Artcles

ለሴቶች የተሰራ ለሕዝብ እንደተሰራ ነው!

By Admin

July 13, 2017

ለሴቶች የተሰራ ለሕዝብ እንደተሰራ ነው!

ውብሸት ሰንደቁ

በሶማሌ ማኅበረሰብ ውስጥ ሴት ልጅ የበለጠ ክብር አላት። በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልም ሴትነት ከምንም በላይ ይከበራል፡፡ ሴትን ሲደበድብ ወይም ሲበድል የተገኘ ሰው ፖሊስ አሊያም ሌላ ሕግ አስከባሪ እስኪመጣ ወይም ፍርድ ቤት እስኪቀርብ፤… ወዘተ. ተብሎ ጊዜ አይሰጠውም። በአካባቢው ያለ ማንኛውም ሰው/አካል እርምጃ ይወስድበታል እንጅ፤ ይህም ብቻ አይደለም።  በአከባቢው ያለና ድርጊቱ ሲፈፀም አይቶ እንዳላየ ያለፈ እንኳን ከድርጊቱ ፈፃሚ ባልተናነሰ መልኩ በጎሳ መሪዎች ወይም በሀገር ሽማግሌዎች ይቀጣል፡፡ ይህ እንግዲህ ሥልጣን ያለው መንግስታዊ ተቋም ቢኖርም ባይኖርም በማኅበረሰቡ አባላት የሚፈጸም የሥነ ሥርዐት እርምጃ ነው። በዚህ ክልል አብዛኞቹ ጎሳዎች ውስጥ ሴቶችንና ግመሎችን ያለአግባብ ማየት እንኳን የሚያስቀጣ እሰኪመስል ድረስ ክብራቸው የተጠበቀ ነው፡፡

በብዙዎቻችን ዘንድ የፆታ እኩልነት ሲባል በመንግስት ወይም መንግስት ውስጥ ባሉት የዴሞክራሲ ተቋማት ተሸምነውና አልቆላቸው ለህብረተሰብ እንደሚቀርቡ ምርቶች አድርገን የምናስበው ሃሳብ ውስጥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሲንፀባረቅ ይታያል። እርግጥ ይህን ለመደምደም ጥናት ማካሄድ ያስፈልግ ይሆናል። ይሁን እንጂ፤ በእለት ተለት ግንኙነታችን ውስጥ የሚስተዋል በመሆኑ ሀሰት ነው ወይም ጭርሱኑ የለም ሊባል ግን አይችልም። ያም ሆኖ ግን፤ በዘመናችን የዴሞክራሲ ጥያቄና ሥርዓት ስያሜውን እና አደረጃጀቱን ሳይንሳዊ አድርጎ፤ ከግዴታም ጋር አጣምሮ አምጥቶታል። በዚህ ክልል ግን የእንስትነት ክብር ከመንግስት በአዋጅ የተነገረ አሊያም በመደበኛ ሥልጠና የተገኘ ሳይሆን ሆኖ ከማኅበረሰቡ ጋር የህይወት መርህ ሆኖ የኖረ፤ ያለና የሚዘልቅ ባህል ነው፡፡

እንግዲህ እኔ ይህን የምላችሁን ጉዳይ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በሶማሌ ክልል ተገኝቼ ያየሁትን እና የታዘብኩትን፤ እናም በቃል ደረጃ ሊተነተን የሚችለውን ለእናንተም ለማካፈል ያህል ነው፡፡  

ይህች የኢትዮጵያ ምሥራቋና ደቡብ ምስራቋ ምድር የሴቶችን መብት የማክበርም ሆነ የማስከበር ነገር ከሌሎች ጉዳዮች እኩል ብዙም አስጨንቋት አያውቅም፡፡ ለምን ቢሉ፤ ህብረተሰቡ ሴትን ማክበር ባህሉም ኑሮውም ነውና! ታዲያ ይህን ያህል ስለሴት ልጅ ክብር የሚወሳላት ክልል በሀገር ደረጃ መጥፎነቱ ታምኖበት ዘመቻ የተከፈተበት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እዚያም አንዳንዴ የእምነት ኮፍያውን አጥልቆ ሌላ ጊዜ ምድራዊ ምክንያቶችን ደርድሮ መልኩን እየቀያየረ በዘመቻው አልሸነፍ እያለ ተግዳሮት ሆኖባታል እንጅ፡፡

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ውስጥ ይዘወተራሉ ከተባሉ 141 ዓይነት አካባቢ ከሚሆኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በክልሉ ትኩረት ተሰጥቶባቸው እና በሴቶችና ህጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተሉ መሆኑ ታምኖባቸው ዘመቻው ተጠናክሮ የቀጠለባቸው 5 ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተለይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ የመጀመሪያው የሴት ልጅ ግርዛት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በእጅጉ የተስፋፋና ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ከመሆኑም በላይ በአፈጻጸሙ አደገኛነት የተነሳ በማህበረሰብ በተለይም በህጻናት ሴቶች ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለ ድርጊት ነው፡፡

ይህን የመሰለው በእምነትና በአስተሳሰብ ተደግፎ ለዘመናት የጸና፤ በተለይ መብታቸውና ደህንነታቸው ቅድሚያ ሊሰጠው በሚገባቸው ሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸም ጎጅ ድርጊት በመሆኑ ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡ ይህም ገና ወደ ስነልቦናዊና አካላዊ ጉዳቱ ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ የሚደርስባቸውን አካላዊ ጉዳት ብቻ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ በህክምና/ጤና ሳይንስ የተዘረዘሩት የሴት ልጅ ግርዛት የሚያስከትላቸውን አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳቶች በጥልቀት ስንመለከት ደግሞ ጥፋቱ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። አዎን! በእነዚህ ዜጎች ላይ  በተዘዋዋሪም ይሁን በቀጥታ ለሚደርሰው የሥነልቦና ጉዳትና በማህበረሰቡ የመገለል ችግር መንስኤ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡

ሁለተኛውና ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ ለማስወገድ እየሰራ ያለው ጉዳይ ያለድሜ ጋብቻ ሲሆን፤ ይህም ልማዳዊ ድርጊት ሴቶች እድሜ ሳይደርሱ፤ በአካልም ሆነ በሥነልቦና ሳይጠኑ እኩዮቻቸው ላልሆኑ ወንዶች ተገድደው የሚዳሩበት በመሆኑ በለጋ ሴቶች ላይ የሚያደርሰው አካላዊና ሥነልቦናዊ ጉዳት ከፍተኛ ነበር።

በተጨማሪም፤ እንጥል መቁረጥ እና ግግ መፈልፈልም ሌሎች በስፋት የሚታዩና በሴቶችና ህፃናት ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት አንፃር ታይተው ቅድሚያና ትኩረት ተሰጥቷቸው አየተሰራባቸው ያሉ የቀድሞ ችግሮች ናቸው፡፡

በዚህች ማህበረሰቡ ሴትን በማክበር ተምሳሌትነት በሚጠቀስባት ክልል፤ ምክትል ፕሬዝደንቷ እንስት ናቸው። በፌደራል ደረጃ ካለው የፓርላማ ጥመርታም በበለጠ የሴት  የፓርላማ አባላት ድርሻ ሀምሳ በመቶ ደርሷል። በክልል ቢሮዎች ደረጃም የግብርና ቢሮ፣ የእንስሳት ሃብት ልማት ቢሮ፣ የውኃና ፍሳሽ ቢሮ ኃላፊዎች ሴቶች ናቸው። እንግዲህ፤ ሴቶችን እንዲህ በውሳኔ ሰጭነትና በአመራር ደረጃ ማስቀመጥ የቻለ ክልል ከቶ እንደምን ማህበረሰቡ በሴቶች ላይ የሚደረግን ጎጂ ለማዳዊ ድርጊት አሜን ብሎ መቀበልና መሸከም ይችላል?

ኢትዮጵያ በ2025 ግርዛትንና ያለእድሜ ጋብቻን የመሳሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለማጥፋት ከፈረሙ ሀገራት አንዷ ናት። ይህንንም እውን ለማድረግ ጠንክራ እየሰራች ትገኛለች። እንግዲህ ክልሎች በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው ካልሰሩ ልፋቱ ፍሬ አልባ ይሆናል፡፡ የማህበረሰብ ችግር ማህበረሰቡን ራሱን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ሲተገበር ችግሩ በዘላቂነት ይፈታል። ማህበረሰቡም መፍትሄዎቹ በጊዜ ሂደት እንዳይዛቡና እንዳይበረዙ ዘብ ይቆማል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለይም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ በሚገኙ ከተሞች አካባቢ አነኝህ ከላይ የጠቃቀስኳቸው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በእጅጉ እየቀነሱ መምጣታቸው ይነገራል፡፡ የችግሩ አፈታት አስተማሪ በመሆኑም ለሌሎች በተሞክሮነት ያገለግላልና  እንዴት፣ ምን፣ ከማን ጋር በመሆን ተሰራ በማለት ላነሳኋቸው ጥያቄዎች የክልሉ የሴቶችና ህፃናት ቢሮ ኃላፊ የሚከተለውን ሀሳብ ሰጥተውኛል።

በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የሴቶችና ህፃናት ቢሮ የሴቶችን አቅም ማጎልበት የስራ ሂደት ኃላፊ ዘኃራ አብዲም እንደገለጹልኝ፤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመቅረፍ በዋናነት የሚሰሩት ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባር ነው። ይህንንም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከሌሎች ተመሳሳይና ተቀራራቢ ዓላማ ካላቸው ተቋሞች ጋር በቅንጅት ይሰራሉ፡፡ በተለይም፤ ከወጣት አደረጃጀቶች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከጎሳ መሪዎች፣ ከሴቶች ጋር (ቀደም ሲል ከተገረዙና ካልተገረዙ ሴቶች ጋር)፣ ከልዩ ልዩ ማህበራት እና ከመሳሰሉት ጋር በመስራታቸውም ድርጊቱ ከከተሞች ውስጥ ተወግዷል በሚባልበት ደረጃ እንደደረሰ ኃላፊዋ ይናገራሉ፡፡ በዚህም፤ የሴት ልጅ ግርዛት ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ ህብረተሰቡ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመረዳት እንዲችል ኦዳን ከመሳሰሉ በክልሉ ለተመሳሳይ ዓላማ ከሚሰሩ የተለያዩ ድርጅቶች፤ እንዲሁም ከጤና ተቋማት ጋር በመሆን በርካታ ስራዎችን መስራታቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሰረት፤ የሴቶችና ህፃናት ቢሮና አጋር አካላት ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ ባደረጉት ርብርብ በክልሉ በሚገኙ ከተሞች የሚፈፀሙ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች፤ በተለይ የሴቶች ግርዛት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ የለም ከሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል። በገጠሩ ክፍልም ተስፋ ሰጪ ለውጥ እንዳለ ከኃላፊዋ ማብራሪያ መረዳት ይቻላል።  

እንግዲህ ሴቶች በአጉልና ጎጂ ልማዶች የደረሰባቸውን በደል ያህል መካስ ባንችልም፤ ስለማይችሉ ሳይሆን ቀንበሩን ጥለንባቸው ስለቆየን ልንክሳቸው ይገባልና አስፈላጊውን ድጋፍ እናድርግላቸው፡፡ በእኔ እምነት የወንዶችን ያህል ነፃነት ከቀድሞ ጀምሮ ሴቶች ቢጎናፀፉ አሁን ለመገመት ከምንችለው በላይ አለማችን ውብና ለመኖር ምቹ ትሆን ነበር፡፡ ሶማሌ በተረቱ እንዲህ ይላል “Sir naageed lagamasal gaadwo” በአማርኛ የሴትን ጥበብ ማንም አይደርስበትም እንደማለት ነው፡፡ ሁሌም መታሰብ ያለበት ስለእንስት ሲሰራ ሰዋዊነት እየተሰራ እንደሆነ ነው፡፡