Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለበለጠ የጸረ ድህነት ዘመቻ የሚያነሳሳ እርምጃ ያስፈልጋል

0 485

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለበለጠ የጸረ ድህነት ዘመቻ የሚያነሳሳ

እርምጃ ያስፈልጋል

 

ዮናስ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የዛሬ አመት ግድም ያለፉትን 15 ዓመታት የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ገምግሞ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። በዚህ ግምገማው ታዲያ ከልማት ጋር ተያይዞ በርካታ ውጤቶችን ስለማስመዝገቡ ተጨባጭ በሆኑ አስረጂዎች አስደግፎ ያቀረበ ሲሆን፤ በዚያው ልክ ደግሞ ሃገሪቱን ወደአዘቅት እያወረዱ የሚገኙ ስህተቶች መኖራቸውንም አምኗል። ይህንን መነሻ በማድረግ ባካሄደው ጥልቅ ግምገማ:-

በአሁኑ ጊዜ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግስት ስልጣን የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ አገራዊ ለውጡ በስኬት ሲጓዝ የቆየው መንግስታዊ ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ማስከበሪያ ማድረግ በመቻሉ የሆነውን ያህል ይህ ስልጣን ያለአግባብ ለመጠቀም ለሚሹ ግለሰቦች በመሳሪያነት ማገልገል ሲጀምር የተጀመረው ልማት ይደነቃቀፋል፡፡ መልካም አስተዳደርም ይጠፋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ህዝብን በማስመረር ላይ ያለው ችግር ዋነኛ መንስዔ ይህ ነው፡፡

ሲል ይፋ ያደረገው ስራ አስፈጻሚ፤ ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የመንግስት ስልጣንን ያለአግባብ ለግል ኑሮ መሰረት ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌና ስህተት መታረም፤ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ እርምጃም መውሰድ እንዳለበት መወሰኑም ይታወሳል፡፡ ይህንንም:-

ዝንባሌው በሚታይባቸው ቦታዎች ሁሉ በአግባቡ እየተፈተሸ እንዲስተካከልና የድርጅታችን ጥራትና ጥንካሬ ተጠብቆ እንዲቀጥል አስፈላጊ የሆነው ርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ ወስኗል፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ረገድ ከራሱ ጀምሮ የሚታዩ የጥገኝነት አስተሳሰቦችና መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህተኝነትነ እንዲሁም የጥገኝነት ተግባራትን በጥብቅ በመታገል ይህ አዝማሚያ እንዲገታ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ዕቅዶችም አዘጋጅቷል፡፡

ሲል በሰጠው መግለጫ አረጋግጦ የነበረ መሆኑም ይታወሳል።

ድርጅቱ ይህን ነሃሴ 2008 ላይ ይበል እንጂ የካቲት 2008 ላይ ደግሞ የመንግስት የሆነው የፖሊሲ ጥናት ማእከል ዘግናኝና ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ መረጃዎች አውጥቶ የነበረ መሆኑና የሙስናው ሰንሰለትም ከብሄር እስከ ቤተሰብ የዘለቀ መሆኑ ተገልጾ የነበረ መሆኑም ይታወሳል። በዚህ ጊዜ ታዲያ ህዝቡ መንግስት ለአንዳች እርምጃ እየተዘጋጀ ነው ብሎ ተስፋ በመሰነቅ የትግሉ አካል ለመሆን ቆርጦ መነሳቱን ይፋ ቢያደርግም መልሶ ዝም ጭጭ ሲሆንበት ዝም ጭጭን መርጦ የነበረ መሆኑም ይታወሳል። ከላይ የተመለከተው የድርጅቱ ውሳኔ ለዓመት ቢቆይም ከሰሞኑ አቋሙን ያልዘነጋ መሆኑን ያሳየባቸውን ውሳኔዎች በተግባር ማሳየት ጀምሯል።

በሙስና የተጠረጠሩ 42 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ግብረ አበሮቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤትን ጠቅሰው በርካታ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃኖች ዘግበዋል፡፡ የጽሕፈት ቤቱን ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮን ዋቢ ያደረጉት እነዚህ ዘገባዎች እንዳመለከቱት መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ለረጅም ጊዜ ጥናት ሲያካሂድ ቆይቶ አሁን ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ወደ ማዋል መሸጋገሩን ነው፡፡


በዚህም በከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጠው ከደላሎችና ከባለሀብቶች ጋር በማበር የህዝብን ገንዘብ ያለ አግባብ ሲጠቀሙ የነበሩ ግለሰቦችን ተከታትሎ የመያዝ ስራው ተጀምሯል፡፡ እስካሁን ድረስ መንግስት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት 42 ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ተጨማሪ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የክትትል ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉም ተገልጿል፡፡


እነዚህ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን እና ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ እና የመስሪያ ቤቶቹ ባልደረባ ያልሆኑ ደላሎችና ግብረ አበሮቻቸው ናቸው።  


አሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ በጣም ጥቂቶቹ እንደሆኑ ይፋ ያደረገው መንግስት  በቀጣይ ቁጥራቸው እንደሚጨምርም አስታውቋል። ከአሁን በፊት በአገሪቱ ይስተዋሉ የነበሩ ከሙስና ጋር የተያያዙ የፍርድ ሂደት መጓተቶች እንዳይኖሩ የመረጃ ዝግጅቶችና ተገቢው ቅድመ ሁኔታ መደረጉም ተመልክቷል፡፡

 

ያም ሆኖ ግን አሁንም  በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የአመራር አካሉ አልተነካም የሚሉ ቅሬታዎች እየተነሱ ነው። ይህ ቅሬታ ደግሞ እውነት ያለው ይመስላል። አንደኛ ነገር እስካሁን የዘገየው በጥናት ከሆነ ሁሉንም ጠቅልሎ ለማስገባት በቂ ጊዜ አልነበረም ወይ? ካልነበረ እነዚህ ሲገቡ የተቀሩት አያመልጡም ወይ? ማምለጥ ባይቻላቸው እንኳ መረጃ አያሸሹም ወይ? በዚህ ደረጃ ወይም በጥቅሉ ከ2ቢሊዮን ብር በላይ የመዘበሩ ሃይሎች በተገለጹበት አግባብ የበላይ ሃላፊዎቻቸው ተጠያቂ መሆን አይገባቸውም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ከሁሉ በላይ ግን በየደረጃው በተደረጉ የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮችም ሆነ በፖሊሲ ጥናት ማእከል ዋነኛ ሆነው የወጡ የመንግስት ተቋማት በመጀመሪያው የእርምጃ ረድፍ ላይ አለመምጣታቸው ህዝቡን እያነጋገረው እና እርምጃውን በጥርጣሬ እንዲመለከተው እያደረገ ነው። አስረጂዎቹንም ከዋና ኦዲተር ሪፖርት እንጀምር።

 

የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ከ42 በመቶ ላልበለጠው የወረደ አፈጻጸም እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 21 ቀን 2016 ድረስ ከአጠቀላይ የፕሮጀክቱ የውል ዋጋ ብር 11,084,850,000.00 (አስራ አንድ ቢሊየን ሰማንያ አራት ሚሊየን አምስት መቶ ሺ ብር) ውስጥ ብር 5,653,273,500.00 ወይም የውሉ 60% ለሥራ ተቋራጩ  ተከፍሏል ይለናል የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት። አፈጻጸሙ ዝቅተኛና በዕቅዱ መሰረት ያልተከናወነ ከመሆኑም በላይ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ኮርፖሬሽኑ ከባንክ ለተበደረው ብድር ወለድ እስከ የካቲት 2008 ዓ.ም ድረስ ብቻ ብር 1,826,513,172.20 (አንድ ቢሊዮን ስምንት መቶ ሃያ ስድስት ሚሊየን አምስት መቶ አስራ ሶስት ሺ አንድ መቶ ሰባ ሁለት ከሀያ ሳንቲም ብር) የተከፈለ መሆኑና ፕሮጀክቱ በተራዘመ ቁጥር ምንም ገቢ ሳይመነጭ ለባንክ የሚከፈለው ወለድ በከፍተኛ መጠን ሊያድግና በፋብሪካው ዘላቂነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር መቻሉንም የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ባመለከተበት አግባብ ከላይ የተመለከቱ መስሪያ ቤቶች አመራሮች በመጀመሪያው ረድፍ ላይ መምጣታቸው ጥርጣሬን ቢያጭር ሊገርም አይገባም።

 

እንደዋና ኦዲተር ግኝቶች ከሆነ ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጪዎች በገቢ ግብር፣ በቀረጥና ታክስ፣ እንዲሁም በሌሎች ገቢ መሰብሰብን በሚፈቅዱ ሕጎች ገቢ የሰበሰቡ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ብቻ 1.13 ቢሊዮን ብር ገቢ ሳይሰበሰብ ቀርቷል፡፡ ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢን በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት ደግሞ 4.1 ቢሊዮን ብር ውዝፍ ገቢ መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡ ደንብና መመርያ ያልተከተሉ 91 መሥሪያ ቤቶች 98.7 ሚሊዮን ብር ከፍለው መገኘታቸውን፣ የግዥ አዋጅ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ የተፈጸሙ ግዥዎችን በተመለከተ ደግሞ በ79 መሥሪያ ቤቶች 324.9 ሚሊዮን ብር የመንግሥት ግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ ግዥ ፈጽመዋል፡፡

ማስረጃ ሳይኖር በወጪ የተመዘገበ 36 ሚሊዮን ብር፣ የማማከር ፈቃድ ሳይኖር ያላግባብ ተረጋግጦ የተፈጸመ 260.9 ሚሊዮን ብር የግንባታ ክፍያ መኖሩም በሪፖርቱ የተመለከተ ሲሆን፤ ሪፖርቱን ያዳመጠው ፓርላማው ለመጨረሻ ጊዜ ወደ እንቅስቃሴ እንደሚገባ፣ የወንጀል ይዘት የታየባቸው የኦዲት ግኝቶችም ላይ ዋና ዓቃቤ ሕግ እንዲላክ መወሰኑም ተመልክቷል፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳዳር ደንብ ቁጥር 190/2002 አንቀጽ 32 እስከ 35 በተደነገገው መሠረት የሰነድ ሂሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ በ113 መ/ቤቶችና በ28 ቅ/ጽ/ቤቶች ብር 5ቢሊዮን 262ሚሊዮን 275ሺ 550.73 በደንቡ መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ብር 375ሚሊዮን 557ሺ 284.38 በ6 መ/ቤቶች እና 6 ቅ/ጽ/ቤቶች ከመቼ ጀምሮ በተሰብሳቢነት እንደተመዘገበ፤ ከማን እንደሚሰበሰብ በቂ ማስረጃ ሊቀርብለት ያልቻለ ሂሳብ በመሆኑ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ያልተቻለ ተሰብሳቢ ሂሳብ ተገኝቷል፡፡

በወቅቱ ያልተወራረደው ተሰብሳቢ ሂሳቡ በዕድሜ ወይም በቆይታ ጊዜው ሲተነተን፤ ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት ብር 134ሚሊዮን 153ሺ 964.72፤ ከአንድ ዓመት በላይ እስከ አምስት ዓመት ብር 3ቢሊዮን 174ሚሊዮን 764ሺ 464.42፤ ከአምስት ዓመት በላይ እስከ አሥር ዓመት ብር 372ሚሊዮን 936ሺ 870.76 እና ከአሥር ዓመት በላይ ብር 196ሚሊዮን 565ሺ 227.12 ሲሆን፤ ቀሪው ሂሳብ ብር 1ቢሊዮን 442ሚሊዮን 465ሺ 210.85 የቆይታ ጊዜው በግልጽ ለመለየት ያልተቻለ መሆኑ በግልጽ በተመለከተበት አግባብ ከሶስት ባልበለጡ  መስሪያ ቤቶች 42 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል በእርግጥም ለጥርጣሬ ይዳርጋል። ወደፖሊሲ ጥናት ማእከል መረጃዎች ሄደን ደግሞ ነገሩን እናገናዝብ።

በሁሉም ክልሎችና በአዲስ አበባ በተደረገው ጥናት ከመሬት ልማት ዘርፍ ጋር ተያይዞ ከተነሱ ዋና ዋና ችግሮች መካከል መሬት ነክ የሆነው ኪራይ ሰባሳቢነት አንዱና ግንባር ቀደሙ ስለመሆኑ በመንግስት በኩል በተደጋጋሚ ተገልፇል፡፡ ለምሳሌ ስለዚሁ ህልውናችንን ለተፈታተነ ጉዳይ መፍትሄ ይገኝ ዘንድ ከትራንስፎርሜሽን እቅዱ ጋር ተያይዞ  በሁሉም መድረኮች በተደረጉ ውይይቶች ሙስና ስለመንሰራፋቱ፤ ጉቦ መስጠትና መቀበልም የቀልድ ያህልና የማያሸማቅቅ ደረጃ ላይ ስለመገኘቱ፤ ከጉቦ ውጪ የሚሰራ ስራ እንደሌለ፤ እንዲያውም ጉቦ መብላት ስራ ሆኗል በሚል መገለጹ ይታወሳል፡፡

የፖሊሲ ጥናት ማእከልም ባዋቀረው የጥናት ቡድኑ በተመለከታቸው የተለያዩ የመሬት ጽህፈት ቤቶች የዳሰሳ ሪፖርትም ኪራይ ሰብሳቢነት በስፋት እንዳለ ማመላከታቸው ይታወቃል፡፡  ለምሳሌም ያህል በእያንዳንዱ የሊዝ ጨረታ አስቀድሞ ለጨረታ የሚወጡ ቁራሽ መሬቶች በችካል ተለይተው ወደ ጨረታ እንደማይቀርቡ፤ ለድርድር በሚመች መንገድ በጅምላ ለጨረታ ይቀርቡና ገንዘብ ለሚሰጡ የተመቹና የሚመርጧቸው ቦዎታች እንደሚሰጡ፣ በግዥ የተገኘን ቤት ነባር ይዞታ እንደነበረ አስመስሎ ሰነድ አመቻችቶ መስጠት፣ የአያት ስም ያልተጻፈበት በዝርዝሩ ሲገኝ ተመሳሳይ ስም ፈልጎ መሙላት፣ ነባር ይዞታ በማጥራት ላይ ቤት ያልነበረውን ባዶ መሬት ህንፃ ወይም ግንባታ ያለበት አስመስሎ ካርታ እንዲሰጠው ማድረግ፣ በመመሪያ የታገደን ነገር በመጣስ ትርፍ መሬትን ማካተት፤ ከከተማው ማስተር ፕላን ጋር የሚጋጭ ፕላን ይዘው ለመጡ ማጽደቅ፣ ህንፃ ያላረፈበትን ባዶ መሬት ህንፃ እንዳለው አስመስሎ እንዲሸጥ ማድረግ፣ ከሻጭና ከገዥ ጋር በመመሳጠር በዝቅተኛ ዋጋ እንደተሸጠ አድርጎ ውል ማጽደቅ፣ ፋይሎችን ሆን ብሎ መደበቅ እና ሳይት ፕላን አዘጋጅቶ ለፕላን ማሰሪያ እና መደራደሪያ ማቅረብ፣ የጨረታው መመሪያ በሚያዘው መሰረት ሁሉንም መረጃዎች ሳያካትቱ  ጨረታ ማውጣት፣ ወደ ጨረታ የሚወጣ መሬት ከይገባኛል ነፃ ሳይሆን በችኮላ ማውጣት፣ ከጨረታ በኋላ ከህግና አሰራር ውጭ ተመሳሳይ ስም በማለት ተለዋጭ መሬት መስጠት በዚህም የተነሳ ድሃው እየተጉላላ ስለመሆኑና ተስፋ ወደመቁረጥ መሄዱን የተመለከቱ እና ለነዚህም ችግሮች ግንባር ቀደም ተዋናዩ አመራሩ  ስለመሆኑ በተረጋገጠበት አግባብ በመጀመሪያው ዙር የእርምጃ አወሳሰድ ውስጥ እነዚህን ተቋማትና ሃላፊዎች አለማግኘት በእርግጥም ጥርጣሬን ቢፈጥር ሊገርመን አይገባም።

በእርግጥ ድርጅቱም ሆነ መንግስት  ከጥዋቱ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመገንባት ሲነሱ  በአንድ በኩል መንግስታዊ ስልጣንን የህዝብና የአገር መገልገያና ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያ ለማድረግ በማሰብ ቢሆንም ባለንበት የዕድገት ደረጃ ጠንካራና ጤናማ መንግስት የመገንባት ጉዳይ ከፈተናዎች ውጭ ይሆናል ብሎ ማመን ተገቢ አይደለም፡፡ ይልቁንም እንደእኛ ባሉ የሽግግር ኢኮኖሚ ውስጥ ባሉ አገሮች ሁሉ በአንዳንዶች ዘንድ መንግስትን ከህዝብ አገልጋይነት መስመር እያስወጡ የግል መጠቀሚያ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት የማያቋርጥ ፈተና እንደሚሆን መታመን አለበት፡፡ ባለፉት ዓመታት በአገራችን የህዝብ መብትና ጥቅም ቅድሚያ አግኝቶ የተከበረበት ስርዓት ለመገንባት በተካሄደው ትግል ካላግባብ የመጠቀም ዝንባሌ ወይም ኪራይ ሰብሳቢነት ትልቁ ፈተናችን እንደሆነ ለአፍታም ቢሆን ሳይነሳ የቀረበት ጊዜ የለም፡፡ ህዝቡም ቢሆን ካላአግባብ መጠቀም የሚሹ ሰዎች የመንግስት ስልጣንን የግል ብልፅግና ማረጋገጫ ለማድረግ በመሻት በሚፈጥሩት እንቅፋት የለመለመ ተስፋው ለአደጋ ሊጋለጥ እንደሚችል ያላነሳበት ጊዜም የለም፡፡ ያም ሆኖ ግን ከላይ ከተመለከቱት የችግሮቻችን ስፋትና ጥልቀት ልክ ከላይ የተመለከቱት እርምጃዎች ውሃ አያነሱምና ምናልባትም ለትግል ወገቡን በማጠባበቅ ላይ ያለውን ህብረተሰብ ተስፋ ያስቆርጣልና በተገባው ቃል ልክ ወይም ገና አልተጠናቀቀም በተባለው አግባብ አሳማኝ የሆኑ እና የህዝቡን አንጀት ቂቤ በማጠጣት ለበለጠ የጸረ ድህነት ዘመቻ የሚያነሳሳ እርምጃ በአፋጣኝ ወስዶ ይፋ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ በኩል መንግስት ጠንክሮ እየሰራ ነውም ተብሎ ይታሰባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy