ህገ ወጥ ስደት ባርነት ነው!
ቶሎሳ ኡርጌሳ
የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በሀገሩ የሚኖሩ የመኖሪያና የስራ ፈቃድ የሌላቸውን ስደተኞች ከሀገሪቱ እንዲወጡ አሳስቧል። ይህን በተመለከተም የሀገሪቱ የተለያዩ ባለስልጣናት የምህረት አዋጁ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ሌሎች ሰነድ አልባ ዜጎች በሪያድ ከሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ተነጋግረዋል። በዚህም ሁሉም የመኖሪያና የስራ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች ሳዑዲን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ከመሰንበቻው መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያልወጡ ዜጎች በምህረት አዋጁ ላይ በሰፈረው ድንጋጌ መሰረት ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ገልፀዋል—የሪያድ ባለስልጣናት።
በአሁኑ ወቅት የምህረት አዋጁ ተጨማሪ ጊዜ ተጠናቅቋል። የሳዑዲ መንግስት ምን እንደሚያደርግ እየተጠበቀ ነው። ምናልባትም ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት የሀገሪቱ ባለስልጣናት ከሀገሪቱ እንዲወጡ ማሳሰቢያ የተሰጣቸው የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ባለመውጣታቸው ሞት፣ እንግልትና ስቃይ እንዲቀበሉ እንዳደረጉት ሊያደርጉ አለመቻላቸው የሚታወቅ ነገር የለም።
ይህም ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በዚያች ሀገር የሚኖሩ ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸው ሳይጠበቅላቸውና ክብራቸው ተገፍፎ በአደጋ ውስጥ ሊገኙ እንደሚችሉ የሚያመላክት ይመስለኛል። እናም ምንም እንኳን የዜጎች በፈለጉት ቦታ ተንቀሳቅሰው የመስራትና ንብረት የማፈራት ህገ መንግስታዊ መብት ቢኖራቸውም፤ ይህን መብታቸውን ህጋዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ያለባቸው ይመስለኛል።
ኢትዮያዊ ዜጋ ከሀገር ወጥቶ ለመስራት እስከፈለገ ድረስ ህጋዊ ሆኖ በመንግስት ዕውቅና መብቱና ክብሩ ተጠብቆለት የሚሰራበት ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል። እዚህ ሀገር በመከናወን ላይ ካለው ተምሳሌታዊ ልማታዊ ተግባር ባሻገር፤ ዜጎች ወደ ውጭ ሄደው እንዲሰሩ በመንግስት የወጣው የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ይህን ህጋዊነት እያረጋገጠ ነው።
እንደሚታወቀው ህገ ወጥ ስደት የሀገርንና የወገንን ክብር የሚነካ ባርነት ነው። እናም ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸውና ክብራቸው ሳይነካ መንገስት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ መጠቀም ይኖርባቸዋል።
ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ለመስራት ካልፈለገና ‘በውጭ ሀገር ሰርቼ ሃብት አፈራለሁ’ ብሎ ካሰበ የሚከለክለው አካል አይኖርም። ምክንያቱም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ህገ መንግስታዊ እውቅና እና ጥበቃ ያለው ነው። ማንኛውም ዜጋ በፈለገው ጊዜና ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሃብት የማፍራት የማይገሰስ ህገ መንግስታዊ መብት አለው። ይህን ማንም ሊቀለብሰው አይችልም። ይህን መብት መቃወም ህገ መንግስቱን መፃረር ነው።
ታዲያ ይህን ህገ መንግስታዊ መብት በአግባቡና ህጋዊ በሆነ ሁኔታ መጠቀም ይገባል። አንድ ዜጋ ባሻው ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ስላለው ብቻ ራሱን ለአደጋ ቤተሰቡን ደግሞ ለችግርና ለስጋት አጋልጦ ህገ ወጥ መንገድን መጠቀም ያለበት አይመስለኝም።
የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የዜጎችን እንግልትና ችግር በመመልከት ዜጎች ለስራ ወደ ውጭ ሲጓዙ ከሞት፣ ከእንግልትና ከስቃይ ይላቀቁ ዘንድ ህጋዊ የአሰራር ማዕቀፍን አበጅቷል። በተለይም ከላይ የጠቀስኩት አዋጅ ቁጥር 923/2008 የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን ህገዊ በሆነ መንገድ ለመፈፀም የተዘጋጀ ነው።
በዚህ አዋጅ ተመርቶ በህዊ መንገድ ወደ ውጭ የስራ ስምሪት ማድረግ ራስን ከአደጋ ቤተሰብን ደግሞ ከሃሳብና ከሰቀቀን የሚታደግ ይሆናል። ይህን አዋጅ ተጠቅሞ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ መጓዝ የህገ ወጥ ደላላዎችን መንገድ ይዘጋል። በጥቅሉ ህጋዊነትን ተቀብሎ በህግ አግባብ ማንኛውንም ነገር ማከናወን ራስን ከአደጋና ከውርደት በመጠበቅ የሀገርን ክብርም ማስጠበቅ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ የሚገባ ይመስለኛል።
ከአዋጁ ጎን ለጎንም በክልሎች ውስጥ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ብርቱ ጥረት መደረግ ያለበት ይመስለኛል። እርግጥ ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መፍትሔው በመንገስት አዋጅ ላይ ብቻ የተጣለ አይደለም። የህገ ወጥ ዝውውሩ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ህገ ወጥ ደላሎችን ህዝቡ በሚገባ ያውቃቸዋል። ማን፣ የትና ምን እንደሚሰራ ከህዝብ ዓይን የተሰወረ አይደለም።
ህዝቡ በየቀየው የህገ ወጥ ዝውውሩ አቀናባሪና ስደተኞችን ወደ ሞት የሚገፉ እነማን እንደሆኑ ያውቃል። እናም ህዝባዊው ጥረት ከመንግስት ህጋዊ አሰራር ጋር እንዲቆራኝ ማድረግ ከተቻለ፤ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ እንኳን ባይሆን ከግማሽ በላይ ሄዶ መቅረፍ የሚቻል ይመስለኛል።
በተለይም በየክልሉ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ በሚፈለገው መጠን ከተሰራ የችግሩን መንስኤ ነቅሶ በማውጣት ተገቢውን ማስተካከያ ማድረግ ይቻላል። በየጊዜው ‘ኢትዮጵያውያን በኮንቴይነር ሲጓዙ እገሌ በሚባል ሀገር ውስጥ ተያዙ’ የሚል ዜናን ላንሰማ የምንችልበት ጊዜ ሩቅ የሚሆን አይመስለኝም።
ታዲያ እዚህ ላይ ሰሞኑን በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተከናወነውን እውነታ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። ከመሰንበቻው መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት፤ በደቡብ ክልል የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የዕድር ዳኞችንና የማህበረሰቡን ተወካዮች በማስተባበር ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው።
ይህ ጥረትም ህዝቡን በማስተማር ላይ የተመሰረተ ቅስቀሳ መሰረት አድርጓል። እርግጥም እንዲህ ዓይነቱ ስለ ህገ ወጥ ስደት የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ውጤቱም ጥሩ ሊሆን እንደሚችል አያጠያይቅም።
በተለይም ታዋቂ የሆኑትንና ተሰሚነት ያላቸውን የተለያዩ የማህበረሰቡን አካላት ወደ ህዝቡ ውስጥ በማሰማራት ስለ ጉዳዩ እንዲያስረዱና እንዲያሳውቁ መደረጉ፤ እነዚህ አካላት በማህበረሰቡ ውስጥ ባላቸው እውቅና ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ። ታዲያ ይህን መሰሉ ጥረት በአንድ መንገድ ብቻ መከናወን የለበትም። ባርነት የሆነው ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እውነታ ዋነኛ ተጠቂ የሆኑትና በህገ ወጥ ደላላዎች ሊታለሉ የሚችሉት ወጣቶች ዘንድም በተጠናከረ ሁኔታ መድረስ ይኖርበታል።
ለዚህም አሁንም በደቡብ ክልል በየትምህርት ቤቶች የፀረ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ክበባትን በማቋቋም ይህ ህጋዊ ባርነት በወጣቶች ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት እንዲሁም ወጣቶች ችግሩን ለመቋቋም ማከናወን ስላለባቸው እንቅስቃሴዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑ “ይበል” የሚያሰኝ ነው።
ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ የክልሉ ነዋሪዎች ፓስፖርት ለማውጣት ወደ ክልሉ የኢሚግሬሽን ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ሲሄዱ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ስለሚያስከትለው አደጋ፣ በሀገር ላይ ስለሚኖረው የገፅታ ግንባታ ችግርና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዩች ትምህርት እየተሰጠ መሆኑ እንዲሁም በህጋዊ መንገድ መስራት የሚያስችል አሰራርን ማስተዋወቅ መቻሉ ተገቢነቱ አጠያያቂ አይሆንም።
ያም ሆኖ በክልሉ እየተተገበረ ያለው ይህን መሰሉ አበረታች ጥረት የአንድ ወቅት ተግባር እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባል። ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቱ በየዘርፉ ሊቋረጥ አይገባም። የክልሉ ተሞክሮም ወደ ሌሎቹ የሀገራችን ክልሎች መስፋፋት ይኖርበታል።
ህገ ወጥ ስደት ህጋዊ ባርነት መሆኑንና መንግስት በአዋጅ ያፀደቀው ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አዋጅ መኖሩን ማስገንዘብ ይገባል። በህገ ወጥ መንገድ መጓዝ ተጠቃሚ ህገ ወጥ ደላላው እንጂ ተጓዡ ህይወቱን እስከማጣት የሚያደርስ እንደሆነ ማስረዳት የግድ ይላል።
እናም ይህን ህጋዊ ባርነት ለመከላከል እንደ ሀገር በሁሉም አካባቢዎች አስፈላጊው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች (በተለይም ዋነኛ ተጠቂ ሊሆኑ የሚችሉትን ወጣቶች ማዕከል በማድረግ) መስጠት ይገባል። በሁሉም ክልሎች ውስጥ ስለ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ችግር ግንዛቤ ተይዞ ተከታታይ በሆነ መንገድ መስራት ከተቻለ፤ ሁሉም ዜጋ እንደ አንድ ሰው፣ አንድ ዜጋ እንደ ሁሉም ሰው ሊሰራና የችግሩን ችግርነት በከፍተኛ ሁኔታ መቅረፍ እንደሚቻል እምነት መያዝ ያስፈልጋል።