስን ችለውበታል፡፡ ለዚህ መብቃት የተቻለው ደግሞ ሺህዎች በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ነው፡፡ በውጤቱም በመላ አገሪቱ ሰላም ተገኝቷል፤ የልማት መስመር ተይዟል፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በፅኑ መሠረት ላይ እየቆመ ነው፡፡

ላለፉት 26 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ጥቅሞቻቸውን በማጎልበት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአንድነት ተነሳስተዋል፡፡ በብዝኃነት ላይ መሠረቱን የጣለው አንድነት ለህዳሴውም ስኬት መገለጫ ነውና የዜጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ህገ መንግሥት ጠብቆ ለማቆየት ሁሉም በፅናት ቆሟል፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩበት፤ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት መሠረት የተጣለበት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት፤ ውበትና ህብረት የታየበት ብሎም የሥልጣን ባለቤት የተረጋገጠበት፤ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ የተጀመረበት መሠረቱ ይኸው ህገ መንግሥት ነው፡፡

የህገ መንግሥቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ሆነው እንዲቀጥሉ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መርጠው በላኳቸው ወኪሎቻቸው አማካኝነት ህገ መንግሥቱ ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለ ሁለት አሥርት ዓመታትን ተሻግሯል፡፡

በእነዚህ ጊዜያት የክልሎችን እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል በተለይም በልማትና ዕድገት አፈጻፀም ረገድ በጎ እርምጃዎች ተወስደው መልካም ውጤቶች ታይተዋል፡፡ በህገ መንግሥት በተደነገገው እኩል የመልማት መብት በመጠቀም በሁሉም ክልሎች በተነፃፃሪ ፈጣን የሚባል ልማትና ዕድገት ተመዝግቧል፡፡

ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ከአገሪቱ ተጨባጭ ታሪካዊ ሁኔታ በመነሳት በህገ መንግሥቱ ተደንግጎ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ሕብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ያለፉት አፋኝ መንግሥታት የቀበሩትን የማንነትና የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት ጥያቄን በአስተማማኝ ደረጃ መመለስ ችሏል፡፡

በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

በዚህም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ተሳትፏቸውና በየደረጃው ተጠቃሚነታቸው ጎልብቷል፡፡ አካባቢያቸውንም በማልማት ለአገር ብልፅግናና እድገት ከፍተኛ ደርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አኳያ ደግሞ የልማትና ዕድገት አፈጻፀም በክልሎች እኩል ተጠቃሚነት እየተፈፀመ መሆኑን የሚያረጋግጥ እውነታ ነው፡፡

የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ልማታዊው መንግሥት ግልፅ የሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ ህጎችን፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በየአካባቢው ተጨባጭ እቅድ እየተመነዘሩ የሚፈፀሙበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በአፈጻፀም ሂደት የተገኙ በጎ ልምዶችም እየተቀመሩ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎችና ለምልዓተ ሕዝቡ የሚደርስበት ስልቶች ተቀይሰዋል፡፡

የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች የሚለዩበትን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ካለፉት ልምዶች በመነሳት እንዲፈተሹና እንዲስተካከሉ በማድረግ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ይገኛል፡፡

የጋራ የተፈጥሮ ሃብት እየተመናመነባት በመጣው ዓለማችን ውስጥ እዚህም ይሀን እዚያ ግጭት መኖሩ ነባሪያዊ ነው። ዋናው ጉዳይ ግጨቱን ለመፍታት ስርዓቶቹ የሚወስዱት ህገ መንግስታዊ ማስተካከያ ይመስለኛል። ከዚህ አኳያ የሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት በታሪክ አጋጣሚም ይሁን በተፈጥሮ ሃብቶች እጥረት ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮችን የሚፈታበት የራሱ መንገዶች አሉት።

ከህግ አኳያ ያለው የግጭት አፈታት መንገድ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአጎራባች ክሎች መካከል ለሚፈጠሩ ግጭቶች ፌዴራላዊ ስርዓቱ ህዝቡ ውስጥ ያሉትን ማህበራዊ መዋቅሮችን ይጠቀማል። አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ተሰሚነት ያለቸው ግለሰቦች የችግሩን መንስኤዎች በማጥናትና ሁኔታው ዳግም እንዳይከሰት የበኩላቸውን ዕገዛ እንዲያደርጉ ሊጠየቁ ይችላሉ።

ይህ ማህበረሰብ አቀፍ የሆነ የግጭት አፈታት መንገድ ችግሩን ከስር መሰረቱ ለማወቅና በማያዳግም ሁኔታ ለመቅረፍ ያስችላል። ምክንያቱም በተጋጩት ሁለት ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ተሰሚነት ያላቸው ወገኖች የችግሩን ስረ መሰረት ለመረዳትና ተጨባጭ መፍትሔም ለመስጠት ከእነርሱ በላይ ለጉዳዩ የሚቀርብ ባለመኖሩ ነው።

የክልሎች ነፃነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በሁለት ክልሎች ህዝቦች መካከል ግጭት ሲፈጠር የፌዴራል መንግሰቱ ጣልቃ የሚገባበት አካሄድም ተደንግጓል። ይህን አሰራር ለመተግበርም የፌዴራል መንግስቱ ሁለቱን የሚጋጩ ወገኖች በመፍትሔነት ሊጠቀም ይችላል። ይህም ተጋጭዎቹ ችግሮቻቸውን በራሳቸው መንገድ እንዲፈቱና ዘላቂ አለመግባባት እንዳይኖር ያደርጋል። ይህ ሁኔታም ዘላቂና አሰተማማኝ ሰለምን ለመስፈንና የተጋጩት ወገኖችን ከንትርክና ከአተካራ ወጥተው በሀገራቸው ልማት ላይ የበኩላቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ ዕድል ይሰጣል።

ይህ ሲሆንም በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠው የዜጎች የመልማት መብት ዕውን ይሆናል። እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ልማት የመብት ጉዳይ መሆኑን ይገልጻል። የልማት እንቅስቃሴ ዋና ዓላማም የዜጐችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል መሆኑ ተደንግጓል። እንደሚታወቀው የልማት አጀንዳ ለአገራችን እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

ህገ መንግስቱ የህዝቦችን ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ብሰቶች እንዲራገቡና የህዘቡ የልማት ተጠቃሚነት በአላስፈላጊ እንካ ሰላንቲያዎች እንዲደናቅፉ በር አይከፍትም። እንዲያውም ይህን መሰሉ የህዝቦችን መብቶች የሚደፈጥጡ አካሄዶች ሀገራችን ውስጥ እንዳይፈጠሩ አስቀድሞ መከላከል ስራ ያከናውናል። ይህም በክለሎች ውስጥ በሚገኙት መንግስታዊ መዋቅሮች አሊያም በማህበረሰብ አቀፍ የማስተማሪያ መድረኮች ተፈፃሚ እንዲሆን ያደርጋል። በጥቅሉ በድንበር ሳቢያ የሚፈጠሩ ውዝግቦችንም ይሁን መሰል ችግሮችን በህገ መንግስቱ አግባብ መሰረት መፍታት እንደሚቻል ግንዛቤ መያዝ ይገባል።