ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል…
ዳዊት ምትኩ
የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ችግርን ለመከላከል በአገራችን ውስጥ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ችግሩን ለመቅረፍ በርካታ ተግባሮች እየተከናወኑ ነው። ተመክሮዎቹ በአብዛኛው ተጠቂዎችን በማስገንዘብ ላይ የተመሰረተ ነው። ታዲያ እነዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጥረቶች በሁሉም አካባቢዎች መስፋፋት ይኖርባቸዋል። በተለይም ለችግሩ መንስኤ የሆኑትን ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን በመታገል ረገድ ህዝቡ ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ በዚህ ረገድ እየተከናወኑ ያሉት ተግባሮች ከፍተኛ ናቸው። ያም ሆኖ ግን እነዚህ ተግባሮች በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባሮቹ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያመላክቱ መሆን አለባቸው። ባለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር፡፡
በዚህም በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊ ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸውን አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት እንዲሁም ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው።
እነዚህ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ እንደሚገኙ እማኝ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይመስለኝም። በዚህ የኢኮኖሚ ስራ ውስጥ ገብቶ እንደሌሎቹ ወገኖች ራስን መቀየር እየታቻለ ስደትን እንደ አማራጭ መውሰድ ተገቢ አይደለም። በተለይም በጉዳዩ ላይ ተሳታፈ የሆኑት ወጣቶች ስለ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። የግንዛቤ ማስጨበጫዎቹም በእነርሱ ላይ ማተኮር አለበት።
እንደሚታወቀው ሁሉ ህገ ወጥ ደላሎች ግንኙነት እንደ ሰንሰለት በተያያዘ ሰንሰለት የተቆራኘ ነው። ይሁንና በዚህ አነስተኛ ፅሑፍ ላይ ከህገ ወጥ ደላሎቹ ማንነት፣ አሰራራቸውና በዝውውሩ ሂደት ከሚኖራቸው ሚና አኳያ አዘዋዋሪዎቹን የአካባቢ፣ ድንበር አሻጋሪ፣ ጉዞ አቀላጣፊ፣ ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በመዳረሻ ሀገራት የሚገኙ ደላሎች በማለት ልንከፍላቸው እንችላለን።
የአካባቢ ደላሎች በሚገኙባቸው ቦታዎች የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና በሌሎች ዘዴዎች ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እንዲሁም ተጋላጭ ግለሰቦችን የመለየት ስራን ከሌሎች ጋር በመሆን ያከናውናሉ።
ድንበር አሻጋሪዎቹም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን የሚያዘዋውሩ በኮንትሮባንድ ነጋዴነት የሚፈረጁ ናቸው። እነዚህኛዎቹ አዘዋዋሪዎች ሰዎችን በቡድን ከአካባቢ ደላሎች ተቀብለው ለሌሎች ተመሳሳይ አዘዋዋሪዎች የማስተላለፍ ስራዎችን ይተገብራሉ።
ጉዞ አቀላጣፊዎቹም ቢሆኑ መቀመጫቸውን ትላልቅ ከተማዎች ላይ በማድረግ ወደ መዳረሻ ቦታዎቹ የሚደረገውን ጉዞና የቅጥር ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ ሲሆን፣ ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው ደግሞ ዘመድና ጎረቤቶች እናግዛለን በማለት እነርሱ ወደ ነበሩበት ሀገር ሄደው እንዲቀጠሩ በግለሰብ ደረጃ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በመደበኛነት የሚንቀሳቀሱ ናቸው።
የእነዚህ ከስደት ተመላሽ ዜጎች እንቅስቃሴ በቤተሰባቸውም ይደገፋል። ቤተሰቦቻቸው ልጆቻቸው ውጪ ሀገር ሄደው የሚያመጡት ገንዘብ በምን ሁኔታ የተገኘ መሆኑን ስለማይገነዘቡ ከስደት የተመለሱት ልጆቻቸው ያስገኙላቸውን ጠቀሜታዎች በመዘርዘር የህገ ወጥ ስደቱ ሂደት ተካፋይ ይሆናሉ። ይህን የህገ ወጥ ስደቱ ተጠቂዎች መገንዘብ አለባቸው።
እርግጥ የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኘና በተግባር እየተከናወነ ያለ ጉዳይ ነው። እናም እዚህ ላይ ዜጎች ለምን ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል። ይሁንና ሰዎች በሀገር ውስጥ ወይም ወደ ውጭ ሀገር ከቦታ ወደ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወይም ስደት የተሻለ ስራ ፍለጋና ህይወት ወይም ልክ ወንድም እንደሆነው የኤርትራ ህዝብ ከጭቆና ለመሸሽ አሊያም የመኖሪያ ቦታን ለመቀየር ሊሆን ይችላል።
ዛሬ ላይ በመላ ሀገሪቱ በተዋረድ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል፡፡ በዚህም ህበረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሔው አካል እንዲሆን በየክልሉ በርካታ ተግባራት ዕውን ሆነዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀው ግብረ ሃይልም በሀገራቸውም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር በህጋዊ ተንቀሳቅሰው መስራት የሚፈልጉ ዜጎችን በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በማስገባት በተለያዩ የስራ መስኮች የአጭር ጊዜ ስልጠና መስጠት እንዲሁም ከሥልጠናው በኋላ በሰለጠኑበት ሙያ በሀገር ውስጥ በመደራጀት ወደ ሥራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ከስራ ጋር ለማስተሳሰር ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት ለሚፈልጉ ዜጎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ፣ ለስልጠና እና መሰል ስራዎች ድጋፍ የሚውል ሐብት ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ማዘጋጀትና ሃብት የማፈላለግ ተግባራት ገቢራዊ ሆነዋል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተከናወኑትን ተግባራት እንደ ምሳሌ ብንወስድ እንኳን፣ ከአረብ አገር ተመላሾችን በጊዜያዊነት በመንከባከብ እንዲረጋጉ ከማድረግም አልፎ በርካታ ከስደት ተመላሾች የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ማድረግ መቻሉን መረጃዎች ያስረዳሉ።
ከዚህ ጎን ለጎንም በዚህ ትውልድን ለአደጋ በሚዳርግ ተግባር የተሰማሩ ደላሎች ላይ የህግ ማስከበር ስራዎችም ተከናውነዋል። በዚህም የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ቦታዎችን መለየት ችግራቸውን መሰረት አድርጎ በተመረጡ እንዲሁም ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች የመቆጣጠር ስራ ገቢራዊ ሆኗል።
በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ሀገር የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግም ህግን መሰረት አድርጎ ነው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ተችሏል። የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎችን የሚመለምሉና የሚያዘዋውሩ ደላላዎችን፣ ተባባሪና ቤት አከራዮችን እንዲሁም አጓጓዦችን መረጃ ማሰባሰብና በመለየት በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር የመፍጠር እርምጃዎች ሲወሰድ ቆይቷል። እነዚህ ጥረቶች ህገ ወጥ ዝውውርንና አዘዋዋሪዎችን ለመከላከል የተደረጉ ናቸው። በህጋዊ መንገድ አዋጅ ወጥቶም ዜጎች በውጭ አገር እንዲሰሩ ተደርጓል። ችግሩን ለመከላከል የሚደረገው የግንዛቤ ማስጨበጫ ጥረት እነዚህን ጉዳዩች ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል።